በብዙ ሚሊዮን ብር በታደሰው የምኒሊክ የግብር አዳራሽ ውስጥ የእራት ግብዣው ተሰናድቷል፡፡ በእዚህ ድግስ ላይ ለመገኘት አምስት ሚሊዮን እና ከእዚያ በላይ ገንዘብ ያዋጡ ግለሰቦችና ድርጅቶች ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል፡፡
ፕሮግራሙን ያዘጋጁት ጠቅላይ ሚኒስቴር መንገድ ላይ የተሰጡ ቆሻሻዎችን ቀኑን ሙሉ ሲያጸዱ በማዋላቸው… ከድካም በተጨማሪ ሃይለኛ የጉንፋን ስሜት እየተሰማቸው ነው፡፡
ይሄም ሆኖ ግን ህመማቸውን ለማታከም ወደ ጤና ተቋማት ቢሄዱ ሰሞኑን ቂም የያዙባቸው ዶክተሮች በፓናዶል ፈንታ የምጥ መርፌ ወግተው እንደሚመልሷቸው ስለተረዱ የፈላ ውሃ ሊታጠኑት እንጂ ሊታከሙት አልፈለጉም፡፡
እኔ ቤተ-መንግስቱ ውስጥ የተገኘሁት ፆለቴ በመሰካቱ ነው፡፡ ‹‹እባክህን ጌታ ሆይ ያለምንም ሃሳብ የምዝናናበትና የፈለኩትን የምበላበት አምስት ሚሊዮን ብር ስጠኝ ብዬ ብጠይቀው በገንዘቡ ፈንታ እራቴን አመቻችቶ ‹‹ጋዜጠኛ›› በሚል ስም ማይክና ካሜራ አሸክሞ ከምኒሊክ አልፍኝ አስገባኝ፡፡
በካሜራዬ ሌንስ አዳራሹን ስቃኘው…. ከዚያ ሁሉ ባለሃብቶች መሃከል የማህደር አሰፋ ውበት ደምቆ ይታያል፡፡ ማሂ ነፍሴ ባንድ ወቅት የሙያ አጋሮቿ የነበሩ አርቲስቶች በችግርና በእጦት እየተንገላቱ ‹‹ሀብቴ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው›› በሚል መጽናኛ እድሜያቸውን ሲገፉ… ቆንጅዬዋ ልጅ ግን ‹‹የኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ እና ህዝብ መቼም ቢሆን ሃብት ሊሆኑ እንደማይችሉ ቀድማ ባወቀች ጊዜ በመክሊቷ ፈንታ ውበቷን በመጠቀም የ5 ሚሊዮን እራት እስከ መብላት ደረሰች፡፡ (የተባረከ እራት ይሁንላት!)
አደራሹ ውስጥ የታደሙ ባለሀብቶችና ሚኒስቴሮች በማውራት ፈንታ ተኮራርፈው የየራሳቸውን ሃሳብ ያሰላስላሉ፡፡ ጭንቅላታቸው ውስጥ ገብቼ የሚያስቡትን ስገምት…. ባለሃብቶቹ ለዚህ እራት የከፈሉትን ገንዘብ እጥፍ አድርገው የሚያስመልሱበትን መንገድ፣ ባለሥልጣናቱ ደግሞ ከአጠገባቸው እንዳሉት ባለሐብቶች ከሚኒስቴርነት ወደ ሚሊየነርነት የሚቀየሩበትን ስልት የሚያስቡ መሰለኝ፡፡ እናም ግምቴ ትክክል ከሆነ የሃሳባቸውን ጥግ ‹‹ጨረታ›› በሚል የስኬት ቃል ሲያጠናቅቁ ሁለቱም ተቀራርበው ማውራታቸው አይቀሬ ነው፡፡
ከተለያዩ ባንኮች የመጡ ሥራ አስኪያጆች አንድ አካባቢ ላይ ተከማችተው ይታያሉ፡፡ በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥራ-አስኪያጅ ከሆኑት ባለሥልጣን ጎን የባንኩ ዋና ደንበኛ የሆኑት ኦቦ ዳውድ አቢሳ ተቀምጠው ‹‹በምዕራብ ወለጋ አካባቢ የሚገኙ ባንኮች የሚሰጡት አገልግሎት ከቀን ወደ ቀን እየተቀላጠፈ መምጣቱን›› ሲነግሩት ከቆዩ በኋላ ‹‹500 ሚሊዮን ብር ለመንግስት የሰጣችሁት ማን ፈቅዶላችሁ ነው?›› የሚል ጥያቄ አነሱ፡፡
‹‹ቦርዱ ፈቅዶ ነዋ!›› ብሎ በመለሰላቸው ጊዜም ‹‹ቦርዱ በእኛ ገንዘብ ምን ያገባዋል?›› ከሚል ጥያቄ ጋር ‹‹በነገው እለት ከኃላፊነትህ ያላነሳሁህ እንደሆነ ʹመንግስትʹ ብለህ አትጥራኝ›› ብለውት ፊታቸውን አዞሩ፡፡
በትዝብቴ መሃከል እራቱ ትዝ ሲለኝ ምራቅ በሚያመነጩ እጢዎቼ ውስጥ ከፍተኛ መነቃቃት ተፈጠረና… የአምስት ሚሊዮን ብር እራት መብላት ብሩን ከማግኘት በላይ እንዳጓጓቸው ገለጹ፡፡ ይሄም በሆነ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ወደ መድረክ በማምራት እራቱ የሚበላበትን ሰዓት ፕሮጀክቱ እንደሚጠናቀቅበት ዓመት ያስረዘመ ንግግር አደረጉ፡፡
በማስከተል ነጋሪት ከተጎሰመ በኋላ ሁሉም ታዳሚ በየተራ ከመቀመጫው እየተነሳ ቡፌ ማንሳት ሲጀምር የካሜራዬን አቅጣጫ ወደዚያው አቅጣጫ አዞርኩት፡፡
ለዚህ የእራት ግብዣ ምንም ዓይነት መዋጮ ያልከፈሉት ጠቅላይ-ሚኒስቴር የሰው እራት መብላት የደበራቸው ይመስል ምግቡን ትተው ሰሐኑን ብቻ በማንሳት ወደ መቀመጫቸው ሲመለሱ እሳቸውን መምሰል የሚፈልገው ከንቲባም ተመሳሳዩን አደረገ፡፡ ከሌሎች ባለሃብቶችና ባለሥልጣናት ሰሃን ላይም የተረዳሁት ነገር ቢኖር የገንዘብ እንጂ የምግብ ፍላጎት እንደሌላቸው ነው፡፡
ዋና ዋና የግብዣው ታዳሚዎች ተስተናግደው ከጨረሱ በኋላ በፆለትና በልዩ ልዩ ምክንያት ከግብዣው ላይ የተገኘን ሰዎች ከመኖሪያ ቤታችን መጠን በላይ ከሚሰፋ የመኖ ጠረጴዛ ዙሪያ ተኮልኩለን…. 80 ብሔር ብሔረሰቦችን በምድሯ ላይ ማቻቻል ባቃታት አገር ላይ 80 አይነት ምግቦችን በአንድ ሰሐን አቻችለን ለማስቀመጥ እንታገል ጀመር፡፡ ሆኖም ግን ያንን ያህል የምግብ አይነት በአንድ ሰሃን ላይ ለማስቀመጥ ከብቃት በተጨማሪ አስማት ያስፈልግ ስለነበር ከሰሐናችን አቅም በላይ የሆኑትን ምግቦች በካሜራችን አማካኝነት ማንሳቱን ታያያዝነው፡፡
ከዚያም በትንሽ እቃ ላይ የከመርነው ‹የምግብ ክምር› ልክ እንደ ምድር ተንሸራቶ በሰዎች ሕይወት ላይ አደጋ እንዳያደርስ ሚዛናችንን መጠበቅ ስለነበረብን…. የመሬት ስበት ጨምድዶ እንደያዘው ሰው እግራችንን ከአዳራሹ ወለል ላይ እያንፏቀቅን ወደ ወንበራችን እናመራ ጀመር፡፡
እንዳለመታደል ሁኖ ግን እኔም በዚህ ሁኔታ ሚዛኔንና እይታዬን ከሳህኔ ላይ አሳርፌ ያለ ምንም መንገራገጭ በለውጡ መንገድ ላይ ስራመድ ከቆየሁ በኋላ…. ከቁጥጥሬ ውጭ በሆነ መልኩ ለቅጽበት ያህል የተንቀሳቀሰ ዓይኔ ከማህደር ዐይን ጋር ተገጣጠሞ አልንቀሳቀስ አለ፡፡
በዚህን ጊዜም የፊት ገጽታዬን በመጠቀም ‹‹ምግቤ ሳይደፋኝ በፊት ዐይኗን እንዲትጨፍንልኝ›› አባበልኳት፡፡
አልሰማችኝም!
ጭራሽ ከፊቴ ላይ ያሳረፈችውን ዓይኗን ከብለል አድርጋ ወደ ቁርጭምጭምቴ ስታወርደው……. ከቆዳ ስፋቷ በሚሰፋ ሰሐን ላይ ያስቀመጥኳት ‹‹አገሬ›› በምዕራብ በኩል መንኮታኮት ጀመረች፡፡
ይሄን በአገር ላይ የተቃጣ አደጋ ለመታደግ እየጣርኩ ሳለሁ ደግሞ… ማሂ በዓይኗ ጨረር ላይ የሚያምረውን ፈገግታውን ጨመረችበትና እኔ እና ሰሐኔ እንደ ባቢሎን ሥልጣኔ ባንድ ላይ እንዲንፈራርስ ፈረደችብን፡፡ እናም ይሄ ዘግናኝ አደጋ ሲከሰት ከስሬ የነበሩ አንድ ባለሥልጣን እንደ ግንቦት ሰባት ተጨፍልቀው ከመክሰማቸው በፊት እንዲህ ሲሉ ሰማኋቸው፡፡
‹‹የቆሻሻውን እና የመናፈሻውን ነገር አደራ!››