/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/ ፡ – ኦህዴድ ለቀድሞ የኢትይጵያ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ከዚህ ቀደም ቃል የገባላቸውን የመኪና ስጦታ ዛሬ አበረከተ። ዶክተር ነጋሶ ማምሻውን ለዶቼ ቨለ እንደገለጹት ሦስት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ኒሳን 2018 ሞዴል ዛሬ ከሰዓት በሗላ በኦህዴድ ጽህፈት ቤት ተገኝተው መረከባውን አስታውቀዋል።
ኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባለፈው ወር ስብሰባውን ሲያካሂድ ለቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት የገንዘብ፣ የመጓጓዣ መኪና፣ የህክምና ወጭን ጨምሮ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች እንደከበሩላቸው መወሰኑ የሚታወቅ ሲሆን መጠኑ ያልታወቀ የገንዘብ ድጋፍም ተደርጎላቸዋል።
ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ኢትዮጵያን ለ7 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉ ሲሆን በ1993ዓ.ም ባላቸው የፖለቲካ ልዩነት ስርዓቱን ጥለው ሲወጡ በሀገሪቱ ህግ መሰረት ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅማ ጥቅም እንዳያገኙ መደረጋቸው የሚታወቅ ነው።
ዶክተር ነጋሶ የፕሬዚዳንት ስልጣናቸውን ጥለው ከወጡ በሗላም በ1997 እስከ 2002ዓ.ም ለፓርላማ የግል ተመራጭ እንዲሁም እስከ2006ዓ.ም ደግሞ የቀድሞው አንድነት ፓርቲ ሊቀ-መንበር በመሆን አገልግለዋል።