እስረኞች ሲፈቱ አይነናችሁ ለሚቀላ /ማህሌት ፋንታሁን/

እስረኞች ሲፈቱ አይነናችሁ ለሚቀላ /ማህሌት ፋንታሁን/

ይድረስ እስረኞች ለምን ተፈቱ ይፈታሉ ለምትሉ

በእስር ላይ እያሉ በደረሰባቸው ድብደባ እና ተገቢ ህክምና ሳይሰጣቸው ህይወታቸው እዛው እስር ቤት ሆነው ላለፉት፤ ኢንጅነር ተስፋሁን ጨመዳ ፣ ኒሞና ጥላሁን፣ ሙባረክ ይመር፣አየለ በየነ፣ አብደታ ኦላንሳ እና ሌሎችም በእስር እያሉ ሳይገባ ህይወታቸው ላለፉ እስረኞች ቤተሰቦች/ወዳጅ ዘመዶች የእስረኞች መፈታት ምንድነው?

ምርመራ በሚል ሰበብ አካላቸው ለጎደለባቸው ለእነ አበበ ካሴ፣ ከፍያለው ተፈራ፣ አስቻለው ደሴ፣ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን እና ሌሎች በርካቶች ከእስር መፈታት ምንድነው?

ተፈቱ የተባሉት እስረኞች ከሚደርስባቸው አካላዊ እና አእምሯዊ ጉዳት በተጨማሪ ህገ መንግስቱ የሚፈቅድላቸውን ከቤተሰብ የመገናኘት እና ክሳቸውን የመከላከል መብታቸውን በሚጋፋ መልኩ (አብዛኛዎቹ ከቤተሰቦቻቸው ተገናኝቶ ጠበቃ ለማቆም እና መከላከያቸውን ለማሰባሰብ ቤተሰቦቻቸውን ለማግኘት ስለማይችሉ ሳይከላከሉ ነው የሚፈረድባቸው)።

ከመኖሪያ ቤታቸው እና ቤተሰቦቻቸው በርካታ ኪሜ ርቀት ላይ ነው ክስ የተመሰረተባቸው፤ ታስረውም እንዲቀመጡ የተደረገው። በሁለት እና ሶስት አመት ፍርድ ቤት መመላለስ ብቻ ፍርድ ማግኘት እድለኝነት ነው። ፍርድ ቤቶች የሚሰጣቸው ቀጠሮ በጣም ረጃጅም ነው። ሌላም ብዙ ፍትህ የማግኘት መብታቸውን የሚፃረሩ ዘርዝሬ የማልጨርሳቸው በደሎች ደርሶባቸዋል። እየደረሰባቸውም ነው። ይህን ሁሉ አሳልፈው ለምን ተፈቱ ይባልልኛል።

ከተፈቱ በኋላ ወደ ስራቸው ለመመለስ ፣ ጤናቸውን ለመመለስ (መመለስ የሚቻለውን)፣ እና ሌሎች የሚገጥሟቸው ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፈተናዎች እንዳሉ ሆነው ማለት ነው።

የእስረኞቹ መፈታት እስረኛ የነበሩ ቤተሰቦቻቸውን በሞት ላጡት ምንም ነው። በህይወት ለወጡትም ቢሆን መፈታታቸው የደረሰባቸውን በደል፣ ያሳለፉትን ስቃይ፣ ያጡትን አካል … አይመልስላቸውም። የቤተሰቦቻቸውን አንግልት እና ስቃይም አይመልስም።

ታስረን ስንፈታ ፤ እስረኞች ሲፈቱ የምንደሰተው ሊመለሱ የማይችሉ በደሎችን፣ ያጣነውን ማንነታችንን እና በህይወታችን ጥሎ የሚያልፈውን አስከፊ አሻራ ችለን ነው።

LEAVE A REPLY