ወፌ ላላ (ወፌ ላይ ላዩን) /ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ/

ወፌ ላላ (ወፌ ላይ ላዩን) /ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ/

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴራችን በእኛ አገር ብርቅ የሆኑ ነገሮችን እንደሌላው አገር ተራ ነገሮች እያደረገ፥ አንዱን አጣጥመን ሳንጨርስ ሌሎቹን ሲያከታትል ሰነበተ። ይኸን ካላደረገ እያሉ የሚያደርገውን ሁሉ እንደ ትንሽ ነገር የሚያጣጥሉ፥ አድርጎት ሊያዩ ቢቸግራቸው ሊያደርግ የማይችለውን እየፈለጉ መጠየቅ ጀመሩ። አሁን ደግሞ፥ “እንዲህ ያሉ ታላላቅ ጉዳዮች በአንድ ሰው የሚወሰኑ አይደሉም” የሚሉ ተነሡ። “ለውጡ የምንፈልገውን አቅጣጫ ይዞ አልሄደም” ብለው እውነቱን እንዳይናገሩ የፈሩት ነገር አለ። በድርሰቴ ርቄ ሳልሄድ መጀመሪያ ስለ ስሙ አጻጻፍ እንነጋገር።

እኛ ኢትዮጵያውያን ቋንቋን በጽሑፍ ካዋሉ ሕዝቦች መካከል ስለሆንን፥ ያንን ክብር የምንጠብቀው እንደተማረ ሰው ስንጽፍ ነው። ለምሳሌ፥ የጠቅላይ ሚኒስቴሩንም ሆነ የሌላውን ስም የምንጽፈው አጠፋንም አለማንም፥ ሁል ጊዜ በአንድ ዓይነት መልክ መሆን አለበት። ያንን መልክ የሚወስነው ባለቤቱ ነው። ባላቤቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ስሙን የወሰነው “ዐቢይ አሕመድ” ብሎ እንደሆነ ተስፋ አለኝ። ምክንያቱም፥ “ዐቢይ” ግዕዝ ነው፤ እንደ ግዕዙ መጻፍ አለበት። “አሕመድ” ዐረብኛ ነው፤ እንደ ዐረብኛው መጻፍ አለበት– ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ።

ዜናውን የተከታተልነው እንደምናውቀው፥ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት ውስጥ ኢትዮጵያን የሚያገኑ ብዙ ሥራዎች ሠርቷል። ኢኮኖሚስቶቹ እንደሚሉት፥ የውጪ ምንዛሪ እጥረት የሥራ እንቅስቃሴዎችን አቁሟቸው ነበር። ከጎረቤት አገሮች ተወዳጅቶ ሥራው የሚያስፈልገውን ያህል እንዳገኘ ነገረን።

ከሱማሌ መንግሥት መሪዎች ጋር በመነጋገር ሱማሌን ከጠላት ወደ ወዳጅ ጎረቤትነት ለወጣት። ስንት ጥቅም ሊሰጡ የሚችሉ የባሕር ወደቦች አሏችሁ። (እንደጥንቱ) አብረን ካልተጠቀምንባቸው የሌሉ ያህል የሚቆጠሩ ናቸው ሲላቸው፥ ራእዩ እንደገባቸው ነግሮናል። ገንዘቡ ከተገኘ የወደቦች ግንባታና የመንገዶች ጠረጋ በቅርቡ ይጀመራል። በነዚህ ላይ የሆቴሎቹ ሥራ ሲጀመር ኢትዮጵያ ስፍር ቍጥር የሌላቸው ሥራ ፈቶች አገር መሆኗ ቀርቶ ሠራተኛ በደላላ የሚፈልግባት አገር ትሆናለች። ከሁሉም የገረመኝ የአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦች አንድ ሕዝብ ነን ብሎ ማንንም ሳይፈራ እውነቱን መናገሩ ነው። ቅኝ ገዢዎች እስከሚመጡብን ድረስ በዘር የተሳሰርን የአንድ አገር ሰዎች ነበርን። ትላልቆቹ የኢትዮጵያን ታሪክ ተመራማሪዎች የሚሉት፥ “ባሉት መረጃዎች መሠረት ማወቅ ያልተቻለው የኢትዮጵያን የምዕራብ ወሰን እንጂ፥ የምሥራቁ ወሰንስ ቀይ ባሕርና የህንድ ውቅያኖስ ናቸው” ነው። አንዳንዶቹ ሰነዶች የተጻፉት በኛ ሊቃውንት በግዕዝና በዐረብ ሊቃውንት በዐረብኛ ነው። ሰነዶቹ ከብዙዎቻችን እጅ አሉ።

ወያኔዎች ኢትዮጵያን እንደተቈጣጠሯት በክልል መከፋፈላቸው፥ ቅድስት ሀገራችንን ለማጥፋት ያቀዱት ሴራ ሆኖ ስላገኘነው፥ እስከዛሬ ድረስ ልባችን እንደተንጠለጠለ ነበር። እግዚአብሔር ይባርከውና፥ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴር፥ “ኢትዮጵያ ውስጥ የክልል ድምበር የሚባል ነገር የለም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የአስተዳደር ወሰን ነው” ብሎ አረጋጋን። ከዚያም፥ “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት አለው። (“Every Ethiopian citizen has the right to engage freely in economic activity and to pursue a livelihood anywhere in the national territory.”)” የሚለውን አንቀጽ 41.1. ን ጠቀሰልን። ሁላችንም ኢትዮጵያን ከዳር እስከ ዳር አገሬ ናት የምንልበትን መብት አረጋገጠልን።ክልል በሕዝቡ ላይ ችግር እንዳመጣ ተረድቶ፥ መፍትሔ ለማምጣት ችሎታና መብት ያላቸውን ሰዎች ሰብስቦ ለማነጋገር መወሰኑን ነግሮናል። ትልቅ ብሥራት ነው። ሲፈጸም ለማየት ቸኩለናል።

የአፍሪካን ፖለቲካ የሚከታተሉ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችአፍሪካ ከማንዴላ ቀጥሎ ዐቢይ አሕመድን አገኘች ሲባል ስናይ፥ “ዱሮም እኮ ኢትዮጵያ አላዋቂዎች እጅ ወድቃ ነው እንጂ፥ እኛ እኮ” ማለት ጀምረናል። ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት የሚያገኝበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ወያኔዎች ዶክተር ዐቢይ የሚያደርገውን ለማድረግ ዕድል ኖሯቸው ሳለ፥ ባለማድረጋቸው ይኸን የሚያህል ትልቅ ክብር ማስወሰዳቸው ሊያሳዝናቸው ይገባል። ለኢትዮጵያ ሕዝብ “መጣንልህ” በማለት ፈንታ “መጣንብህ” አሉት። እኛን ብቻ ሳይሆን፥ እነሆ ራሳቸውንም ጎዱ።

የዶክተር ዐቢይ መነሣት ብዙ ጀግኖች አፍርቶልናል። ዱሮ ብዙ ሰዎች ለተቃዋሚ ቡድኖች ገንዘብ አዋጡ ሲባሉ፥ ጣታችሁን እሳት ንኩበት የተባሉ ይመስል ይሸሹ ነበር፤ ትንሽ ደፈር ያሉ ደግሞ ማንነታቸው እንዳይገለጥ ከአስማሉ በኋላ በስም-አልባነት ያዋጡ ነበር። ዛሬ ግን ወያኔን ፊት ለፊት የሚራገሙ ሰዎች ድረ-ገጾቹን በእርግማን አጫንቀውታል። እንግሊዞች የደቡብ አፍሪካ ወታደሮቻቸውን ይዘው የጣሊያንን ወራሪዎች ለማጥቃት ከኬንያ ተነሥተው በደቡብ ኢትዮጵያ በኩል ዘምተው በነበረ ጊዜ የሆነው ትዝ አለኝ። ታሪኩን እንዳነበብኩት፥ ኬንያ ላይ የመለመሏቸው ኢትዮጵያውያን ጀግንነት የሚታየው እጦርነቱ ላይ ሳይሆን፥ ተሸንፎ በመሸሽ ላይ ያለውን የጠላት ጦር አሳድዶ መምታት ላይ ነበር።

ወፌ ላላ ሆይ፤ እባክሽ ይኸንን መልክት ለዶክተር ዐቢይ አድርሽልኝ፤ “እኛ የአፍሪካ ቀንድ ነዋሪዎች አንድ ሕዝብ ነን” እያልክ፥ እኛን በምታነጋግርበትም ሆነ ዐዋጅ በምታሰማን ቍጥር፥ ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝቦች መሆናችንን በአጽንዖ ታስታውሰናለህ። እባክህ የተለያየን የሚያስመስሉ ምልክቶችን አጕልቶ ማስታወስክን ትተህ አንድ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆናችንን አጽናልን። “ጎሳዎችና ነገዶች ተረሳን” ይላሉ ብለህ ሰገተህ ከሆነ፥ ሕገ መንግሥቱ ከሁሉ አስቀድሞ እመግቢያው ላይ ኢትዮጵያ የብሔሮች፡ ብሔረሰቦች፡ ሕዝቦች አገር መሆኗን በይፋ ዐውጇል። ለነገዶች ዕውቅና ለመስጠት ከሆነ፥ ይህ ዐዋጅ ይበቃናል። በነጋ በጠባ ቍጥር በጎሳ፥ በነገድ የተለያያችሁ መሆናችሁን አትርሱ አትበለን። አንዳንድ ጊዜ፥ “የኢትዮጵያ ሕዝብ” ብለህ ስትጠራን፥ ማናቸውም ጎሳ ፥ “በዚህ አጠራር እኔ ተረሳሁ” ሲል አልተሰማም። ቀጥልበት። እኛ ፖለቲካ ስንተች፥ ሊለያዩን ለሚችሉ ለጎሳና ለሃይማኖት ዋጋ ላለመስጠት እንፈልጋለን። ሃይማኖትና ጎሳ የግል ናቸው።

ነገዶችና ጎሳዎች ለኢትዮጵያ ለአንድ ሰው እንደ ዓይን፥ እንደ ጆሮ፥ እንደ እጅ እንደ እግር ማለት ናቸው። ታዲያ አንድን ሰው ለማነጋገር ስንፈልግ፥ እንደ መልክ ጸሎት፥ “አንተ ባለ ዓይን፥ ባለ ጆሮ፥ ባለ እጅ፥ ባለ እግር፥ ባለ ወዘተ. ሰውየ ሆይ፥ እንደምን አደርክ?” አንለውም። ስሙን ብቻ ነው የምንጠራው። እሱም ስሙን ብቻ መጥራታችንን እያወቀ፥ ዓይኑን፥ ጆሮውን፥ እጁን፥ እግሩን፥ ወዘተውን ጨምረን ያናገርነው መሆኑ ገብቶት፥ “ዛሃር ምስጌን” ይላል።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር፥ ልትነግረን የምትፈልገውን፥ “ውድ የሀገሬ ልጆች ኢትዮጵያውያን ሆይ” ብለህ ጀምረው። ይኸንን ካንተ ቀጥሎ የሚመጣ መሪ ብሎት፥ አስተዋፅኦህን ሁሉ እንዳያሳንስብህ ዕድልህን ተጠቀምበት።

LEAVE A REPLY