“ጌታውን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” ቅዱስ ሲኖዶስ ለምን ዝም አለ?

“ጌታውን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” ቅዱስ ሲኖዶስ ለምን ዝም አለ?

/መላኩ_አላምረው/

የቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ምንኩስና ለመፈጸም ዓለም በቃኝ ብለው ወደ በረሃ የመነኑ.. በዋልድባ ገዳም ሥርዓት መሠረት ከመራራ ቋርፍ ውጭ የጣመ የላመ እህል በአፋቸው የማይቀምሱ… በእጃቸው ከክርስቶስ መስቀል በቀር የሌለ… በቤታቸው ከጸሎት መጻሕፍት ውጭ የማይገኝ… የዓለምን ክብር ንቀው ለሰማያዩ መንግሥት ራሳቸውን የለዩ… እነዚህ መነኮሳተ ዋልድባ “በሽብር ወንጀል” የመከሰሳቸው ጉዳይ ኢ-ግብረገባዊነት ሆኖ ያሳዘነኝ ሳያንስ….. ጭራሽ ለፍርድ ቤት ባሰሙት ቃል “የምንኩስና ልብሳችሁን አውልቆ” ተብለናል ማለታቸውን ሰማሁ።

“እንዴት አንድ መነኩሴ ልብሱን አውልቅ ይባላል? ይህማ ዝም ብሎ ሐሜት ነው” በማለትም ነገሩን በጥርጣሬ አይቼ ዝምታን መርጬ ነበር። ይሁንና ብዙ የቤተ ክርስቲያኗ መምህራን ጭምር (ለምሳሌ ሰባኬ ወንጌል ሙሐዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት) ጉዳዩ አሳስቧቸው ሲጽፉና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እየተደፈረ መሆኑን በአጽንኦት ሲገልጹ በማየቴ እኔም የራሴን የቅሬታ አስተያየት ለመስጠት ወደድሁ።
….
በእኔ እምነት… በሰሙ እማኞች እንደተነገረው መነኮሳቱ “የምንኩስና/የምናኔ ልብሳችሁን አውልቁ” መባላቸው ቤተ ክርስቲያኗን መናቅ ነው። ሥርዓተ ምንኩስናን መደፋፈር ነው። ይህ ጉዳይ ከማንም ይልቅ ሊያስደነግጠውና ሊያሳስበው የሚገባው ቅዱስ ሲኖዶስን ነው። ይህ የሁለት መነኮሳት የመብት ጥሰት ከመሆን እጅግ ያልፋል። በቀጥታ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተቃጣ መደፋፈር ነው። ለዚህ ጉዳይ ሲኖዶስ ዝምታን መምረጡ ያሳፍራል(እኔ ምንም ሲል ስላልሰማሁ ነው… ያለው ነገር ካለ እታረማለሁ)።

እንደወጉ ከሆነ መነኮሳቱ ጥፋት ኖሮባቸው ቢሆን እንኳን መክሮና ገሥጾ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ማረም የአባቶች የጳጳሳት ድርሻ ነበር። ገና የመታሰራቸው ዜና ሲሰማ የሲኖዶስ አባላት (በተለይ ፓትርያርኩ) በቀጥታ ወህኒ ቤት መሄድና መንግሥትን/የሚመለከተውን አካል ማናገርና ጉዳዩ ከሃይማኖት(ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን) ጋር የሚያያዝ መሆኑን በማስረዳት… ሲሆን ኃላፊነት ወስዶ ማስፈታትና ችግር ካለም በቀኖና ማስተካከል ይገባ ነበር።

ይህም ባይቻል ግን…… ቢያንስ ሥርዓተ ምንኩስና እንዳይደፈር ለወህኒ ቤቱ አስተዳደር ሥርዓቱም ማስረዳትና የመነኮሳቱ የእምነት መብት እንዳይጣስ ማሳሰብ እንዴት ይከብዳል? በእውኑ ይህንን ሲኖዶሱ ካላደረገው ማን ያድርገው? ደግሞስ ስለ ገዳማት ክብር መከራከር ከመነኮሳቱ ይልቅ የሲኖዶስ ድርሻ አልነበረምን? የመነኮሳቱን ልብስ አውልቁ ካሉት የወህኒ ቤት ሰዎች ይልቅ… ይህንን ሰምቶ ዝም ያለው የቤተ ክርስቲያኗ ራስ የሲኖዶስ ጉዳይ ያሳዝነኛል።

ለመንጋዎቹ መብት ግድ የሌለው እረኛ… የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መጣስ የማያስደነግጠው ሲኖዶስ… መኖሩ ለምን ነበር ያስፈለገው?????

አሁንም ቅዱስ ሲኖዶስ ለእነዚህ አባቶች መብት መቆም አለበት። እንደማንኛውም አካል የዳር ተመልካች መሆን የለበትም። ቢረፍድም መሽቶ አልጨለመም።

በሺዎች የሚቆጠሩ ከፖለቲካ እና ከሌሎች ወንጀሎች ጋር ስማቸው የተያያዘ እስረኞች ሲፈቱ መነኮሳቱ ማይፈቱበት ምክንያት ምንድነው? የምንኩስና ልብሳችሁን አውልቁ እስከመባል የደረሰ ድፍረት የተመላበት የመብት ጥሰት ሲደርስባቸው… እንዴት ቅዱስ ሲኖዶስ ዝም ይላል? ይህ እኮ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት የሚጥስና ክብሯን የሚያዋርድ ነውረኛ ተግባር ነው።

በዚህ ጉዳይ ዝምታን ከመረጥህ መቼ ልትናገር ነው?
ቅዱስ ሲኖዶስ ሆይ! ተናገር!

LEAVE A REPLY