የዛሬ ማክሰኞ ዐበይት ዜናዎች || ዋዜማ

የዛሬ ማክሰኞ ዐበይት ዜናዎች || ዋዜማ

1. ለኢትዮጰያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ስራ አመራር አባላትን ለመምረጥ የተቋቋመው ኮሚቴ የዕጩ መመረጫና የመጠቆሚያ መስፈርቶችን አሳውቋል፡፡ ኮሚቴው ዛሬ በሰጠው መግለጫ ከመጠቆሚያ መስፈርቶች መካከል ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆነና ከምርጫ ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ዘርፎች የአመራር ብቃት ያለው የሚሉት እንደተካተቱ ፋና ብሮድካስት ዘግቧል፡፡ ጥቆማ ለኮሚቴው የሚቀርበው በኢሜል፣ በደብዳቤና በፖስታ ሲሆን በተለይ በጸሁፍ ቢቀርብ ተመራጭ ይሆናል፡፡ የጥቆማ ቀነ ገደቡ እስከ ግንቦት 22 ምሽት 11፡30 ድረስ ነው፡፡ መስፈርቶቹ ከዛሬ ጀምሮ በመገናኛ ብዙሃን ይተላለፋሉ፡፡

2. የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ አየለ ዲቦ ከዳኝነት እንዲባረሩ ያቀረበውን ውሳኔ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውድቅ እንዳደረገው ሸገር ዘግቧል፡፡ ምክር ቤቱ በ8 ተቃውሞ በ5 ድምጸ ተዓቅቦ ነው ውሳኔውን ያሳለፈው፡፡ በመሆኑም ላንዱ ጥፋት ብቻ በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ደንብ መሠረት የዲስፕሊን ቅጣት ተቀብለው ወደ ዳኝነት ሥራቸው እንዲመለሱ ተወስኗል፡፡ ዳኛው ፈጸሟቸው ከተባሉት 5 የዲስፕሊን ጥፋቶች መካከል ቀደም ሲል በሌሎች ችሎቶች የተከለከለን የክስ ይጣመርልን አቤቱታ መፍድቀዳቸውን ብቻ ነው እንደ ጥፋት ያገኘሁባቸው- ብሏል ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው የፍትህ፣ ህግና ዲሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ፡፡ ጉዳዩ ዘለግ ላለ ጊዜ ምክር ቤቱን፣ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤንና ቋሚ ኮሚቴውን ሲያከራክር መቆየቱ ይታወሳል፡፡

3. ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የነዳጅ አቅርቦትና ሥርጭት የሚቆጣጠር ባለስልጣን እንዲቋቋም ወስኗል፡፡ ኢዜአ እንደዘገበው ባለስልጣኑ የመንግስትን ነዳጅ አቅርቦት ይቆጣጠራል፤ ሕገ-ወጥ ተግባር ሲፈጸም ርምጃ ይወስዳል፡፡ ለነዳጅ ውጤቶች ደረጃ ያወጣል፤ በወጣው የሀገሪቱ ደረጃ መሠረትም መስፈርቶች ስለሟሟላታቸው ክትትል ያደረጋል፡፡ የግብይቱ ተሳታፊዎች ሕጉን ጥሰው ሲገኙ ደሞ የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀታቸውና የንግድ ፈቃዳቸው እንዲታገድ ወይም እንዲሰረዝ ያደረጋል፡፡ ተቋሙን ማቋቋም ያስፈለገው በውድ ዋጋ የሚገዛው ነሳጅ ለብክነት እየተዳረገ በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡

4. ሐኪሞችና የህክምና ተለማማጆች ያቀረቧቸው ጥያቄዎችን ለመፈታት ጥናት ጀምሬያለሁ- ብሏል የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር፡፡ ለዚሁም ሚንስቴሩ 4 የጥናት ቡድኖችን አቋቁሟል፡፡ ከተለያዩ ዘርፎች ምሁራን የተካተቱባቸው አጥኝ ቡድኖች አዳማ ላይ ተሰብስበው እየሰሩ መሆኑን ሸገር ዘግቧል፡፡ የተለማማጅ ሐኪሞች ያነሷቸው ጥያቄዎች 5 ሲሆኑ ሁሉም ተገቢ ናቸው ተብሏል፡፡

5. በቤንሻንጉል ክልል ባለፈው ሰኔ በተቀሰቀሰው ግጭት 53 ተከሳሾች ፍርድ ቤት ቀርበው ምስክር እየተሰማባቸው መሆኑን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡ ሰዎቹ የተከከሰሱት በአሶሳ ከተማ ዙሪያ የ16 ሰዎች ሕይወት እንዲጠፋ በማድረጋቸው ነው፡፡ ከተከሳሾቹ መካከል የቀድሞው የአሶሳ ከተማ ከንቲባ፣ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ፖሊስና ልዩ ሃይል የቀድሞው አዛዦች ይገኙበታል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እስካሁን አሶሳ ከተማ በተሰየመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት 65 የሰው ምስክሮችን ያሰማ ሲሆን ቀሪ 95 ምስክሮች ደሞ ይቀሩኛል ብሏል፡፡ ቀጣዩ ቀጠሮ ግንቦት 19 ነው፡፡

6. ጃፓን በያዝነው የፈረንጆች ዐመት “ስፕሪንግ ኢምፔርያል” የተባለውን ለውጭ ዜጎች የምትሰጠውን ሽልማት ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ልታበረክት መሆኗን አስታውቃለች፡፡ DW እንደዘገበው ሽልማቱ የጃፓንና የኢትዮጵያን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር እንዲሁም በቶክዮ ዐለም ዐቀፍ የአፍሪካ ልማት ጉባኤ አማካይነት የጃፓን-አፍሪካን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ስለጣሩ መሆኑን በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ አስታውቋል። ሽልማቱ በመጭው ሐሙስ የጃፓን ንጉስ አኮሂቶና ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በተገኙበት በጃፓን ቤተ መንግሥት ይሰጣቸዋል። ከኃይለ ማርያም ጋር በጠቅላላው ከ61 ሀገራት የተመረጡ 142 የውጭ ዜጎች ይሸለማሉ፡፡

LEAVE A REPLY