የ”ሶማሌ” – ጦርነት እና እናቴ | ጽዮን ግርማ

የ”ሶማሌ” – ጦርነት እና እናቴ | ጽዮን ግርማ

ለእናቴ የፖለቲካ ጨዋታ አይመቻትም። ለእርሷ ደግሞ ሁሉ ነገር ፖለቲካ ነው። ቤት ውስጥ መንግሥት ሲወቀስም፤ ሲወደስም አትወድም። “እግዚያብሔር ያስቀመጠውን ማንም አይሽረውም።” የሚል ጥብቅ አቋም አላት። ፖለቲካ መሰል ወሬ ከተነሳ ትቁነጠነጣለች፤ “አሁን ፖለቲካውን ተውና ሌላ ጨዋታ አምጡ። ፖለቲካው ባለቤት አለው” ትለናለች። በስህተት ፖለቲካ የመሰላት ወሬ አፏ ከገባ እንኳን የፈጣሪን ስም ጠርታ ታስወጣዋለች። ሁሌ ታስገርመኛለች።

አንድ ታሪክ ግን አላት ከጀመረች የማታቋርጠው። ስለ ሶማሌ ጦርነትና ስለ ዚያድ ባሬ ካነሳች ማቆሚያ የላትም፤ “ፈጣሪ መቼም እሱን ጊዜ አይመልስው” ትላለች። የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዚያድ ባሬ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ካወጁ በኋላ ጦራቸው ድንበር ጥሶ ገብቶ ጦርነት ከከፈተባቸው ከተሞች አንዱ ሐረር – በእናቴ አገር ነበር።

ለጦርነቱ የዐይን እማኝ ናት። “አቤት ፣አቤት የጥይት ድምፅ” ትላለች። “ደሞ በየመንደሩ እየመራ የሚያመጣቸው ሰው ነበር። ቀስ ብለን በቀዳዳ ስናያቸው አቤት አረዛዘማቸው” ይሰቀጥጣታል። “የመንደሩ ሰው ሁሉ አንድ ላይ አንድ ቤት ውስጥ ይሰበሰባል። ጥይት እንዳያገኛቸው ቅድሚያ ለሕፃናት ሰጥተን ፍራሽ እንጭንባቸዋለን። ከተረፈ ደግሞ ለሴቶችም እንዲያው ይደረጋል። ወይ ጭንቀት! ወይ ጊዜ!” ትላለች። “ከዛ ክፉ ጊዜ ያስወጡን ልጆቻችን በደንብ መወደስ ነበረባቸው” ስትል በቁጭት ታስታውሳለች።

ፈጣሪዋ እንዲህ ያለ ጭንቀት በዘመኗ መልሶ እንዳያሳያት አደራ ትሰጠዋለች። ጅግጅጋ፣ ሐረርና ድሬድዋ የጦርነት አውድማ እንደነበሩ ትነግረናለች። የስንት ሰው ሕይወት እንደተቀጠፈ እያስታወሰች ታዝናለች። ድንበርን ማስጠበቅ እንዴት ጥብቅ መሆን እንዳለበትም ትንታኔ ትሰጣለች።

ዛሬ የዚህ ጦርነት ማብቂያና የኢትዮጵያ ጦር የሶማሊያ ወራሪ ኃይልን ያሸነፈበት የካራማራ ድል 41ኛ ዓመት መታሰቢያ መሆኑን ይኸው የፌስቡክ መንደር ሲያስታውሰኝ እናቴም ትዝ አለችኝ። “ለእናቶቻችን እንዲህ ያለ የጭንቅ ጊዜ መልሶ አያምጣባቸው።” የሰው አገር እናትን ኑሮ ባየሁ ጊዜ መመኘት የጀመርኩት ልባዊ ምኞት ነው። መላ አገራቸውን ሰላም አድርጎ ከጭንቀት ይገላግላቸው🙏

LEAVE A REPLY