የሚሞካሽ እና የማይወቀስ የአደባባይ ሰው ሊኖር አይችልም! |

የሚሞካሽ እና የማይወቀስ የአደባባይ ሰው ሊኖር አይችልም! |

በህዝብ እና በአገር ጉዳይ በአንድ ወይ በሌላ መልኩ እጁን የከተተ ሰው ለወቀሳ፣ ለትችት፣ ለነቀፌታ፣ ለተጠያቂነት፤ እንዲሁም ለሙገሳ እና ውደሳ ከማንም በላይ ተጋላጭ ነው። አደባባይ እና ከፍ ያለ ማማ ላይ ቆሞ አትዩኝ ማለት አይቻልም። በአገር እና በሕዝብ ጉዳይ ውስጥ እጅን አስገብቶ እያቦኩ እና እየፈተፈቱ አትጠይቁኝ፣ አትተቹኝ አይባልም። ተጠያቂነትን፣ ትችትን፣ ወቀሳን እና መብጠልጠልን የሚፈራ ወይም አጥብቆ የሚሸሽ ሰው በሕዝብ እና በአገር ጉዳይ ውስጥ እራሱን አስገብቶ ያሻውን ሊያደርግ አይችልም።

የአደባባይ ሰዎች (public figures) ሆደ ሰፊ እና ደንዳና ቆዳ ያለቸው ናቸው። በሕዝብ እና በአገር ጉዳይ ውስጥ እጃቸውን በሰነዘሩት እና ጠልቀው በገቡበት ልክ ተጋላጭነታቸውም የዛኑ ያህል ይጨምራል። እቤቱ አርፎ የተቀመጠን ሰው ወይም ከሕዝብ እና ከአገር ጉዳዮች በብዙ ማይልሶች እራሱን አሽሽቶና በግል ኑሮው ብቻ ታጥሮ የሚኖር ሰው ማንስ ያየዋል፣ ማንስ ይነካዋል፤ መፈጠሩንስ ከወዳጅ ዘመዱ በቀር ማን ያውቃል።

የአደባባይ ሰዎች ባለስልጣናት፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኖች፣ ጋዜጠኞች፣ የመብት ተሟጋቾች፣ ተመራማሪዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ እስፖርተኞች እና ሌሎች በሙያቸው ታዋቂ የሆኑ ሰዎችን ሁሉ ያቅፋል። እነዚህ ሰዎች በተሰማሩበት የሙያ ዘርፍም ሆነ የሕዝብ እና አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ባላቸው ተሳትፎ ከሌሎች ልቀው ተገኝተው ወይም ሁኔታዎች ገፍተዋቸው ወይም እድል ተፈጥሮላቸው እራሳቸውን ከፍ ያለ ማማ ላይ ያስቀመጡ ሰዎች ናቸው። በመሆኑም ከየትኛውም አቅጣጫ እና እርቀት ባለ ሰው አይን ውስጥ በቀላሉ ይገባሉ።

በብዙዎች አዕምሮ ውስጥ ይሳላሉ። በተግባራቸው መጠን ወይም ከዚያ በላይ ስማቸው ይገናል። ተንደርድረው የወጡበት ማማ ተጋላጭነታቸውንም እጅግ ከፍ ያደርገዋል፤ ይጨምረዋል። ከፍ ባሉ ቁጥር ከፍ ያለ ተጠያቂነት እና ተጋላጭነት ይጠብቃቸዋል። ከዚያ በኋላ ደብቁኝ፣ አትውቀሱኝ፣ ማንም አይድረስብኝ ማለት አይችሉም። አንዳንዴም ተጋላጭነታቸው ከሕዝብ እና ከአገር ጉዳይ አልፎም እስከ ግል ሕይወታቸው ሁሉ ሊዘልቅ ይችላል። በሕዝብ ዘንድ ከፍ ከፍ ብለው በታዩ ቁጥር የግል ሕይወት ጉዳይ (privacy) እየሳሳ ይመጣል።

የአደባባይ ሰዎችን በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን። የመጀመሪያው የግል ተሰጧቸውን፣ ህልማቸውን እና የሙያ ብቃታቸውን ለማሳካት ሲሉ ሌት ተቀን የሚተጉ ሰዎች በሙያ ስኬት ወይም በተሰማሩበት ዘርፍ በሚያሳዩት እጅግ የላቀ (extraordinary) ጥረት አንቱታን የተቀዳጁ ዝነኛ፣ ታዋቂ እና ስመ ጥር ሰዎችን በአንድ ማዕቀፍ ልናይ እንችላለን። በዚህ ውስጥ በኪነ ጥበብ፣ በእስፖርት፣ በንግድ እና በሌሎች የሙያ ዘርፎች የስኬት ቁንጮ የሆኑ ሰዎችን መጥቀስ ይቻላል።

በአገራችን ከዘፋኝ ጥላሁን ገሰሰን እና አስቴር አወቀን፣ ከሯጭ ኃይሌን እና ደራርቱን፣ ከንግድ አልአሙዲንን፣ ከጻህፍት ሎሬት ጸጋዮን፣ ከምሁር ፕ/ር መስፍንን፣ ከጋዜጠኛ መዓዛ ብሩን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። በእዚህ መደብ ውስጥ የሚገኙት የአደባባይ ሰዎች በሙያ ብቃታቸው ወይም በተሰማሩበት ዘርፍ ልቀውና ግንባር ቀደም በመሆን ከማንም በላይ ጎልተው የሚታዩ ናቸው። ለሙገሳም ሆነ ለወቀሳ ከማንም በላይ ተጋላጭ ናቸው። እያንዳንዱ እርምጃቸውም ሆነ ከአፋቸው ጠብ የምትል ነገር ሁሉ ጎልታ በብዙዎች ዘንድ ትታያለች። አንዳንዴ ባልዋሉበትም ስማቸው ደምቆ ይታያል። ይጥረቱ እና የስኬታቸው ባለቤቶች እራሳቸው ስለሆኑ የተጠያቂነት ደረጃቸውም በግለሰው ደረጃ ብቻ የሚወሰን ነው።

በሁለተኛው ምድብ ውስጥ የሚገኙት የአደባባይ ሰዎች የመንግስት ተሿሚዎች፣ ባለሥልጣናት፣ ፖለቲከኞች እና የማህበረሰብ ተቋማት መሪዎች ናቸው። የእነዚህ ሰዎች ከፍታም ሆነ በሕዝብ እና በአገር ጉዳይ ያላቸው ጣልቃ ገብነት እና የተጋላጭነት ምንጩ ከተቀመጡበት ኃላፊነት ጋር የተቆራኘ ነው። በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ያሉት ሰዎች የከፍታቸው መጠን የሚለካው በሙያ ብቃታቸው ልቀት ብቻ ሳይሆን በሕግ እና በሕዝብ በተሰጣቸው የኃላፊነት ደረጃ መጠን ነው። ስኬታቸውም ሆነ ውድቀታቸው ከላይ ከተጠቀሱት ሰዎች በተለየ መልኩ በሕዝብ እና በአገር ጥቅም ላይ ቀጥተኛ የሆነ ተጽዕኖ ስላለው በተጓዳኝ የሕግ ተጠያቂነትንም አብሮ ይዟል።

አንድ በሕዝብ ዘንድ ታዋቂና ተወዳጅ የሆነ ዘፋኝ መስመር ቢስት እና አስነዋሪ ነገር ቢፈጽም ጉዳዩ በሕግ የሚያስጠይቅ እስካልሆነ ድረስ ኪሳራው የራሱ ብቻ ነው። ወደ ከፍታው በወጣበት መንገድ ተመልሶ ቁልቁል ተንደርድሮ ይወርዳል። የሱ ክሽፈት የራሱ ብቻ ይሆናል እንጂ አገር እና ሕዝብ አብሮት አይረክስም። በተቃራኒው አገርን በመምራት ወይም በህዝብ ተቋማት መሪነት ግንባር ቀደም የሆነ ሰው መስመር ሲስት እና ቁልቁል ሲወርድ በሕዝብ የተሰጠውን ኃላፊነት እና አመኔታ አብሮ ይዞ ስለሆነ ወደ ገደል የሚንደረደረው ሕዝብ እና አገርም አብሮ ይጎዳል። ስለዚህም የፖለቲካና የሕዝብ መሪዎች ኪሳራም ሆነ ትርፍ የሕዝብና የአገር ስለሆነ ከወቀሳ እና ነቀፌታ ባለፈ የሕግ ተጠያቂነትም አለበት። በሳቱትና ቁልቁል በወረዱት ልክ በሕግ ይጠየቃሉ። ባለሙት እና ከፍ ባሉትም ልክ በሕዝብ ዘንድ ይወደሳሉ፣ ይከበራሉ።

ጠንካራና ነጻ የመገናኛ ብዙሃን ባሉበት እና የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ባህል በዳበረበት አገር የየቀኑን የዜና እና የዘገባ ሽፋን ከግማሽ በላይ የሚይዘው የእነዚህ የአደባባይ ሰዎች ውሎና አዳር ነው። የእነሱ ጉዳይ የአገር ጉዳይ፣ የአገር ጉዳይ የእነሱ ጉዳይ ይሆናል። እነዚህ በቁጥር እጅግ አነስተኛ የሆኑ የማህበረሰብ አካላት የአገር እና የሕዝብ ጉዳይ ማጠንጠኛ ማዕከሎች ይሆናሉ። የሕዝቡንም የአስተሳሰብ እና የውይይት አቅጣጫ ይመራሉ። በቅርቡ ከአዲስ አበባ ከንቲባ ታከለ ዑማ ጋር ተያይዞ ይነስቅ የነበረው እሰጣ ገባ መነሻው ይሄው ነው።

የዚህ ጽሁፍ ዋና አላማ በእነዚህ የአደባባይ ሰዎች ዙሪያ ድጋፍ በመስጠት ለተሰባሰቡ ሰዎች አጭር መልዕክት ለማስተላለፍ ነው። በሕዝብ አደባባይ ከፍታ ላይ የቆሙ እና በስኬታቸው የተደመምንባቸው ሰዎች ሲተቹ እና ሲወቀሱ ለምን ተነኩ እያላቸው እቧ ከረዮ የምትሉ ሰዎች ውዳሴ እና ነቀፌታ፣ ሙገሳና እርግማን፣ ሹመትና ሽረት፣ አድናቆት እና ተጠያቂነት የአንድ ሳንትም ሁለት ገጽታዎች የመሆናቸውን እውነታ የሳታችሁት ይመስለኛል። በበጎ ሥራው የሚደነቅ እና የሚሞካሽ ሰው በስንፍናው፣ በመጥፎ አድራጎቱና በጥፋቱ ተወቃሽ እና ተጠያቂ ነው። ማንም ሰው በደህና ጊዜ የሰራቸው መልካም ነገሮች ለዘላለም ያለመወቀስ ከለላን አያጎናጽፉትም። የወደድነው ሰም መጥፎ ቢሰራም መወቀስ የለበትም የሚል የጅል አስተሳሰብ የዲሞክራሲ ባህልን እና ተጠያቂነትን ያቀጭⶻል፤ ያከስማልም። የምንወደው ሰም ለምን ተወቀሰ ከማለት የተወቀሰበትን ምክንያት በአግባቡ መመርመር መቅደም አለበት። ጭፍን ድጋፍ እራስን ብቻ ሳይሆን የምንደግፈውንም ሰው ይዞ ገደል ይገባል።

በቅርቡ በአቶ ታከሉ ዑማ ላይ ትሽት እና ነቀፌታ በሰነዘረው አክቲቪስት ስዩም ተሾመ #Seyoum Teshome ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ የሰነዘራችው የከንቲባው አፍቃሪዎች እና ደጋፊዎች ከእንዲህ ያለ አስነዋሪ ስህተታችው ትምህርት ትወስዳላችው ብዮ ተስፋ አደርጋለሁ። በተመሳሳይ ዶ/ር አብይ ባለፈው ሳምንት በምክር ቤት ያቀረቡትን ንግግር በጨረፍታ የምትተች አጭር ጽሑፍ መጻፌን ተከትሎ የስድብ ናዳ ያወረዳችሁብኝ ሰዎችም የሙገሳ እና የተጠያቂነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዊ ባህሪ ያልገባችው ሰዎች ትመስሉኛላችሁ እና እሲት ለራሳችው እድል ስጡና ወደውስጣቸ ተመልከቱ። የምንወደውን ሰው የምንደግፈው ሲያለማም ሲያጠፋም ‘ከአንተ ወዲያ ወደ ኋላ’ እያልን እየዘፈንን አይደለም። በመረጃ እና በማስረጃ ተደግፈን ስህተቶቻቸውንም ነቅሰን እያወጣንና እያሳየን ተጠያቂዎች ማደረግ ስንችል ብቻ ነው።

በቸር እንሰንብት!

LEAVE A REPLY