16 ኩንታል የኢትዮጵያ ብር በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ

16 ኩንታል የኢትዮጵያ ብር በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/:- በምዕራብ ሀረርጌ አሰቦት ከተማ 16 ኩንታል የኢትዮጵያ ብር በቁጥጥር ስር መዋሉን የመኢሶ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮን በመጥቀስ ምንጮች ገለፁ። በቶዮታ ላንድ ክሩዘር መኪና ታጭቆ ወዴት እንደሚጓጓዝ ለጊዜው ያልታወቀ በ16 ጆንያዎች የተሞላ ገንዘብ በነዋሪዎች ጥቆማና ክትትል ሊያዝ መቻሉ ታውቋል።

በተለያዩ ጊዜያት በርከት ያሉ ገንዘቦች በየቦታው በቁጥጥር ስር ቢውሉም ለምን እና በማን እንደሚንቀሳቀሱ ከመላምት ባለፈ በውል የታወቀ ነገር የለም። መንግስትም በጉዳዩ ዝምታን መምረጡ እና በጉዳዩ ቁርጠኛ አቋም አለመያዙ ግራ እንዳጋባቸው ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ቅሬታቸውን እያስተጋቡ ነው፤ ማብራሪያ እንዲሠጥም መንግስትን እየወተወቱ ይገኛሉ።

በተመሣሣይም ከአዲስአበባ ወደ ድሬደዋ በመጓዝ ላይ ባለ የመንግስት ታርጋ የለጠፈ ቶዮታ ፒክ አፕ መኪና በሁለት የተሠረቁ አስከሬኖች ውስጥ በርካታ ገንዘብ በማሸሽ ላይ ያሉ ግለሠቦች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ምንጮች ከሂርና ጠቁመዋል። ግለሰቦቹ ሲያዙ በአስከሬኖቹ ሆድ ዕቃ ከተደበቀው በተጨማሪ በእጃቸው 160 000 ብር ተገኝቷል ተብሏል።

በሁለቱም ጉዳዮች ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሠዓት ድረስ በመንግስት በኩል ምንም አይነት መረጃ ይፋ አልተደረገም።

LEAVE A REPLY