እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያን በኪሱ ይዞ ሲዞር አገኘሁት!… /ቅንብር – በኆኅተብርሃን ጌጡ/

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያን በኪሱ ይዞ ሲዞር አገኘሁት!… /ቅንብር – በኆኅተብርሃን ጌጡ/

በአርባዎቹ የመባቻ ዓመታት ላይ የሚገኝ ጎልማሳ ነዉ። ሰዉ እንደ ኮረንቲ የሚፈራዉን ፖለቲካ የተቀላቀለዉ ገና በጧቱ ነዉ። የሙሽርነት ጊዜዉንም በዉል ሳያጣጥመዉ ነዉ፤ በቃሊቲ ሃኒሙን ያደረገዉ። ዘብጥያ የወረደዉም ገና የእምቦቅላ ሕፃናት ልጆቹን ጠረን ሳይጠግብ ነዉ። ዓይናቸዉ እያዬ ነዉ  ደህንነት መጥቶ ለፊጥኝ አስሮ የወሰደዉ። የዕድሜ ልክም እስራት ፍርደኛም ነበር። በእራሱ አገላለጽ ግን የሰዉን ልጅ ዕድሜ የሚወስነዉ እግዜብሔር እንጂ፤ ፍርደ ገምድሉ የሰዉ ዳኛ አይደለም ባይ ነዉ። ወጣቱ ፖለቲከኛ ከፖለቲከኛነት ባሻገርም ብዕረኛ ነዉ። ባለፉት የእስር ዓመታት ሁለት መፃሕፍትን በመድረስ ይታወቃል።

  • ያልተሄደበት መንገድ … እና
  • የሀገር ፍቅር ዕዳ …. የተሰኙ መፃሕፍት። እኒህ መፃሕፍት በእጁ ገብተዉ ላነባበቸዉም ደራሲዉን ፖለቲከኛ? ወይንስ ብዕረኛ? በማሰኘት እራሱን አንባቢዉን እንዲጠይቅ ያስገድዱታል።

ወደ ግላዊ ባሕርዩ ስንመጣ ደግሞ በእጅጉ ፈሪሃ – እግዜአብሔር ያለዉ፤ ትሕትናን ክእግር ጥፍሩ እስከ እራስ ፀጉሩ የተላበሰ ነዉ። ከዉኃና ከሻይ በቀር ሌላ የሚጎነጨዉ መጠጥ የለም። ጥም አርኪዉንና የዓለም ታዋቂዉን የጀርመን ቢራ ሳይጎነጨዉ ነዉ ጀርመንን የለቀቀዉ። ይህንን የታዘበ አንድ ሰዉ በአንድ የግብዣ ቦታ ላይ፤

የሚጠጣዉ ዉኅ፤ የሚበላዉ ሽሮ፤

እንዲህ ያለ እንግዳ ይምጣ ዞሮ ዞሮ …

በማለትም ገጥሞለታል። ሰዉ ቤት ተጋብዞ የዊስኪ ዓይነት ሲቀርብለትም፤ ጠረጴዛችሁን ለፎቶግራፍ ዲኮሬት (ለማስዋብ) ካልሆነ በቀር፤ አኔ ምንም አልቀምስም በማለት ጋባዦቹንም ሊሳለቅባቸዉ ወይም ሊተርባቸዉ ይሞክራል። ለትንሹም፤ ለትልቁም አክብሮት አይለየዉም።

ከቃሊቲ ማግስት ወደ አዉሮፓ ጎራ ብሎ የሳምንታት ቆይታ አድርጉዋል። በደረሰባቸዉ ቦታዎች ሁሉ ሰዉ ፍቅሩን ገልጾለታል። አክብሮቱን ችሮታል። የደረቅ ስንቅ ዳቦ ቆሎም ሆነ፤ የእርጥብ ስንቅ በሶ ሁሉም እንደ ኪሱ አቅም ጀባ ብሎታል። የሙያ ክሂሎቱ ያላቸዉ የህክምና ጠበብት ወገኖቹም የነፃ ህክምና አድርገዉለታል።ቤተክርስቲያንም ከካሕን እስከ ምዕመናን ከበዉታል። እስፖርት ሜዳም ጎራ ብሎ ወጣቱ እየተቀባበለ ፎቶ አብሮት ለመነሳት ተሻምቶበታል። የሰዉን ፍቅር ያገኘ፤ የሕዝብን ልብ የማረከ ፖለቲከኛ ነዉ። የአዉሮፓ መዲና በሆነችዉ ብራስልስም  በተደረገ ሕዝባዊ ስብሰባ ከዚያ ከ 60 ዎቹ ትዉልድ አዛዉንት ፖለቲከኞችና ከሎሎችም የዘመኑ ለዉጥ የነፃነት ፈላጊ ወገኖች ጋር ተገናኝቷል። አዛዉንቶቹ ፖለቲከኞች ጠያቂ፤ ወጣቱ ፖለቲከኛ መልስ ሰጭ በመሆን የፖለቲካ አዉራሽና ወራሽ ትዉልድ  (እታዲያ ዉርሱ በርዕዮተ ዓለም አለመሆኑ ይታወቅልኝ) በግንባር ተገናኝተዋል።

ዙሪያ ጥምጥም መሄዱንና የመግቢያ ማስተዋወቂያዬን እዚሁ ላይ ልግታና  ወደ ተነሳሁበት ቁምነገር ላምራ። የተወሰኑ ዓረፍተ ነገሮች በመወርወር ከላይ በመግቢያዬ ለማስተዋወቅ የሞከርኩት ወጣት ፖለቲከኛዉን አንዷለም አራጌን ነዉ። አንዷለም በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እንደተገለጸዉ፤ ከእስር መፈታት ማግስት በጥቂት የአዉሮፓ አገሮች የሥራ ጉብኝት ማድረጉ ይታወቃል። ይህንኑ የጉዞዉን ፍፃሜ ምክንያት አድርገን ጋባዡ ክፍል …. በጀርመን የኢትዮጵያዉያን የዉይይትና የትብብር መድረክ…. ያመቻቸልንን መድረክ  አጋጣሚ ተጠቅመን ስለቆይታዉ እና ስለሌሎችም ተዛማጅ አገራዊ ጉዳዮች ፍራንክፈርት አየር ማረፊያ በመገኘት አነጋግረነዋል። ተከታተሉት።

ጥያቄ – በመጀመሪያ ወደ ጀርመን ለመምጣት ምክንያት የሆነዉን የ…መዘክረ ቴዎድሮስ… ጉባዔን እንዴት ተመለከቱት? እንዴትስ ከእስር በተፈቱ ማግስት ወደ ጀርመን መጋበዝ ቻሉ? ይህን ጉባዔ ካዘጋጀዉ … በጀርመን የኢትዮጵያዉያን የትብብርና የዉይይት መድረክ… በመባል ከሚታወቀዉ የሲቪክ ተቁዋም ጋር ቀደም ያለ ግንኙነት ነበረዎት ማለት ነዉ?

መልስ  ማንም ሰዉ ፍጹም አይደለም። በፖለቲካ ጉዳይ ላይ ደግሞ ነጭ ወይንም ጥቁር የሚባል ነገር ላይኖር ይችላል። በዘመናችን ካሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር በሀሳብ እንደምንለያየዉ ሁሉ ባለፈዉ ዘመን ከተነሱ ጀግኖቻችንና የዘመኑ እሳቤ ጋር ልዩነት ሊኖረን ይችላል። ነገር ግን ማዕከላዊ እሳቤያቸዉን፤ ዝንባሌያቸዉን፤ የጀግንነት ዉሏቸዉንና ለሀገራቸዉ ያሳዩትን ቁርጠኝነት በመገንዘብ ልናከብራቸዉና  ልንዘክራቸዉ ይገባል። ይኸንን በማድረግ ለብዙ ጀግኖች መፈጠር ምክንያት እንሆናለን። ይኸንን በማድረግ  ቀና  የፖለቲካ ባሕልን እናዳብራለን። ይህንን ስናደርግ የፖለቲካና የማህበራዊ መስተጋብሮችን እናበለፅጋለን። ይኸንን ስናደርግ ከእኛ ዘመን በሁዋላ ከሚመጡ ትዉልዶች ጋር የሚያገናኘን የታሪክ አቅጣጫ እናሰምራለን። የሀገርነት ኅላዌ ድልድይ እንዘረጋለን። የጉባዔዉንም አስፈላጊነት የማየዉ ይኸንንና ይኸንን ከመሰሉ ጉዳዮች አንፃር ነዉ። በጣም የተዋጣለት ጉባዔ በማድረጋቸዉ እንኩዋንም ደስ ያላቸዉ ሳልላቸዉ ማለፍም አልፈልግም። … በጀርመን የኢትዮጵያዉያን የውይይትና የትብብር መድረክ…  በጉባዔዉ ምክንያትነት ይህንን ድልድይ ዘርግቶ ከአዉሮፓ ኗሪ ኢትዮጵያዉያን ወገኖቼ ጋር እንድገናኝ በማድረጉም ደግሜ ባመሰግነዉ ሲያንሰዉ እንጂ፤ የሚበዛበትም አይመስለኝም።

ጥያቄ  – እርስዎ ከመጡበት ከሜይ 11 ቀን ጧት ፍራንክፈርት ኤርፖርት አቀባበል ጀምሮ እስከ ቆይታዎ ድረስ ከኢትዮጵያዉያን ወገኖችዎ ጋር፤ ፍራንክፈርት፤ በርሊን፤ ኮለን እናም በሌሎችም አንዳንድ ከተሞች እየተገኙ ተነጋግረዋል። የወገኖዎችን ሀገራዊ ስሜት እንዴት አገኙት? 

መልስ– እንደ አንድ ሀገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ ከሀገሬ አያሌ ኪሎ ሜትሮችን እርቄ መጥቼ የሀገሬን ልጆች በባዕድ ሀገር ጎዳናዎች ላይ ማየቱ በራሱ ልዩ ስሜትን ይፈጥራል። ልዩ የደስታ ስሜት በልብ ዉስጥ ያፍለቀልቃል። በሌላ ወገን ደግሞ እስር ቤት በነበርንበት ወቅት ስለመፈታታችንና የኢትዮጵያም ሕዝብ የሉዓላዊ ሥልጣኑ ባለቤት ይሆን ዘንድ ለዓመታት ያለመታከት ያታገሉ እህትና ወንድሞቼ አንዳንዶቹ ኤርፖርት ዉስጥ በማደር፤ አንዳንዶች ደግሞ በሌሊት ከተለያዩ እርቀቶች ተጉዘዉ ብዙዎች ከእንቅልፍ በማይነቁበት ሰዓት የሀገራችንን ልዩ ልዩ ዝማሬዎች እየዘመሩ ሲቀበሉኝ፤  የተፈጠረብኝን ስሜት በቃላት ለመግለፅ መሞከር ስሜቱን ማበላሸት፤ ዉለታቸዉንም ማሳነስ መስሎ ይሰማኛል። ቃላት የማይገልጸዉ ልዩ የኢትዮጵያዊነት ፍቅር፤ ልዩ የወንድማማችነት ህብር ለእኔ ደግሞ በእግዜአብሔር ፀጋ የተቸረኝ ልዩ ክብር ነበር።

በጉባዔዉ ወቅትስ በዚያ ዉብ አዳራሽ ዉስጥ የተፈጠረዉን ልዩ ድባብና የኢትዮጵያዊነት አዉድስ ምን ብየ ልገልጸዉ እችላለሁ? ግሩም ድንቅ ብየ ብቻ ልለፈዉ። ብዙ ኢትዮጵያዉያን እኔን ለመቀበል የቤቶቻቸዉን ሳንቃ ብቻ ሳይሆን የልባቸዉንም ጟዳ ወለል አድርገዉ በመክፈት በፍቅራቸዉ ፀበል አጥምቀዉኛል። የልባቸዉን ደስታ፤ ምኞትና ጥልቅ ሀዘን ጭምር ያለገደብ አጫዉተዉኛል። እኔን ለማስተናገድና ለማክበር የሄዱት እርቀት በልባቸዉ ዉስጥ የተንሰራፋዉን ጥልቅ የሀገር ፍቅርና ናፍቆት እንዲሁም ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ሰፍኖ የማየት እርሃባቸዉን ያሳብቃል። አፈ- አዉጥቶ ይናገራል። በሀገራቸዉ ጎዳናዎች ከሀገራቸዉ ልጆች ጋር በክብር ለመራመድ ልባቸዉ ምን ያህል በመናፈቅ እንዳዘለ ዓይነ ውኃቸዉ ላይ ይታያል። ነገር ግን በሰዉ አገር በማንአለብኝነት የነፃነት መገፈፍን የሞት ያህል ይጠሉታል። በሕግና በሥርዓት መዳኘት፤ መሥራትና ብሎም የመኖር ልማዳቸዉና መብታቸዉ እንዲሸራረፍ ፈፅሞ አይሹም።

በተለይ አንዳንዶቹ በተማሪዎች ትግል ተሳትፎ የነበራቸዉና ከአርባ ዓመታት በፊት በላይ ከሀገራቸዉና ከወገናቸዉ ርቀዉ የቆዩ ኢትዮጵያዉያን ወገኖቻችን ሁኔታ እጅግ ያሳዝናል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ለአያሌ ዓመታት መፍትሔ ሳይበጅለት በትግሉ ወቅት የተከፈለዉ መስዋዕትነት አንሶ አሁን ድረስ በባይታወርነት በሰዉ ሀገር ታዛ እንዲኖሩና ወደ ሀገራችን ቢመለሱ የአገዛዙ ሰለባዎች ለሆኑ እንደሚችሉ በመስጋት ከሚወዱት ሕዝብና ሀገር ርቀዉ የእርጅና ዘመናቸዉን እንኩዋን በባይታወርነት እየኖሩ መሆኑን ማሰብ ልብን ያደማል። እንደ ሀገር በፍቅር መኖር አለመቻላችን እጅግ ያሳስባል። ያሳዝናልም። ሌሎችም በኢትዮጵያ ዴሞክራሲና ፍትሕ እንዲሰፍን ለዓመታት የታገሉ ወገኖችም ወደ ሀገራቸዉ ቢመለሱ የአገዛዙ ሰለባዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ከፍ ያለ ስጋት አድሮባቸዋል። ሀገራቸዉን እየናፈቁና እየተናፈቁ በአገዛዙ ባሕሪ ምክንያት ከሀገራቸዉ የራቁ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ ስናስብ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ዕርቅን ማድረግ ከቻልን ሀገራችን በሁሉም መስክ ምን ያህል ልታገግም እንደምትችል በገሃድ ያሳያል።

ጥያቄ –  ባጭሩ በተናጠልም ሆነ በስብስብ መልክ ከተገናኟቸዉ ወገኖችዎ ዉይይት በመነሳት ጀርመንን እንደ ምሳሌ በመዉሰድ ዲያስፖራዉን እንዴት አገኙት? ስለዲያስፖራዉ የሚባለዉና እዉነታዉ ተጋጨብዎት? ወይስ ሰምሮ አገኙት?

– እዉነቱን ለመናገር ከሀገሬ ከመዉጣቴ በፊት አንዳንድ ወገኖች  የራሳቸዉን የግል ተሞክሯቸዉን ተመርኩዘዉ ስለ ኢትዮጵያዊዉ ዲያስፖራ (በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገሩ ወጥቶ በሌሎች አገሮች ዉጭ የሚኖር) አስተያየታቸዉንና ምክራቸዉን ለግሰዉኝ ነበር። በበጎነት የተነገረኝ ከሰማሁትም በላይ በጣም በጎ ሆኖ ሳገኘዉ በአሉታዊ ጎን የተነሳዉ በተለይም ስሜታዊ ፅንፍ የረገጠና ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ያፈነገጠ ነዉ የሚለዉን አስተያየት ምናልባት በተለያየ ምክንያት ተሸፍኖ እንደሆነ አላውቅም። ለእኔ ግን የገጠመኝ ከተባለዉ የተለየ ነዉ።

ባደረኩዋቸዉ ዉይይቶች ሁሉ ምናልባት ለመሃላ አንድ ወይም ሁለት አስተያየቶች ሰምቼ ካልሆነ በስተቀር በጣም አርቆ አሳቢነትና ምክንያታዊነት የተሞሉ ሀሳቦችንና አስተያየቶችን የሰማሁት። ከሰከኑ ኢትዮጵያዉያን የሰከኑ፤ የበሰሉና የተሰለቁ ሀሳቦችን ነዉ ሲቀርቡ የሰማሁት። ያየሁትም፤ የገጠመኝም። የአዉሮፓዉ ዲያስፖራ ከአሜሪካዉ ይለይ ይሆን፤ በእውነት አላዉቅም። ፈጣሪ አጋጣሚዉን ከሰጠኝ ወደፊት የማረጋግጠዉ ይሆናል።

ጥያቄከጀርመን ወጣ እንበልና በሆላንድ፤ በቤልጅዬም እናም በግል ፕሮግራም ፓሪስም ተጉዘዋል፤ በተዘዋወሩባቸዉ ቦታዎች ሁሉ ኢትዮጵዉያን ወገኖችዎን ብቻ ሳይሆን፤ ሀገሯን እራሷን ከነክብር ሰንደቅ ዓላማዋ አግኝቻታለሁ ለማለት የሚያስደፍሩ አሻራዎችን ማዬት ችያለሁ ብለዉ አያምኑም?

መልስ – ከዚህ ቀደም ስለ ኢትዮጵያዉያን ሥልጣን ወዳድነት የምሰማዉ አንድ አባባል ነበር። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በኪሱ ዘዉድ ይዞ ይዞራል የሚል። አሁን እኔ በተዘዋወርኩባቸዉ ቦታዎች የገጠመኝ ከዚህ የተለየ ነዉ። … እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያን በኪሱ ይዞ ይዞራል… በሚል ቢለዉጥ ይሻል ይሆን? ካልሆነ ሁለቱንም ቢባልስ? መቼም በየደረስኩበት የገጠመኝ በጣም የተለየ ነዉ። ኢትዮጵያዉያን አብዱኪያር እንደሚለዉ በወረቀት ሳይሆን  በደም ግን የኢትዮጵያ መሆናቸዉ  ሁለንተናቸዉ ላይ ተፅፎ ይነበባል። በተለይ የአንዳንዶቹ ለአያሌ ዓመታት የዘለቀ የሀገር ናፍቆት ፊታቸዉ ላይ ይታያል። በአካል ከሀገራቸዉ ይራቁ እንጂI በመንፈስ ከሀገራቸዉ ተነጥለዉ የሚያዉቁ አይመስልም። ስለ ሀገራቸዉ ይጨነቃሉ፤ ይጠበባሉ፤ ይዘምራሉ፤ ያልማሉ። ብዙዎቹ ምንም ያህል ሀገራቸዉን ቢናፍቁም መመለስን ቢራቡም አይመለሱም። ምክንያቱም ቢመለሱ በሌሎች ወገኖቻቸዉ ለይ የሚፈጸመዉ የአፈና ተግባር እስርና እንግልት ይደርስብናል፤ ዋስትና የለንም ይላሉ። የኢትዮጵያ ሥም የተፃፈባቸዉ ኤምባሲዎችም ቢሆኑ ዜጎችን በእኩልነት አያገለግሉም። የአገዛዙ ደጋፊዎችን ብቻ ነዉ የሚያገለግሉት ብለዉ ያምናሉ። ከአንዳንዶች የኢሳትን ቲሸርት ሺጣችሁዋል በሚል ፓስፖርት መከልከሉን አጫዉተዉኛል። ኤምባሲዎች እንደ ሀገር ዉስጥ ቀበሌዎች ሁሉ የካድሬና የደጋፊዎች ልዩ መጠቀሚያዎች ሆነዋል የሚል ስጋትና እምነትም አላቸዉ። እንዲያዉም በተቃዉሞዉ ጎራ ዉስጥ ያሉ ኢትዮጵያዉያን በኤምባሲ ሰዎች እንሰለላለን ብለዉ ያምናሉ። ናፍቆትና ስጋት ተጋብተዋል።

በ 1960 ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ተሳትፎ በተለየየ ደረጃ የነበራቸዉ ወገኖችም ምንም ያህል በሀገራቸዉ ናፍቆት ልባቸዉ ቢዝልም ሀገራቸዉ ቢገቡ የሚገጥማቸዉን ችግር በመገመት ለመሄድ አይፈልጉም። በናፍቆትና በስጋት ድሮች የተቀየዱ ኢትዮጵያውያንን ማየት ስለ ኢትዮጵያ በዓይናችን ብቻ ሳይሆን በልባችንም እንድናነባ ያስገድዳል። ስለ ነፃነት ከመቼዉም ጊዜ በላይ እንድንታገል ያነሳሳል። ኢትዮጵያ የናፈቁዋትን ልጆቿን የምትገፋበት ሳይሆን እጆቿን ዘርግታ የምታቅፍበት ጊዜ መንጋትና መምጣት ይኖርበታል።

ጥያቄ –  እርስዎም ሆኑ ሌሎች የቅርብ የትግል አጋሮችዎ ለምሳሌ እነ ተመስገን ደሳለኝ፤ እነ እስክንድር ነጋ፤ እነ ናትናኤል መኮንን፤ ከእስር በመፈታታችሁ ሁሉም ኢትዮጵያዉያን በደስታ ፈንድቀዋል።

እንዴት ነዉ ይህን ደስታ ዘለቄታ ባለዉ መንገድ ኢትዮጵያን በመታደግ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠር  በሚደረገዉ ግብግብ እንደ አማራጭተፎካካሪ ኃይል ሆኖ የመዉጣት የወደፊት ዓላማ አላችሁ? ወይስ ትግላችሁ ከቃሊቲ በሁዋላ ግቡን መቷል ብለዉን ያምናሉ?

መልስ – ሕዝቡ ለእኛ መፈታት ትልቅ መስዋዕትነት ከፍሏል። አብሮን ታስሯል ብልም ማጋነን አይሆንብኝም። በመፈታታችንም ትልቅ ደስታ ተሰምቶታል። ደስታዉም ሆነ ትግሉ ከእራሱ መታሰርና መፈታት ጋርም የተቆራኘ እንጂ፤ ከእኛ ጋር ብቻ የተያያዘ አይመስለኝም። የእኛን እስራትም ሆነ ፍች ተምሳሌታዊ አድርጎ የወሰደዉ ይመስለኛል። ታግሎ ለዉጥ ማምጣት በመቻሉ የራሱንም ሃይልና የሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት በተወሰነ ደረጃ ያረጋገጠበት አጋጣሚ ይመስለኛል። በዚህም ከፍ ያለ ደስታ የተፈጠረ መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል። ደስታዉ እንዲቀጥል ትግሉን በመቀጥል ብሎም የእዉነተኛ የሉዓላዊ ሥልጣኑ ባለቤት መሆን ነዉ መፍትሔዉ። ሕዝቡ ለመብቱና ለነፃነቱ ዘብ እስከቆመ ድረስ ማንም እየተነሳ ጫንቃዉ ላይ አይፈናጠጥበትም። እስከተጎነበሰ ድረስ ደግሞ ጉልበት ያለዉ ሁሉ እየተነሳ ልጋልብህ ይለዋል። መቼም ቢሆን ይኸንን ለመሰለዉ ሁኔታ ምቹ ሆኖ መገኘት አይገባውም።

ለብዙ ዓመታት ስለብዙ ነገሮች ቃል ተገብቶልን ያዉቃል። የተገቡ ቃሎች ዉለዉ ሲያድሩ አፈርድሜ ሲበሉ ዓይናችን ሥር ሲሰባበሩ እናዉቃለን። ለወንድማማችነትና ለለዉጥ የዘረጋናቸዉ እጆች እየተረገጡ ለዓመታት በመከራ ስርጥ ዉስጥ እንድናልፍ መገደዳችንንን ይቅር ብንልም አንዘነጋዉም። ስለዚህ የእዉነተኛ ነፃነት አዉራ ጎዳና የፀና ሰላማዊ ትግል ማድረግ ነዉ። ሰላማዊ ትግል ለማድረግ የፓርቲ ብቸኛዉ መንገድ ነዉ ባይባልም መደራጀት ግን ለሰላማዊ ትግል መሠረታዊ ግባት ነዉ። ስለጉዋደኞቼ በእርግጠኝነት መናገር ባልችልም በበኩሌ ከመታሰሬ በፊት ወደ ነበርኩበት ሰላማዊ ትግል ለመመለስ ወስኛለሁ። ፈጣሪ ቢረዳኝና አቅሜ በፈቀደዉ መጠን አሁን የታየዉ የነፃነት ብልጭታ ወደ ደማቅ የነፃነት ቀትር እስኪለወጥ ድረስ አበክሬ መታገል እንዳለብኝ አምናለሁ። ለዚህ ይረዳ ዘንድ በሀሳብና በፖለቲካ እምነት ከሚመስሉኝ ወገኖች ጋር በመሆን አንድ ዓይነ ግቡ የፖለቲካ ፓርቲ ዉስጥ መምጣቴ የሚቀር አይመስለኝም። ለማንኛዉም ብዙም በማይርቅ ጊዜ ዉስጥ ሁኔታዎች ግልፅ ይሆናሉ ብዬ አምናለሁ።

ጥያቄ –  ወደሁዋላ ልመልስዎትና ከልጆችዎ፤ ከባለቤትዎ፤ ባጭሩ ከግላዊ ሕይወትዎ ይልቅ እንዴት ግፍና መከራን መቀበልና የእድሜ ልክ ፍርደኛ ታሳሪ መሆንን መረጡ? በዚህ ረገድ አትርፈዋል? ከስረዋል? ባጭሩ አርፎ ከመቀመጥ ዉድ ዋጋን የሚያስከፍል ሕይወት መምረጥን ለምን  ፈለጉ?

መልስ – መታሰርና መሞት ይቅርና መገላመጥም የምትመኘዉ ነገር አይደለም። አትመርጠዉምም። ከማንኛዉም ሰዉ ሳትበልጥ ወይንም ሳታንስ ሰብዓዊ ክብርህ ሳይገሰስ በሀገሬ ላይ መኖር ነዉ የእኔ ምርጫ። ነገር ግን ይኸንን ሥርዬት እንደሌለዉ ኀጢአት የሚቆጥር አገዛዝ ሲገጥምህ ሰዉ ለመሆን እየታገልክ የሚያስከፍለዉን እስራት፤ ሞት ሌላም መስዋዕትነት በፀጋ ለመቀበል ከመጨከን ዉጭ ሌላ አማራጭ አይቀርብልህም። ከዚህ መሠረታዊ የሕይወት መርሆ በመነሳት ነዉ እኔም መዉጣትና መዉረድ የነበረብኝን የግፍ ኮረብታ ለመጋፈጥ የተገደድኩት።

ይኸንን በመሰለዉ የሕይወት መስመር ላይ በገዛ ሀገሬ፤ በሀገሬ ልጆች በተፈጸመብኝ ግፍ ሀዘን አልተሰማኝም። አልተበሳጨሁም። ወይንም የልጆቼና የባለቤቴ ሀዘንና እንግልት ዉስጤ ድረስ ዘልቆ አልተሰማኝም ማለትም  እራሴን መዋሸት ይሆንብኛል። ነገር ግን በታሪክ ትክክለኛ መስመር ላይ እንደቆምኩ አምናለሁ። ከሁሉ ለላቀ ዓላማ አኔ በግል ቤተሰቤም እንደ ቤተሰብ ዋጋ እንደከፈልን ይሰማኛል። በዚህ ትልቅ የህሊና እረፍት አለኝ። ከሚገባኝ በላይ ሕዝብ አክብሮትና ፍቅር ችሮኛል። ይኸንን ደግሞ ምንም ያህል ከፍለን የምንገዛዉ ነገር አይደለም። ስለዚህ በበኩሌ ትልቅ ደስታና ኩራት ይሰማኛል። ያለ መከራ ፀጋ አይገኝም እንደሚባለዉ ለትክክለኛዉ ነገር ዋጋ በመክፈሌ ደስታ ይሰማኛል።

የሰዉ ልጅ ነፃነቱን ከተገፈፈ ከሰብዓዊ ልዕልናዉ ይወርዳል። ሰዉ ያለ ነፃነቱ ምንድነዉ ነዉ? የሚለዉን ጥያቄ አነሳለሁ። ለእኔ ሰዉን ሰዉ የሚያሰኘዉ ምናልባትም እንደሚባለዉ ሥራዉ ሳይሆን ነፃነቱ ነዉ። ለነፃነት ደግሞ እንግልትና እስራት አይደለም፤ ሞትም አይበዛባትም። ስለዚህ አትራፊ ነኝ። እጅግ አትራፊ ነኝ። ደስታዬ ሙሉ የሚሆነዉ ግን በኢትዮጵያ አሳሪና ታሳሪ፤ አሳዳጅና ተሰዳጅ፤ ገዳይና ሟች በሌሉበት ሁኔታ የሰዎች ሰብዓዊ ልዕልና ከፍ ብሎ የሚከበርበት ዴሞክራሲያዊ ሀገር መገንባት ስንችል ነዉ። የፍትሕ፤ የነፃነትና የወንድማማችነት ፀሐይ ስትወጣ  ትርፌ ሚሊዮን እጥፍ ይሆናል፤ ደስታዬም እጥፍ ድርብ ከመሆን አልፎ ገደብ ያጣል።

ጥያቄከዚሁ ጥያቄ ጋር በተያያዘ፤ ከሰዎች ጋር ሲወያዩ ጆሮዬን ጣል አድርጌ የሰማሁት ኅሊናዬ ግን ያልተቀበለዉ አንድ ነጥብ አለ። ልጆቼንና ባለቤቴን የትም ሜዳ ጥዬ እኔ ላመንኩበት ዓላማ ብቻ ሕይወቴን ማስገደዴ የእኔን … ሰልፊሽነት… ያሳያል ሲሉ ይደመጣሉ። ይህ ቃል ደግሞ በተለምዶ ትርጉሙ ከእራስ ወዳድነት፤ ከመስገብገብ፤ ከሁሉም በፊት ለግል ጥቅም (አድቫንቴጅ) ኅሊናን ሽጦ ማደርን አመላካች ነዉ። እንዴት አንድ የነፃነትና የዲሞክራሲ የለዉጥ ሐዋርያ መላ ሕይወቱን ለሀገሩ አሳልፎ በመስጠቱ ሰልፊሽ ሊባል ይችላል ብለዉ ያምናሉ?  በዚህ አባባልዎስ እነ ተመስገንና እነ እስክንድርና ሌሎቹም የቅርብ የትግል አጋሮችዎ ቅር የሚሰኙ አይመስልዎትም? (የራስዎትን እንተወዉና ሌሉቹንም እኮ ሰልፊሾች ብለዉ እየተሳደቡ ነዉ!)

መልስ የዚህ ፍልስፍና በለቤት እኔ አይደለሁም፤ የፍልስፍናዉ ባለቤት .. አያን ራንድ .. ነች። እኔም በሀሳቧ እስማማለሁ። ሰዎች ከተለያዩ እሴቶቻችን በመነሳት በሕይወት ዘመናችን ከዉነናቸዉ የምናልፋቸዉ ነገሮች ከሁሉም አስቀድሞ ታሳቢ የሚያደርጉት ከህሊና ጋር ሰላም መፍጠር ነዉ። የህሊና ሰላም ደስታን ይሰጣል። ምክንያታዊና ሞራላዊ የሆነ ተግባር ፈፅመዋል የሚል ማረጋገጫ ይሰጣል። በዚህ ምክንያት ደስታ ይገኛል። ያንን አለማድረግ ወይንም ተቃራኒዉን መፈጸም ደግሞ የህሊናን ጩኸት ይቀሰቅሳል። በዚህም ምክንያት ሰላም ይታጣል። ደስታ ይርቃል። ስለዚህ እኔ ከሁሉ አስቀድሜ ትግሉን የሕይወቴ አካል ያደረኩት የወገንንም ጭንቀት ለመመለስ ሳይሆን የህሊናዬን ጩከት ለማስታገስ ነዉ። አንድ ሰዉ የራሱን ደስታ ሲያስቀድም እራስ ወዳድ መሆኑን ያሳያል። የእኔም እንደዚሁ ነዉ። ምናልባት ከፖለቲካ እርቄ እንደ ሌሎች አባቶች ሳልታሰር ከልጆቼና ከባለቤቴ ጋር ብኖር በሁኔታዉ እነርሱ የሚደሰቱበት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የእራሴ የህሊና ጩኸት በለጠብኝ። በጥንቃቄ ነገሮችን ወስደን ብንመረምር የሁላችንም የሕይወት መንገዶች ላይ የምንወስናቸዉ ዉሳኔዎች የየግላችንን ደስታ  ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ልንደርስበት እንችላለን። ሁላችንም በሕይወት ዘመናችን ምን አከናዉነን ብናልፍ ይሻላል?  የሚለዉ ጥያቄ መልስን ወስደን ይመስለኛል ተግባራዊ ለማድረግ የምንቀሰቀሰዉ። የአመክንዮ ድሮቻችንና የግብረ ገብነት ሕግጋቶቻችን በአመዛኙ ትክክልና ስህተት ብለዉ ያሰመሯቸዉን መስመሮች እንፈትሻለን። ትክክል በምንለዉ መንገድ እንራመዳለን። እንዳልኩት የትክክለኛነት ማረጋገጫ ከህሊናችን ይደርሰናል። ያለፀፀትና መረበሽ በደስታ ስለምናምንበት ዋጋ እንከፍላለን።

ተመስገን፤ በቀለም ሆነ እስክንድር በሰዎች ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት የሚያምኑ በመሆናቸዉ እምነቴን በግልፅ በመናገሬ ቅሬታ ይገባቸዋል ብዬ አላምንም። እራሳቸዉን እንደፍጹምና ለሕዝብ የተለየ ባለዉለታ አድርገዉ የሚቆጥሩ አይመስለኝም። በከፈሉት መስዋዕትነት የሚዝናኑና የሚመጻደቁ ሳይሆኑ ለሌላ መስዋዕትነት የተዘጋጁ የነፃነት ታጋዮች መሆናቸዉን ነዉ የማምነዉ። እዉነተኛ የነጻነት ታጋይ ደግሞ ሌላዉ ሀሳቡን በነጻ ሲገልጽ ይደሰታል እንጂ፤ የእኔን መስዋዕትነት ያሳንሳል (ያኮስሳል) በሚል የሚከፋ አይመስለኝም።

ጥያቄ ባለፈ ታሪካችን ብዙዉን ጊዜ መንግሥትን ለመለወለጥ የምንጠቅምበት ስልት እርስ በርስ (ወንድም ወንድሙን) በመገዳደል ቤተ መንግሥት መግባት ነበር። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በሕዝባዊ እምቢተኝነት (ሰላማዊ ትግል) አምባገነናዊ ሥርዓቱን የማሽመድመድ ምልክት እየታየ ነዉ። በሀገራችን መሠራታዊ ለዉጥን የማምጣቱ የመታገያ ስልት ከመሠረቱ እየተናደ አይመስልዎትም?

መልስ – ሠላማዊ የትግል ስልት ለኢትዮጵያችን አዲስ አይደለም። በተለይም የኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ትግል ለረዥም ዓመታት የተራመደበት መንገድ ሰላማዊ የትግል ስልት ነዉ። ወደሁዋላ ላይ ሃዲዱን ቢስትም። ለዘመናት የገነነዉን ንጉሣዊ አገዛዝ ለግብዓተ መሬት ያበቃዉ (ያደረሰዉ) የትጥቅ ትግል አይደለም። የተማሪዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰላማዊ ትግል ነዉ። በወቅቱ የነበረዉ ሥርዓትም የዜጎችን የተቃዉሞ መብት ከማክበር አንፃር ከእርሱ በሁዋላ ከመጡት አገዛዞች በጣም የተሻለ እንደነበር በጊዜ መነፅር ወደሁዋላ አይተን መናገር ይቻለናል። ሁልጊዜም የሚደንቀኝ ግን ንጉሣዊዉን ሥርዓት በሰላማዊ መንገድ የተቃወሙ ሰዎች ሥልጣን ላይ ሲወጡ እንዴት ቢያንስ የተቃወሙትን ሥርዓት ያህል የሕዝብን የመቃወም መብት ሊያከብሩ አልቻሉም ነዉ? ከሁሉ በላይ ቅስምን የሚሰብረዉ ግን እንዴት በዚያ ዘመን የመቃወም መብቱን ተጠቅሞ አገዛዙን የታገለ ስብስብ (ቡድን) ባዶ እጃቸዉን ወጥተዉ መብታቸዉን የሚጠይቁ ወጣቶችን በገፍ በጥይት አረር ይበላል? የሚለዉ ነዉ።

ለማንኛዉም የሰላማዊ ትግል መስመር ከዘመን ጠገቡ የመገዳደል ባሕላችን አንፃር ገና ጥቅም ላይ በቅጡ ያዋልነዉ ነገር ግን አብዝተን ልንሄድበት የሚገባን መንገድ ነዉ። እርሱ ወደ ፓለቲካ ባሕላችን ፊት ለፊት ሲገባ የመገዳደል በሕላችን በሁዋላ በር ይወጣል። እንደተባለዉምም ከመሠረቱ ይናዳል።

ጥያቄ –   እርስዎ … ያልተሄደበት መንገድ… በሚለዉ መፅሐፍዎ  ስለ ሠላማዊ ትግል በሰፊዉ አትተዋል። በመፅሐፍዎ የገለጹት መሪ ሀሳብ በአሁኑ ጊዜ በተግባር እየተተረጎመ ነዉ ብለዉ አያምኑም? … ያልተሄደበት መንገድ… የሚለዉን መፅሐፍ በ 2005 ለንባብ ሲያበቁ ያልተሄደበትና የተከለከለዉ መንገድ በር ተከፍቶ እንዲህ ባጭር ጊዜ ይኬድበታል (በተግባር ይተረጎማል) ብለዉ አስበዉ ነበር?

መልስ ሠላማዊ ትግል የእዉነተኛ ንጋት መንገድ መሆኑን ተጠራጥሬ አላውቅም። ዴሞክራሲም የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የኢትዮጵያችን መዳረሻ ስለመሆኑ ተጠራጥሬ አላዉቅም። አሁን ያለዉ ሁኔታ በጎ ጅምር ስለመሆኑ ብስማማም የተለየ ነገር ጨብጠናል ብዬ አላምንም። ዋናዉ ቁምነገር የሕልማችን በፍጥነት የመወለድና ያለመወለድ ጉዳይ የሚወስነዉ በሕዝቡ ተባብሮና ተደራጅቶ የመታገልና ያለመታገል ጉዳይ ላይ ነዉ። በተደራጀነዉና በታገልነዉ መጠን ሕልማችን የሚወለድበት ቀን ወደ እኛ ይገሰግሳል።

ጥያቄ –  በዚሁ ..ያልተሄደበት መንገድ በሚለዉ መፅሐፍዎ ገፅ 271 ላይ …በእዉነት መቼ ነዉ ፖለቲካችን ከአፈ-ሙዝ አዙሪትና ከጽንፈኛ ፖለቲካ ወጥቶ ያሸነፈዉ አሸንፎ ተጨባብጠን የምንለያየዉ? …የማንፈራዉ ግን የምናከብረዉ መሪ መቼ ይኖረን ይሆን? የሚል አገላለጽ ተጠቅመዋል። ዶ/ር ዓቢይ አህመድ ለዚህ አገላልጽዎ መልስ የሚሆኑ መሪ ይመስልዎታል?

መልስዶ/ር ዓቢይ በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ ባሕል በዉል የማናዉቀዉ ነገር ግን በጣም የሚያስፈልገንን የፖለቲካ ባሕል ጅማሮ እያሳዩን ነዉ። ለዚህ ሕዝቡ አክብሮት ችሯቸዋል። ተገቢም ነዉ ብዬ አምናለሁ። ከምንፈልገዉ አንፃር ሲታይ ግን ምንም አልተራመድንም። ገና በበጎ ንግግር ነዉ፤  አክብሮታችንና ድጋፋችንን ያልነፈግናቸዉ። የተባለዉን ዓይነት መሪ መሆን ቢችሉ ለኢትዮጵያዉያን ሁሉ የአዲስ ዘመን ንጋት ብሥራት ይሆናል። ክብሩ ለእርሳቸዉ በግል ለኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለሌሎቻን ደግሞ እንደ ሕዝብ ከፍ ያለ ይሆናል። ፈጣሪ ይርዳቸዉ። እኔም ተስፋ ላድርግ፤ ተስፋ አለኝ።

ጥያቄ –  እርስዎ ጋር ባደረኩት ቆይታ በማየት ያስተዋልኩት አንድ ነገር አለ። ትንሹም ትልቁም፤ ሴቱም ወንዱም፤ ምዕመኑም፤ ካህኑም፤ እስፖርት ስፍራም፤ ቤተክርስቲያንም ለእርስዎ ያለዉን አክብሮትና ፍቅር በመግለጽ ሁሉም አብሮዎት ፎቶግራፍ ለመነሳት ይሽቀዳደማል። ቀደም ባሉት ጊዜያት ግን እንዲህ ዓይነት ሰዎች በዞሩበት ላለመታየት ሽሽት ወይም ፍርሃት ነበር። እኛ ዲያስፖራዎችም ብንሆን ከካሜራ ጋር ጠበኞች ነበርን። አሁን ግን  ከካሜራም ጋር እርቅ የወረደ ይመስላል። ምክንያቱ ምን ይሆን ብለዉ ያስባሉ?

መልስ – ድሮዉንም ቢሆን ሕዝቡ በጎ የሰሩ ሰዎች ናቸዉ ብሎ ሲያምን አክብሮትና ፍቅር እንደነበረዉ አምናለሁ። ነገር ግን በወቅቱ የአገዛዙ ፈርጣማ ክንዶች ሕዝቡን ትልልቅ የፍርሃት ቆፈን ውስጥ ጥለዉት ነበር። አሁን ደግሞ በሕዝብ የተባበረ ክንድ ሕዝብ ከአገዛዝ ጨለማ ወደ ዴሞክራሲ ንጋት የሚወስድ ብልፅታን አይቷል። ፍርሃትም በከፍተኛ ሁኔታ ተስብሯል። ለዚህም ይመስለኛል። ይኸንን የመሰለ ለዉጥ የምናዬዉ።

ጥያቄ –  ትንሽ እንዲቆዝሙ ለማድረግ፤ በትዝታ ፈለግ ወደሁዋላ ልመልስዎትና በ 1997 በቅንጅት እንቅስቃሴ ወቅት ታስራችሁ በነበረበት ወቅት ፈርማችሁ በይቅርታ ከእስር መፈታታችሁ ይታወሳል፤ በአሁኑ ጊዜ ግን ፈርሞ ለመዉጣት ፈቃደኞች ሆናችሁ አልተገኛችሁም። የቃሊቲ ኑሮ ስትለማመዱት ጣማችሁ ማለት ነዉ? በዚህ ዙሪያ ያለዉ ምስጢርስ ምን ሊሆን ይችላል ብለዉ ይገምታሉ? ከዚሁ ጥያቄ ሳንወጣ በእንፈርምና አንፈርምም እሰጥ አገባ ታሪክ የፍልሚያዉ የረድፍ አሰላለፍ ምን ይመስል ነበር?

መልስ – እያንዳንዱ ዓዉድ የዉሳኔዎቻችን አቅጣጫዎች ላይ ተፅእኖዉን ያሳርፋል። የሁዋለኛዉ ከቀደመዉ የመማርም ትልቅ አጋጣሚ ይኖረዋል። በ 1997 እንፈርም-አንፈርም ላይ የነበረዉ አሰላለፍ ትኩረቱ እነማን ምን አቁዋም ያዙ፤ የሚለዉ እንጂ፤ ለምን  ይህን ያዘ የሚለዉን አይመልስም። ጠቃሚዉም ለምን የሚለዉን ጥያቄ በመመለስ የሚቀሰም ትምህርት ካለ እርሱን መቅሰም ካስቻለን ነዉ። በዚህ ሁኔታ እርሱን መመለስ አይችልም። አስላለፉም ይጠቅማል ብየ አላስብም። የአሁኑ ዙር ይቅርታ የመፈረምና ያለመፈረም ጉዳይ ሲነሳ መቼም ፈገግታ ለማጫር እንጂ፤ (ግን ፈገግ እያሉ ነዉ) ቃሊቲ ምቾት ይኖረዋል ከሚል መነሻ እንዳልተሰነዘረ ግልፅ ነዉ። ሚስጢሩ፤

1ኛ. በእኔ በኩል መዋሸት በፈጣሪ ዘንድ ኃጤያት መሆኑን ሽለምገነዘብ ከገዥዎች ይልቅ ፈጣሪን መፍራት ተገቢ መሆኑን ስለማምን እንዲያዉም ገዥዎች የሚያስከብር ተክለ-ሰብእና ካላቸዉ ማክበርና መዉደድ እንጂ፤ መፍራት ተገቢ አለመሆኑን  ስለማምን፤ በተለይም በዉሸት ዶሴ፤ በዉሸት ምስክርና አስፈፃሚ ይቆጣጠረዋል ብየ በማምነዉ …ፍርድ ቤት… የተሰጠን የግፍ ዉሳኔ እዉነት ነዉ፤ ይቅርታ ብሎ መጠየቅ እራስን መናቅ ነዉ። በእርግጥ ጥፋተኛ ብሆን ደግሞ ወረቀት ላይ መፈረም ሳይሆን እንደ ባሕላችን ድንጋይ ተሸክሜ ይቅርታ ብጠይቅም ከፍ ያለ ክብር ይሰማኝ ነበር።

2ኛ. እስከ መቼ ነዉ ገዥዎች አንገታችን ላይ እየቆሙ ባስጨነቁን ቁጥር ዋሽተዉ እንድንዋሽ ባስገደዱን ቁጥር ለእኩይ ዓላማቸዉና ተግባራቸዉ ተገዥ የምንሆነዉ? ይኸ  የዉርደትና የዉድቀት መንገድ አንድ ቦታ ላይ የሚከፈለዉ መስዋዕትነት ተከፍሎ መቀየር ነበረበት። በእስክንድርና በእኔ በኩል ገና ሳንታሰር ጀምሮ ይኸንን መስዋዕትነት ለመክፈል ቁርጠኝነቱ ነበረን። ጊዜዉ ሲደርስ ሆኖ የመገኘትና ያለመገኘት ጥያቄ ነበር። ሆነን እንድንገኝ ደግሞ የፈጣሪ ፀጋ በዛልን።

3ኛ. ነገ የማያልቅ መንገድ ነዉ። ሁላችንም በዚህ መንገድ ላይ ለጥቂት ዘመናት ተጉዘን ወደ እዳሪ እንጣላለን። ትዉልድ ግን በዚህ መንገድ ላት ተቀጣጥሎ ይቀጥላል። ለልጆቼና  ላልተወለዱ ልጆቻችንም ጭምር ይኸን መሰል ያልተገባ ነገር ጥዬ ከማለፍ ይልቅ በአስር ቤት ለረዥም ዓመታት መከራን መቀበል የተሻለ ምርጫዬ ነበር። በእነዚህና ሌሎች መሰል ምክንያቶች ነዉ ይቅርታ ፈርሜ ላለመዉጣት የወሰንኩት። ሌሎቹ ጉዋደኞቼም  ወደ ግንዛቤ የከተቷቸዉ ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ታሳቢ ማድረጉ ተገቢ ነዉ።

ጥያቄ –  በቆይታዎ በሚያደርጉዋቸዉ ንግግሮች፤ ጭዉዉቶች ስለ ቂም በቀልና ስለ ገራፊዎችዎም፤ ስላሳደዱዎትም ሰዎች ምንም ነገር ሲሉ አይደመጡም። የት አባቱ፤  እኔ ቆሜ እየሄድኩ እሱ አይኖራትም ..ወዘተ ወዘተ… የሚለዉን አበሻዊ ወኔያዊ ፉከራ ወዴት አዉልቀዉ ጣሉት? ወይንስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ማደግዎ ከሕገ ኦሪቱ ይልቅ አመዛዝነዉ በሕገ ሐዲስ ኪዳን ሕይወትዎን ለመምራት ተፅዕኖ አሳድሮብኛል ይላሉ?

መልስ የሌለህን እንደማትሰጠዉ ሁሉ፤ በልብህ ዉስጥ ያልቁዋጠርከዉን ነገር መናገር ያስቸግራል። ከህሊናህ ጋር ዘመንህን በሙሉ መፋለም ግድ ይሆንብሃል። በተለያዬ ቦታ እንደገለጽኩት ደረጃዉ ይለያይ እንጂ፤ ቀድሞዉንም በሰላማዊ የትግል ስልት ለዉጥ ይመጣል ብየ ገና ጥዋት መንገዱን ስጀምር ፍቅር፤ እርቅና ወንድማማችነት የትግሉ ግቦች ብቻ ሳይሆኑ በትግሉም ወቅት መሠረታዊ ቁምነገሮች መሆናቸዉን ተገንዝቤና ሰላማዊ ትግልን የሃይማኖት ያህል በመቀበል ነዉ፤ ጎዳናዉን  የጀመርኩት። ጊዜ ወስዶ ስለሀገራችን ኢትዮጵያ ችግሮች የሚያስብ ሰዉ በዉል የሚገነዘበዉ ችግር የፖለቲካ ባሕላችን በአያሌ ሕፀፆች የተሞላ መሆኑን ነዉ። ጠፍ መሬት፤ ጥሩ ምርት እንደማይሰጥ ሁሉ የተበላሸ የፖለቲካ ባሕልም የሰመረ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለቤት አያደርገንም።

መሪዎቻችንን ያበቀላቸዉ ጠፉ የፖለቲካ  ባሕላችን ነዉ። ሕዝቡንም ለዘመናት የአገዛዝን ቀንበር በአርምሞ እንዲስብ ያደረገዉ ይኸዉ የፖለቲካ ባሕላችን ነዉ የሚል እምነት አለኝ። በቀላሉ ስለዚህ መቀየር መዘመን ይገባዋል። ደጋፊ ለማብዛትና ምናልባት የደም ፍላትን ለማስታገስ መግደል፤ ማሰርና ማሰቃየት ይቀል ይሆናል። ይህ መንገድ የዉድቀት መንገድ ስለመሆኑ ከኢትዮጵያና ከሕዝቧ በላይ ማን የማያዋላዳ እማኝነት ሊሰጥ ይችላል። ስንገድል የሟቹን ሥጋ የራሳችንን መንፈስ (ኅሊና) እንገድላለን። ስናስር በሰዉ ስቃይ ስንደስት መሠረታዊ የሰብዕና ቀዉስ ሰለባዎች መሆናችንን ያሳያል። አንዳንዶቻችን በዉል ባልተረዱት ነገር በእኛ መታሰርና በልጆቻችን ልብ ዉስጥ ስለፈሰሰዉ እንባ ደስተኞች ስለ መሆናቸዉ በወቅቱ ሰምቼያለሁ። ለአሳሪዎችም ሆነ ለእነዚህ ወገኖቼ የልጆቼ ስቃይ እንደሚያሳዝነኝ ሁሉ የሚገኙበት የተቃወሰ ሰብዓዊ ጤንነታቸዉ ያሳዝነኝ ነበር። ይኸንን መድገም አልመኝም። ሰዎች ሊያደርጉባችሁ የማትፈልጉትን እናንተም በሰዎች ላይ አታድርጉ የሚለዉ ወርቃማ ቃል ሕግ በአብዛኛዉ ሃይማኖቶቻችን ላይ ተፅፏል። በእኔና በቤተሰቤ ላይ የደረሰዉ ስለምን በሌሎች ወገኖቼ ላይ እንዲደርስ እሻለሁ?

ፍቅር ዉስጥ ፍትሕ አለ። ፍቅር ከፍትሕም በላይ ነዉ። ፍቅር የፍትሕ ፍትሕ፤ ሰላም ደግሞ የሰላም ሰላም፤ ሰላም ደግሞ የልማትና የሌሎች በጎ ነገሮች ሁሉ መሠረት ይሆናል። በዚህ መሠረታዊ ነገር ከልብ ስለማምን ነዉ፤ ስለ ፍቅርና እርቅ ወንድማማችነት ደጋግሜ የምናገረዉ። በፍቅር፤ በእርቅና በወንድማማችነት ማእዘኖች ላይ ጠንካራና ዴሞክራሲያዊ ሀገር ልንገነባ እንችላለን። ይገባናልም። ቤተክርስቲያን አካባቢ ከሌላዉ ኢትዮጵያዊ የላቀ የሃይማኖት ትምህርት ግንዛቤ እንዲኖረኝ ስለማስቻሉ እርግጠኛ አይደለሁም። የተለያዩ ሃይማኖቶች ብንከተልም ኢትዮጵያዉያን በአመዛኙ ሃይማኖተኞች እንደሆንን እረዳለሁ። ብዙዎችም እምብዛም ቤተ እምነቶች አካባቢ ሳያዘወትሩ እጅግ የላቁ የእምነት ሰዎች ሲሆኑ ማስተዋል ይቻላል። እንደ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ያሃይማኖት ባሕሉ ተፅዕኖ በእኔም ላይ ሲታይ ግን የተለየ አያደርገኝም።

ጥያቄ –  ከመፅሐፍ ምን ዓይነትና የማንን መፅሐፍ ማንበብ ይወዳሉ? (በማርቲን ሉተር ኪንግ እንደተለከፉ ስለሚታወቅ፤ ከዚያ በተጨማሪ ማለቴ ነዉ) ከዚሁ ጥያቄ ጋር እናዳብለዉና ከሀገርኛ ሙዚቃስ ምን ዓይነት ሙዚቃና ያማንኛዉን ከያኒ ሙዚቃ (ዘፈን) ማዳመጥ ያዘወትራሉ?

መልስ – እንደተጠቀሰዉ ለዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ያለኝ ፍቅር የተለየ ነዉ። ፅሁፎቹና ንግግሮቹ ለእኔ የመንፈስ ምግብ ናቸዉ። ከመታሰሬ በፊትም ጥዋት የእርሱን አንድ ነገር በማንበብ ነበር ሥራ የምጀምረዉ። ንግግሮቹ ለእኔ የፀሎት ያህል ይመስጡኛል። የጋንዲ መፃሕፍቱ የተግባሩን ያህል ባይመሰጡኝም የእርሱንም አነባለሁ። የተለያዩ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ መፃሕፍትን ለማንበብ እድል አግኝቻለሁ። የፍልስፍና መፃሕፍትንም በፍቅርና በተመስጦ ነዉ የማነበዉ።በደራሲ መወሰን አልችልም።አልፈልግምም። ከይዘት አንፃር ግን ከፍ ብዬ የጠቀስኩዋቸዉ ይዘቶች ያሏቸዉን መፃሕፍት ማንበብ ያስደተኛል።

በልጅነቴ የኤፍሬም ታምሩና የነፃነት መለሰን ዘፈኖች በጣም አዳምጥ ነበር። ለኤፍሬም ያለኝ ቦታ ከፍ ያለ እንደነበር ቤተ ዘመድና ወዳጅ ሁሉ እንደ ታሪክ የሚያነሳዉ ነዉ። ሳጠና እንኩዋ የእርሱን ሙዚቃ እያዳመጥኩ ነበር የማጠናዉ። ከሀገር ቤት ስወጣ አባይ በርሃ ዉስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አዉቶብስ ሲመጣ የነፃነት መለስን ይላል ዶጁ ፏፏ የሚለዉን እየሰማሁ ነበር። በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ በቴፕ የሰማሁትም ይኸዉ ሙዚቃ ይመስለኛል። የድምፅዋ ቀለምም ደስ ይላል። የጋሽ ጥላሁንን ሙዚቃዎችንም ከፍ ባለ ስስት ነዉ የምሰማቸዉ። ነገር ግን እኔ የምወዳቸዉ ዘፋኞችም ሆኑ ዘፈኖች በጥቂቱ የሚቆጠሩ አይደሉም።የሄለን በርሄ፤ የአበባ ደሳለኝን፤ የማህሌት ገብረጊዮርጊስን፤ የዘሪቱ ከበደን፤ የሌሎችንም አያሌ ወንድና ሴት ዘፋኞችንም ዘፈኖች እሰማለሁ። እወዳለሁም።

ነገር ግን ለእኔ በሙዚቃዉ ዓለም ንግሥት እና ንጉሥ ብየ የምወስዳቸዉ በድምፃዊነት ብቻ ሳይሆን በምናብ ምጥቀታቸዉና በስብዓዊ ከፍታቸዉ ለእጅጋየሁ ሽባባዉና ለቴዎድሮስ ካሳሁን የተለየ ቦታ አለኝ። በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ ምጤን ሲያደምጡልኝ ያልቻልኩትን ሲያዜሙ፤ ሲቀኙልኝ ለእነርሱ ያለኝ ፍቅርና አክብሮት በዚያዉ መጠን ከፍ ያለ ነዉ።

ስለ ሰጡኝ ማብራሪያ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ። መልካም ጉዞ ይሁንልዎ!

LEAVE A REPLY