የጅጅጋ ፖለቲካ | በመስከረም አበራ

የጅጅጋ ፖለቲካ | በመስከረም አበራ

ለሃያ ሰባት አመት የኖረው ኋላቀር ፖለቲካችን የሃገራችንን ክልሎች ሁሉ ሲያንገላታ የኖረ ቢሆንም የሱማሌ ክልል ደግሞ ከሚብሱት በባሰ ችግር ውስጥ የቆየ፣በሁለት ሶስት ለበቅ ሲገረፍ የኖረ ክልል ነው፡፡ የዚህ ክልል ህዝብ ከሌላው ህዝብ በተለየ መከራው እንዲብስ ያደረገው በሁለት በኩል እሳት የሚነድበት መሆኑ ነው፡፡በአንድ በኩል የመለስ ዜናዊ ምልምል የሆነው አብዲ ኢሌ “ኦብነግን ትደግፋላችሁ” እያለ ህዝቡን ወደ እስር ቤት አጉሮ ሊያልፉበት ቀርቶ ሊያደምጡት  በሚያስቸግር መከራ ውስጥ ይዶላል፡፡በስሙ ጦስ ህዝብ በአብዲ ኢሌ ለበቅ የሚገረፍለት ኦብነግ በበኩሉ አብዲ ኢሌን ፈርተው ይሁን አላማውን ተቃውመው ያልተባበሩትን የክልሉ ነዋሪዎች “አብዲ/የመለስ መንግስት ደጋፊዎች ናችሁ” እያለ ያንገላታል፡፡በዚህ ላይ ክልሉ እምብዛም ያልለማ ከመሆኑ በላይ ያለው የፀጥታ ችግር ተደምሮ ህዝቡ በሶስተኛው ለበቅ(በኢኮኖሚ ችግር) እንዲገረፍ አድርጓል፡፡

የአብዲ ኢሌ አረመኔነት በህዝቡ ላይ ያደረስ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እኛን የሃገራቸውን ሰዎች ቀርቶ ምዕራባዊንን ያሳሰበ ነበር፡፡በስተመጨረሻው እንደውም አሜሪካ አብዲ ኢሌን ከተፈላጊ ወንጀለኞች አንዱ አድርጋ ታድነው ሁሉ ነበር፡፡የህወሃት/ኢህአዴግን ገመና ለመክተት ተብሎ የተቋቋው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዓለምን ጉድ ያስባለ እርኩሰት ወደሚሰራበት ወደ ሶማሌ ክልል ትውር ብሎ አያውቅም፡፡ቱሪስትም መናኝም መስለው ገብተው በክቡሩ የሰው ልጅ ላይ አብዲ ኢሌ እና መለስ ዜናዊ ይሰሩት የነበረውን ግፍ የሚያጋልጡት ባዕዳኑ ምዕራባዊን ነበሩ፡፡የመልቲው አዲሱ ገብረእግዚአብሄር መስሪያቤት  በፈረንጆቹ  ስለ ጉዳዩ ሲጠየቅ “ወደዛ ክልል ሄጄ አላውቅም” ሲል በምቾት ነበር፡፡

ታዛቢ በሌለበት ተከድኖበት ሲንተከተክ የኖረው የሶማሌ ህዝብ አምላክ በቃህ ብሎት አብዲ ኢሌ የተባለው ሰውየ ከትከሻው ተነስቷል፡፡አብዲ ሲነሳ የተተኩት አቶ ሙስጠፋ ኡመር ደግሞ ለበደሉ በካሳነት የተቀመጡ የሚመስሉ ሰው ናቸው፡፡ አቶ ሙስጠፋ ጥሩ በሚከፍሉ ዓለም ዓቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ተቀጥረው ባህርማዶ የሚኖሩ ሰው ነበሩ፡፡የተመቼ ኑሯቸውን ጥለው በአመፅ ስትታመስ የኖረችውን የሱማሌን ክልል ለማቅናት በጄ ማለታቸው ያስመሰግናቸዋል፡፡የተረከቡትን ሃላፊነት በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚገርም ቅንጅት አመርቂ በሆነ ሁኔታ ለመወጣት እያደረጉት ያለው ጥረት እጅግ ያስመሰግናቸዋል፤በብዙዎች ዘንድም ተወዳጅነትን አትርፈውበታል፡፡

አቶ ሙስጠፋ በኢህአዴግ ፖለቲካ ውስጥ የኖሩ ሰው አይደሉም፣ክልሉን የሚመራው ሶህዴፓ አባልም አይደሉም፡፡ይልቅስ የእርስ በርስ ጦርነት ወደ ፍርስራሽነት የቀየራቸውን የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራትን ህዝቦች በረድኤት ለመታደግ በሚሰሩ የረድኤት ድርጅቶች ውስጥ ሲሰሩ የኖሩ የተግባር ሰው ናቸው፡፡በስራቸው ምክንያት የእነዚህን ሃገራት አሳዛኝ እጣፋንታ ያዩት አቶ ሙስጠፋ ኢትዮጵያም እንደ ሃገር እስካልቆመች ድረስ የሶሪያ እና የየመን እጣ እንደሚጠብቃት ተረድተው ይህ እንዳይከሰት ለመስራት እንደሚፈልጉ ለአውስትራሊያው SBS ሬዲዮ በሰጡት ቃለ መልልስ ገልፀዋል፡፡

ሙስጠፋ የኢህአዴግ ካድሬነት ታሪክ ስለሌላቸው የሰሩትን የመዘከሩ የፕሮፖጋንዳ ጥማት አይፈትናቸውም፣በክልሉ ያለውን የፖለቲካ ችግር መጠኑን በሚወክል ሁኔታ ተረድተው በአፋጣኝነቱ መጠን ይሰራሉ እንጅ እንደ ሌሎቹ የክልል ባስልጣናት በችግሩ ዙሪያ አይዞሩም፡፡ስልጣን ላይ ከተቀመጡ ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ክልሉ ያልለመደውን የሰላም አየር እንዲስብ አድርገዋል፡፡የዘር ፖለቲካ ሃገሪቱንም ሆነ ሱማሌ ክልልን እንደማይጠቅም በግልፅ የተናገሩ የመጀመሪያው የሃገራችን ባለስልጣን ሙስጠፋ ኡመር ናቸው፡፡ቋንቋ መግባቢያ እንጅ ማግለያ እንዳልሆነ ለማስመስከር ዘር ሳይቆጠር ሶማሊኛ የሚናገር ኢትዮጵያዊ ሁሉ በሱማሌ ክልሉ እንዲያገለግል አድርገዋል፡፡በአብዲ ኢሌ የመጨረሻ የስልጣን ቀናት የክልሉ ነዋሪዎች ዘር፣ሃይማኖት ቆጥረው የተጋደሉ ለማስመሰል የተደረገውን ክፉ ስራ ለማርከስ የክልሉ ተወላጆች ባያጠፉ እንኳን “ጥፋቱ የተደረገው በእኛው ስም ስለሆነ ወንድሞቻችንን ይቅርታ መጠየቅ፣የጠፋባቸውን ንብረት ምትክ እንዲያገኙ ማድረግ፣በስነ-ልቦና በማፅናናት ወገንተኝነታችንን ማሳየት  አለብን” የሚል በጎ አካሄድ እንዲፈጠር የሙስጠፋ አመራር ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡

በጎሳ ተሸንሽኖ ለመባላት አንድ ሃሙስ ቀርቶት የነበረውን የሶማሌ ክልል በጎሳዎች መካከል ያለውን ፍጥጫ ሳይቀንሱ ስለሱማሌ ክልልም ሆነ ስለኢትዮጵያዊነት ማውራት አይቻልም በሚል እሳቤ በጎሳዎች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር የሃገሩን ባህላዊ የእርቅ መንገድ ተጠቅሞ በጣም ባጭር ጊዜ አመርቂ ስራ ሰርቷል-አቶ ሙስጠፋ፡፡ከክልሉ መጠሪያ ጀምሮ እስከ ባንዲራው ድረስ በህዝቡ ዘንድ የነበረውን ቅሬታ አዳምጦ ህዝብ በሚፈልገው መንገድ መፍትሄ ሰጥቷል፡፡አቶ ሙስጠፋ እንዲህ ባለው ብቁ አመራሩ በበኩሌ እጅግ ያሰጋኝ የነበረውን የሶማሌ ክልል ፀጥታ አረጋግቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ በትርምስ ይታወቅ የነበረውን ክልል በአሁኑ ወቅት ምናልባትም ከሌሎች ክልሎች በተሻለ ሰላም ላይ የሚገኝ ክልል አድርጎታል፡፡ሃገራችን እንዲህ ያሉ ወደ ስራው ያመዘኑ፣ ስራቸው ራሱ አፍ አውጥቶ የሚያወራላቸው እንጅ የፕሮፖጋንዳ አጀብ የማይጠሩ ሰዎች ያስፈልጓታል፡፡

የአቶ ሙስጠፋ አስተዳደር በሱማሌ ክልል ሰላም አና መረጋጋት ላይ ላስመዘገቡት ስኬት የኦብነግ ድርሻም ላቅ ያለ ነው፡፡ኦብነግ በትጥቅ ትግል የህወሃት/ኢህአዴግን የግፍ አገዛዝ ከመንበሩ ለማውረድ ከሚታገሉ ብረት አንጋች ታጋዮች መካከል በአቶ መለስ በጥብቅ ይፈራ የነበረው ነው፡፡አቶ መለስ ኦብነግን ላቅ አድርገው ይፈሩት እንደነበር የክልሉን  ልዩ ሃይል ለማቋቋም ያፈሰሱት በጀት፣በኦብነግ አጋርነት  በተጠረጠሩ ሰዎችላይ ይፈፀም የነበረው ለየት ጭካኔ፣አብዲ ኢሌን ይዘውበት የነበረው የወዳጅነት ትስስር ጥብቀት  ማስረጃ ነው፡፡በተጨማሪም ኦብነግን ወደ ሌላ ፍጥረት በሚጠጋ አረመኔነት እና ሰላም ያለመፈለግ አመፀኝነት የመፈረጁ የፕሮፖጋንዳ ናዳ ኦነግን በጥብቅ ከመፍራት የመጣ ነገር ነው፡፡

በህወሃት/ኢህአዴግ በኦብነግ ላይ በተነዛው ፕሮፖጋንዳ ሳቢያ ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ሲመጡ መደመር ለሚለው ፍልስፍናቸው ትልቅ ፈተና ሊጋርጥ የሚችለው ኦብነግ ሊሆን ይችላል የሚል ፍርሃት ነበር፡፡የሆነው ግን ሌላ ነው፡፡ምናልባትም ኦብነግ ከአብዛኛዎቹ የኦዴፓ አመራሮች በተሻለ የዶ/ር አብይ የመደመር ፍልስፍና አጋር ሳይሆን አልቀረም፡፡ጭራሽ የአቶ ሙስጠፋን መንግስት ለመበጥበጥ በአቶ አህመድ ሽዴ እየተመራ ያለውን የሶህዴፓ እና የኦዴፓ ጥቂት አመራቶች ቡድን አደብ እንዲገዙ፣በክልሉ ሰላም ላይ ያነጣጠረ እኩይ ስራቸውን እንዲያቆሙ  እያስጠነቀቀ ያለው ኦብነግ መሆኑ የሃገራችን ፖለቲካ እንዴት ባለ የግልምቢት ዘመን ላይ እንዳለ ወለል አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡

የአቶ መለስ ዘመን ኢህአዴግ የቀኝ እጅ የነበሩት አቶ አህመድ ሽዴ የአቶ ሙስጠፋ አስተዳደር ላይ ታች ብሎ ፈር ያስያዘውን የሶማሌ ክልል ሰላም ለማደፍረስ፣የአቶ አብዲ ኢሌን ዘመን አስተዳደር ትንሳኤ ለማምጣጥ እየሰሩ እንደሆነ የክልሉ የህግ እና ሰብዓዊ መብት አማካሪ የሆኑት አቶ ጀማል ድርየ ቀጥ ባለ ግልፅ ቋንቋ ለኢሳት ተናግረዋል፡፡ይህ ግልፅነት ፌደራል መንግስቱን ጨምሮ ሌሎችም የክልል አስተዳደሮች ሊከተሉት የሚገባ አካሄድ ነው፡፡የኢህአዴግ ባለስልጣናት እንደ ብልህነት የሚያዩት የበዛ ማስመሰል እና መሸነጋገል ለተገዳዳሪ የመፈርጠሚያ ጊዜ ይሰጥ ይሆናል፣የችግሩንም ጥልቀት ይጨምር ይሆናል እንጅ የትም አያደርስም፡፡ይህ የተገለፀላቸው የሱማሌ ክልል ባለስልጣናት የአረመኔውን አብዲ ኢሌን አገዛዝ ትንሳኤ ለማምጣት ላይ ታች የሚሉ የሶህዴፓ ሹማምንትን (በዋናነት አቶ አህመድ ሽዴን) በስም ጠቅሰው፣ከድሮ እስከ ዘንድሮ ቅንጣት ያህል የህዝብ ወገንተኝነት የሌላቸው ስልጣን እና ጥቅም አምላኪ ተላላኪዎች እንደሆኑ  አቶ ጀማል ድርየ አስረግጠው ለኢሳት ተናግረዋል፡፡

ዛሬ ለምን ሰላም ወረደ ብለው በጥባጭ የሆኑት አቶ አህመድ ሽዴ አመት ካልሞላ ጊዜ በፊት ኦብነግን በበጥባጭነት ሲከሱ የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ዛሬ ደግሞ ሸሽተው ቱርክ ኢስታምቡል ከገቡ የአብዲ ኢሌ ግብራበሮች ጋር ግንባር በመፍጠር ክልሉን ለማረጋጋት ደፋ ቀና የሚሉ ሰዎችን ለማደናቀፍ እየሰሩ ነው፡፡አሁን የማን ምንነት አየለየ ነው፡፡አሁን በሹመት ላይ ሆነውም በመከራ የተረጋጋውን ክልል ለማመስ እየሞከሩ ያሉት አቶ አህመድ ሽዴ ድሮም አሁንም የሶማሌ ክልል ሰላም እና የህዝቡ እጣ ፋንታ የሚያስጨንቃቸው ሰው እንዳልነበሩ ነው ከሰሞኑ ስራቸው መገንዘብ የሚቻለው፡፡በአንፃሩ ትናንት በአመፀኝነት ሲከሱት የነበረው አብነግ ሳይሾም ሳይሸለም፣አመራሮቼ በክልሉ አስተዳደር ላይ ይሾሙልኝ ሳይል ለህዝብ ሰላም ስለሆነ ብቻ በቂ ነው ብሎ አደብ ገዝቶ መቀመጡ ሳያንስ እነሱኑ እንዲታገሱ እየመከረ ነው፡፡አልፎ ተርፎም በሃገራችን የዘር ፖለቲካ አብቅቶ የዲሞክራሲ ዘመን እንዲመጣ ለመስራት ስለሚፈልግ ለዚሁ እንዲመቸው ራሱን ወደ ህብረብሄራዊ ፓርቲነት ሊቀይር እንደሆነ በይፋ ተናግሯል፡፡ይህ ያልገረመው አይገኘም መቼም!

የኦብነግ ጨዋነት ትናንት ትጥቅ ያስነሳው በህዝብ ላይ ሲደረግ የነበረው ግፍ ብቻ እንደሆነ አስመስካሪ ነው፡፡ይህ የኦብነግ ብስለት የተሞላበት ፖለቲካዊ ጨዋነት  ለሶማሌ ክልልም ሆነ ለሃገራችን መረጋጋት እጅግ አስፈላጊ ግብዓት ነው፡፡በአራቱም ማዕዘን በሰላም ውላ በማታድረው ሃገራችን ፖለቲካዊ ትኩሳት ላይ ኦብነግም እንደ ኦነግ ለጠብም ለፍቅርም የማይመች ቢሆን ኖሮ ፈተናችን ይከብድ ነበር፡፡አብዲ ኢሌን ሲወጋ የነበረው ኦብነግ አቶ ሙስጠፋንም ለመውጋት አልተነሳም፤ በአንፃሩ ብዙ አመት ታገልኩ የሚለው ኦነግ አቶ አባዱላን/አቶ ሙክታርን ለመውጋት አልሆንልህ ባለው ጦሩ አቶ ለማ መገርሳን የመሰሉ ሰው ሊወጋ ይገለገላል፡፡

የኦብነግ የአዋቂ እርምጃ፣የአቶ ሙስጠፋ ድንቅ አመራር ከሱማሌ ህዝብ የሚበጀውን አዋቂነት ጋር ተደማምሮ የጅጅጋ ፖለቲካ ሙክክ ብሎ እንዲበስል አድርጎታል፡፡አሁን በነእ አቶ አህመድ ሽዴ ቆስቋሽነት የተነሳው የለውጥ ቅልበሳ ሴራ የሚናቅ ባይሆንም ህዝባዊ ድጋፍ ስለማይኖረው እምብዛም ሩቅ የማይሄድ ግን ደግሞ በአንክሮ ሊታይ እና መላ ሊባል የሚገባው ችግር ይሆናል፡፡አቶ አህመድ ሽዴ ከዚህ በኋላም በዶ/ር አብይ እልፍኝ እንዲሽሞነሞኑ ሊፈቀድላቸው አይገባም፡፡ሌላ ሰው የማይገባው የኢህአዴግ ካድሬዎች ጠላትን አጠገብ በማድረግ የሚከናወን የፖለቲካ ጨዋታም ቢሆን እንዲህ ነገሮች ፍርጥ ብለው ከወጡ በኋላ የሚያመጣው ጥቅም ያለ አይመስለኝም፡፡

ይልቅስ አጋጣሚውን ተጠቅሞ የወዳጅ ጠላትን ማጥፋቱ የተሻለ ይሆናል፡፡አደገኛ ጠላትን አጠገብ አድርጎ መሾም መሸለሙ፣በክልሉ የተጠላ ካድሬን ፌደራል ወንበር ላይ ቂብ አድርጎ ረዥም እጁን ወደ ተወለደበት ክልል ፖለቲካ እንዲሰድ የመልቀቁ የኢህአዴግ ካድሬዎች ዘይቤ ኢህአዴግ ላልሆኑት አቶ ሙስጠፋ ግርታን መፍጠሩ አይቀርም፡፡የሆነ ሆኖ አቶ ሙስጠፋ ዑመር ድምፃቸውን አጥፍተው፣በአጭር ጊዜ ላስመዘገቡት ድንቅ አስተዳደራዊ ብልጫ ምስጋና የሚገባቸ፣ያለንበትን ዘመን የሚመጥን ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሊደግፋቸው የሚገባ፣በሃገር ደረጃ ሳይቀር ትልቅ ስራ የመስራት ችሎታ ያላቸው ብስል እና የተግባር ሰው ናቸው፡፡

LEAVE A REPLY