የዛሬ ሰኞ ዐበይት ዜናዎች || ዋዜማ

የዛሬ ሰኞ ዐበይት ዜናዎች || ዋዜማ

1. የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር ብርቱካን ሚደቅሳ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በውይይቱ የተሳተፈው የዋዜማ ሪፖርተር እንደዘገበው ቦርዱ ቀጣዩ ምርጫ በተያዘለት ዕቅድ እንደሚካሄድ ታሳቢ አድርጎ ተቋማዊ ለውጥ እየሰራ ነው፤ ለምርጫው ማካሄጃም 3.7 ቢሊዮን ብር ከመንግሥት ጠይቀናል ብለዋል- ሊቀመንበሯ፡፡

የሀገር ዐቀፉ ሕዝብና ቤት ቆጠራ እስካሁን አለመካሄዱ በምርጫው ላይ ተጽዕኖ ያመጣ እንደሆነ ሲናገሩም በመራጮች ምዝገባ ላይ ተጽዕኖ እንደማይኖረው ገልጸዋል፡፡ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ መቸ ይካሄድ የሚለውም ገና እንዳልተወሰነ ተናግረዋል፡፡

2. በሶማሌ ክልል “የጄል ኦጋዴን” እስር ቤት ሃላፊ የነበረው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ፋና ብሮድካስት ዘግቧል። ሐሰን ኢስማኤል ኢብራሂም ወይም በቅጽል ስሙ “ሐሰን ዲሬ” ሶማሊያ ውስጥ ባለች የድንበር ከተማ ተደብቆ ሳለ ነው በሱማሊያ ጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ሥር ያዋሉት፡፡ ለኢትዮጵያ ተላልፎ ከተሰጠ በኋላም ባሁኑ ሰዓት በጅግጅጋ እስር ቤት ይገኛል። ግለሰቡ በቀድሞው የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ መሐመድ ኦማር ዘመን በክልሉ ውስጥ በተፈጸሙ ሰቆቃዎችና የሰብዐዊ መብት ጥሰቶች ዋና ተፈላጊ ነው፡፡ ግለሰቡ ከእነ አብዲ መሐመድ ኦማር ጋር በፌደራሉ ፍርድ ቤት ክስ ከተመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎች መካከል አንዱ ነው።

3. ሳዑዲ ዐረቢያ ለኢትዮጵያዊያን ቤት ሠራተኞች የሰጠችውን ቪዛ መሰረዟን የሳዑዲ ጋዜት ድረ ገጽ ዘግቧል፡፡ ኢትዮጵያንም ላሁኑ ሠራተኛ ከሚቀጠርባቸው ሀገራት ዝርዝር ሰርዛታለች፡፡ ይህ የሆነው በቅጥርና ምልመላ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እስካሁን ስምምነት ሊደረስ ባለመቻሉ ነው ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ለምልምል ሠራተኞች ቋሚ የጤና መመርመሪያ ማዕከል እንዲያቋቋም ሳዑዲ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጧ አንዱ የልዩነት ነጥብ ነው፡፡ ሠራተኛ ቀጣሪ ኤጀንሲዎች ለሚቀጥሯቸው ሠራተኞች የመኖሪያ አገልግሎት እንዲያቀርቡም ትፈልጋለች፡፡ ከረመዳን በፊት በርካታ ተቀጣሪ ቤት ሠራተኞች ሳዑዲ እንደሚገቡ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ማንም አልገባም፡፡

4. የውጭ ባለሃብቶች በኮንዶሚኒየምና ሪል እስቴት ቤቶች ግንባታ ዘርፍ እንዲሳተፉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚንስቴር ያቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ እንደገና እንዲታይ ገንዘብ ሚንስቴር ወስኗል፡፡ እንደ ካፒታል ዘገባ በዘርፉ የውጭ ኩባንያዎች መሳተፋቸው ለዜጎች ሥራ ፈጣሪ አይሆንም፤ መንግሥትንና የቤት ገዥዎችንም ከፍተኛ ወጭ ይጠይቃል- ብሏል ገንዘብ ሚንስቴር፡፡ ሃሳቡ ቢያንስ ለ3 ዐመታት እንደገና እንዲጠናም አሳስቧል፡፡ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚንስቴር መነሻ ሃሳብ የሀገር ወስጥ ባለሃብቶች ለቤት ግንባታ በቂ የገንዘብ አቅም የላቸውም የሚል ነው፡፡

5. ከ8 ዓመታት በፊት ምስረታ ሂደት ላይ ሳለ ታግዶ የነበረው ዘምዘም እስላማዊ ባንክ ሥራውን እንዲጀምር ከብሄራዊ ባንክ ፍቃድ እንዳገኘ ሪፖርተር አስነብቧል፡፡ ባንኩ በእስልምና ሐይማኖታዊ ቀኖና መሠረት ከወለድ ነጻ ብድር ለማበደር ነው የተቋቋመው፡፡ 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ይዞ ወደ አክሲዮን ሽያጭ ለመግባትም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ደብዳቤ እየተጠበቀ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለብሔራዊ ባንክ ገዥ ደብዳቤዎችን በመጻፍ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳደረጉም የባንኩ ምስረታ አስተባባሪዎች ይገልጣሉ፡፡ ብሄራዊ ባንክ በቅርቡ ባንኮች ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት እንዲኖራቸው መፍቀዱ ይታወሳል፡፡

6. ለእሳት አደጋ መቆጣጠሪያ ሄሊኮፕተር እንዲገዛ ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ጠያቂው የከተማዋ የእሳት አደጋ መከላከል ሥራ አመራር ኮሚሽን ነው፡፡ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ በዘንድሮው ወይም በመጭው በጀት ዐመት ሄሊኮፕተር ለመግዛት እንሞክራለን፤ ካልሆነም በእርዳታ አፈላልገን እናመጣለን ብለዋል ሲል ሸገር ዘግቧል፡፡

LEAVE A REPLY