አስራት ቴሌቭዥን | ታሪኩ ደሳለኝ (ሚኪ)

አስራት ቴሌቭዥን | ታሪኩ ደሳለኝ (ሚኪ)

ትውስታ ፩
ከእናቴ ልጀምር፤ ዕድሜዋ ወደ ሰባዎቹ ተጥግቷል። ዛሬ በህይወት ያሌለችው የመጀማሪያ ልጇ (የማላውቃት እህቴ) ቆንጂት በ1960ዎቹ መጀመሪያ በሁለት ወሯ በፅኑ ታማ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተኝታ ነበር። የሚከታተሏት ደግሞ ፕሮፌሰር አስራት ነበሩ። ከዕለታት አንድ ቀን ህመሙ ይብስባትና በነፍስ ታጣጥር ጀመር። ተረኛ ሐኪሙና ነርሶቹ አብዝተው ተጨነቁ። ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ እየወጣ ሲሄድ፣ በዕለቱ እረፍት ወደ ነበሩት ፕሮፌሰር አስራት ቤት ይደውላሉ፤ የሉም። ቤተ-መንግሥት እንደሆኑ ይታወቃል።

ወደእዛው ተደውሎ የሕፃኗ ጉዳይ ይነገራቸውና “ምን እናድርግ?” ሲሉ ምክር ይጠይቋቸዋል።
“ቆይ፤ አሁኑኑ እራሴ መጣሁ”
ታምናለህ! ሕዝብ ቆጣሪ ለማያውቃት አንዲት የድሃ ልጅ ከጃንሆይ ቤት ሲበሩ እንደ መጡ?! በወቅቱ የጋለውን አበርደው፣ የእናቴን ጭንቀት ቢቀንሱም፣ ቆንጂት ከሁለት ወር በኋላ ከተወለደች ጀምሮ ሲጠብቋትና ሲያጫውቷት በነበሩ የሰማይ መልአክት እቅፍ ሥር ወድቃለች።

እናቴ ስለ አስራት ወልደየስ አውርታ አትጠግብም፤ ደግነትና ርህራሄያቸውን ዘውትር ትተርክልናለች። መለስ ዜናዊና ጓደኞቹ አሰቃይተው የገደሏቸው ግዜ፣ ዜናውን ታላቅ ወንድሜ ሲነግራት ምርር ብላ ማለቀሷን አስታውሳለሁ።

ከትላንት ወዲያ ደግሞ በሁለት ሠይፍነት በስማቸው የተሰየመ ግዙፍ ሚዲያ እየተቋቋመ እንደሆነ ስነግራት፣ አላስጨረስችኝም ዶ/ር አብይ አህመድን ለመመረቅ ተጣደፈች። አቋረጥኳትና ዶክተሩ እዚህ ውስጥ እጃቸው እንደሌለበት ነግሬያት ሳበቃ፤ መስራቾቹ የእኒህን ታላቅ ሰማእት አርማ ያነሱ ወጣቶች እንደሆኑ ነገርኳት። ለአፈታ በአርምሞ ከተዋጠች በኋላ በተለመደው አስራአታዊ አክብሮቷ እንዲህ አለችኝ:- “ገና ምን አይተህ ብዙ መታወሻ ይታነፅላቸዋል”

ምን ለማለት ነው? በፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ስም “አስራት” ቴሌቪዥን ጣቢያ ለማቋቋም ከግማሽ መንገድ በላይ መኬዱን በመመልከታችን ለማመስገንና ወደፊትም የበኩላችንን ለመወጣት መዘጋጀታችንን ለመጠቆም ነው። በመጨረሻም ይህንን ለማለት ወደድኩ “ሚዲያዎች ብዙልን፣ ተባዙልን።

አዲስ አበባ
የካቲት 5/2011

LEAVE A REPLY