ይድረስ ለዶክተር አሻግሬ ይግለጡ እና ዶ/ር ትእግስት መንግስቱ ሃይለማሪያም |ዲጎኔው ሞረቴው ከአሜሪካ

ይድረስ ለዶክተር አሻግሬ ይግለጡ እና ዶ/ር ትእግስት መንግስቱ ሃይለማሪያም |ዲጎኔው ሞረቴው ከአሜሪካ

ተስፋ ስለሌላቸውም ሁሉ ተፋረድ  በእውነትም ለድሃና ለምስኪን ፍረድ ምሳሌ 31:8

በሃገራችን ኢትዮጲያ ፍትህ እኩልነትና ዲሞክራሲ  ይሰፍን ዘንድ ለደከሙና ክቡር ህይወታቸው ለሰጡ በተለይ ዛሬ ቀና ብለው ማየት ለማይችሉት ክብርና እውቅና መስጠት የተገባ ነው:: በሌላውም አንጻር ይህን የሃገራችንን በጎ መጻኢ እድል ለማዳፈን የተጉትና ተባባሪዎቻቸው በታሪክም በህግም የመጠየቅ ተገቢ ሂደት ሊደረግ የግድ ነው::

ሰሞኑን ካለሁበት ከምከታተላቸው ብዙ የግል ታሪክ መቀባባቶች ማሳመሮች መካከል ዝም ለማለት ያስቸገሩኝ የቀድሞው የኢትዮጲያ መንግስት አምባገነን መሪ መንግስቱ ሃይለማሪያም ባለሟል ሚንስትር ዶ/ር አሻግሬና የኮሎኔሉ ልጅ  ዶ/ር ትእግስት ቃለምልልሶች ናቸው:: የሌሎቹን በደርግና በወያኔ  የክፉ ስርአቶቹ ተባባሪ ፕሮፓጋንዳ ሰሪዎችና ተላላኪዎች መልስ ልስጥ ቢባል ጊዜ ስለማይበቃ የፈጣሪ መንፈስና ህሊናቸው ይመልስላቸው::

ዶር አሻግሬ በሚመሩት ንግድና ቱሪዝም ሚንስቴር ያኔ የነበረው የተማሪውን ትግል የበለጠ ለመተባበር  ተቀጥሬ በመስራት ላይ ሳለሁ ዶ/ር አሻግሬ የመደቡት ካድሬ ጥላዬ ተሾመ ታጋዮችን ሃጎሳን አምዴን ጸጋዬ ተክሉና በሃይሉ ሞረቴውንና ሌሎቹንም በማስለቀም ሲያሳስሩ ራሴም ከቀበሌዬ በጥቆማ ለመታሰር በቅቼ ነበር:: ሁላችንም ተገርፈን በተለይ አምዴ ጥፍሩ ተነቅሎ ሲፈታ ሃጎሳና በሃይሉ በደርግ ገዳዮች ተሰውተዋል:: ማንነቴን ስለማያውቁ ለካድሬነት ወደህዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽ/ ቤት ሊልኩኝ ብዙ ሞክረው ነበር::  ዶ/ር አሻግሬ በነበልባል እየተጠበቀ የደርግ ታማኝነቱን በሚገባ እየፈጸመ ለምክትል ጠቅላይ ሚንስትርነት ሲደርስ  ጥላዬ ግን በመኢሶን  አባልነቱ ቆይቶ ወያኔ ሲገባ ታስሮ ተለቋል:: ከሰፈራችን ጠቁሞ ያስገረፋቸው ያስገደላቸው መሃመድ ሳላ ተካልኝና ሌሎቹም ይገኛሉ:: ዶ/ር አሻግሬ  በሃሰት ይህን ቅንብር  ሳላውቅ የምንም ፖለቲካ ድርጅት አባል ሳልሆን ነው በማለት ዛሬ ታሪካቸው ሊያሰማምሩ  ዝም ብል በአመራራቸው ታፍነው የተገረፉ የተገደሉ  ወገኖቼ አጥንት ይወጋኛል:: ይህን ኢሳትም ሆነ ሌሎቹ ሚዲያዎች እኔንም ሆነ ሌሎች በህይወት ያሉ የንግድና ቱሪዝም ሚንስቴር ባልደረቦችን  መጠየቅ ይችላሉ::

ቀጣይዋ ዶ/ር ትእግስት ምንም እንኳን የሴት ልጆች አባት ሆኘ የሴቶችን ክፉ መናገር ባልወድም ስለእውነት ግን ዝም ማለት ያቅተኛል:: አንቺ ወንድሞችና እህቶችሽ ተሳክቶላችሁ ለከፍተኛ ደረጃ ብትደርሱም አባትሽን ለደርግ አባልነት ያበቁት ኮሎኔል አጥናፉ አባተ ልጆችና ሚስት ኮሎኔሉ ሲገደሉ ለዘመናት ያገለገሉት ከቁጥር ሳይገባ ያለጡረታ ከመንግስት ቤት ተባረው ህይወታቸው የተጎዳ ያበዱና ዛሬ በድህነት የሚኖሩትን ብትችይ ርህሩህ እናትሽ ወ/ሮ ውብአንች ያኔ ያቀፉዋቸውን የኮሎኔል አጥናፉን ሚስት ካሉ  ቢደገፉ ከሌሉ ልጆቻቸውን ብትረጅ ትልቅ በጎ ስራ ይሆናል:: ከዚህ በተረፈ አባትሽ ጳጳሱን ቴዎፍሎስን ፕሮቴስታንቱ ቄስ ጉዲናን የጅማ ሼኮችን ያስገደሉ ለብላቴናዎች ለነባቢሌ ላስረሸኗቸው የጥይት ዋጋ ላስከፍሉና ድንቅ የሃገራችንን ጄነራሎች ሚንስትሮችና ምሁራን ከመቶሺዎች በላይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ለጨፈጨፉ ምንም የታሪክ ማስተካከያ ማሻሻያ የለም  ሁሉን ይቅር ከሚል ፈጣሪ በንስሃ ይቅርታ ከመቅረብ በስተቀር::

LEAVE A REPLY