/Ethiopia Nege News/:- ዶ/ር አብይ በቤተመንግሥት የተፈጠረውን ድንገተኛ የወታደሮች ጉብኝት አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል። እንደጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ ዛሬ ቤተመንግሥት አካባቢ የነበረው ግርግርና ወከባ ቡራዩ አካባቢ የተፈጠረውን ችግር ለማረጋጋት በሃላፊነት ላይ የነበሩ ወታደሮች ግዳጃቸውን ፈጽመው ወደመደበኛ ቦታቸው ሲመለሱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤቱታቸውን ለመስማት የመጡ መሆናቸው ተመልክቷል።
240 የሚሆኑ ወታደሮች ከነ ሙሉ ትጥቃቸው ቤተመንግሥት በመግባት ለመነጋገር እና የሚወዱት መሪያቸው መሆኑን በመግለጽ ለዶ/ር አብይ ችግራቸውን ለማስረዳት እንደሚፈልጉ ቢገልጹም የቤተመንግስት አሰራር ከነትጥቃቸው መግባት እንደማይፈቅድ ተገልጾላቸው በቤተመንግሥት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል።
የወታደሮቹን ሁኔታ ለማጣራት አካባቢው በሙሉ በፍተሻ ላይ እንደነበርና ለበርካታ ሰዓታት የተለያዩ መላምቶች ሲሰጡ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን ዛሬ አመሻሽ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቀጥታ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በእኔ እንዲደመጡ የፈለጉ የጦር አባላት ቤተመንግሥት መጥተዋል። ሁኔታዎች ተመቻችቶላቸው ከወታደሮቹ ጋር የሚያስማማና ጠቃሚ ውይይት አድርገናል፤ ያለባቸውን ችግርም በመረጃ ሰጥተውኛል ሲሉ ተደምጠዋል።
በማያያዝም እንዲህ አይነት ነገር ሲከሰት ህዝብ የተጣራ መረጃ እስኪያገኝ እንዲጠባበቅ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ህዝቡ ተጨባጭ መረጃዎችን እስኪያገኝ ችግር እንዳለ ግጭት እንዳለ በማስመሰል ሊያባሉን የተዘገጁ ሃይላት አሉ በማለት ህዝብ ከነዚህ ከሚያደናግሩ ሁኔታዎች ራሱን እንዲጠብቅ ምክር ሰጥተዋል።
ሁኔታውን በሚመለከት ለኢትዮጵያ ነገ ድረገጽ የፖለቲካ ምልክታቸውን በማካፈል የሚታወቁ ተንታኝ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ህዝብን ከማረጋጋት ረገድ እጅግ ጥቃሚ እንደነበር ገልፀው ህዝብ ከእንዲህ አይነት አወዛጋቢ ሁኔታ ነጻ ሊሆን የሚችለው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዳሉት የተጣራ መረጃ በመጠበቅ ሳይሆን መንግስት በወቅቱ በሚሰጠው ፈጣን ምላሽ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አያይዘውም በቤተመንግሥት አካባቢ ጦር ታዬ፣ በአካባቢው ያሉ መስሪያቤቶች ተዘግተው ሰራተኞች ከየ ህንጻው ወጡ፣ በቤተመንግሥት አካባቢ ፍተሻ አለ፣ ኢንተርኔት ጠፋ… የሚሉ የሚያደናግሩ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ስጋትን የሚፈጥሩ እውነታዎች ባሉበት ሁኔታ መንግስት በአፋጣኝ ምላሽ መስጠት ሲገባው ለሰአታት እና ሙሉ ቀን እየዘገየ ምላሽ እየሰጠ በሶሻል ሚዲያው ማላከክ አግባብ አይደለም ብለዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን መሳሪያ ቤትም ሆኑ የፖሊስ አካላት ሁኔታውን አስከትለው በጊዜው ለህዝብ ይፋ ማድረግ ይገባቸዋል። ይህ የህዝብ የማወቅ መብት ብቻ ሳይሆን የአገር ደህንነት ዋነኛ ጉዳይ ተደርጎ መታየት አለበት። የኦነግ ትጥቅ አለመፍታት፣ አሮጌዎቹ በመባል የሚታወቁት የህወሀት ባለስልጣናት ሁኔታና ሌሎች ያልተፈቱ ጥያቄዎች ባለበት ሀገር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፈጣን የመረጃ ፍሰትን ትኩረት ሊሰጡ ይገባል። በተለይ አሁን አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ እርምት ሊደረግበት ይገባል ብለዋል።
ጦሩን ይዘው ውደ ቤተመንግሥት የመጡ ሃላፊዎችም ከማስጠንቀቂያ እስከ መባረር የሚደርሱ ቅጣቶች ሊሰጣቸው እንደሚገባ የገለጹት እኝሁ የፖለቲካ ተነታኝ ጦር ሰራዊቱ እየተነሳ በየአቅጣጫው የሚጓዙበት አግባብ እርምት ሊወሰድበት የሚገባው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን አስምረውበታል።

























