አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በእስር ቤት የጻፉት መጽሐፍ ነገ ለገበያ ሊቀርብ ነው

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በእስር ቤት የጻፉት መጽሐፍ ነገ ለገበያ ሊቀርብ ነው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በብዙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ በእጅጉ የሚወደዱትና በነጻነት ታጋይነት ስማቸው ጎልቶ የሚጠቀሰው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በእስር ቤት ቆይታቸው የጻፉት፣ “ትውልድ አይደናገር፤ እኛም እንናገር” የሚል መጠሪያ የተሰጠው አዲስ መጽሐፍ የፊታችን አርብ ግንቦት 30 ቀን2011 ዓ.ም በገበያ ላይ እንደሚውል ታውቋል፡፡

በጊዜው የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ኢህአዴግ ያለበትን ችግርና እግረመንገድም መፍትሔውን በጸሁፍ እንዲያመላክቱ ላፕቶፕ ኮምፒዩውተር ሰጥተዋቸው ነበር:: በዚህም መስርት የመጀመሪያውን ጥናታዊ ጽሑፍ ሰርተው አስርክበዋል:: ይህንን ታሪካዊ መጽሐፍ በጠባቧ የደህንነት ስውር ዕስር ቤት ውስጥ
እንዳዘጋጁት፣ ጽሑፉን ለማጠናቀቅም አራት ወራትን እንደፈጀባቸው ከደረሰን ዜና መረዳት ተችሏል፡፡

በወቅቱ አቶ አንዳርጋቸው መጽሐፉን ቢያዘጋጁም እስር ላይ እንዳሉ፣ የደህንነት ኃላፊዎቹ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ኮምፒውተሩን ቀምተዋቸው ነበር:: ለዓመታት ይህንን ጽሁፍ ሳያገኙና ህትመቱም ዕውን ሳይሆን ቆይቷል፡፡ በቅርቡ ግን ላፕቶፑን ወስዶባቸው የነበረው የደሕንነት ሰው (ግለሰቡ አሁንም በደህንነት መ/ቤቱ ውስጥ በስራ ላይ ይገኛል) በአንግሊዝ ኤምባሲ በኩል በኢሜይል ጽሁፉን ለኮላቸዋል:: መጽሐፉ ቢዘገይም ወደ ህዝብ እንዲደርስ ሁኔታዎች መመቻቸታቸው ታውቋል፡፡

664 ገጽ ያለው ይሄው መጽሕፈ ከነገ አርብ ግንቦት 30 ቀን ጀምሮ በነጻነት አሳታሚ አማካይነት በኢትዮጵያና አውሮጳ ለገበያ ይቀርባል:: በይዘት ረገድ አዲስ አበባ ከተማ ከተመሰረተችበት ጊዜ አንስቶ ያለውን የመቶ አመት ታሪክ፣ እንዲሁም ከባሪያ እስከ አሳዳሪ ያለው አጠቃላይ የሕይወት ውጣ ውረድን በመረጃ የሚያስቃኝ ትውልድ ተሻጋሪ መጽሐፍ እንደሆነ ከወዲሁ ተነግሮለታል፡፡ ከመጽሐፉ የሚገኘው ሰባ ከመቶ ገቢው አዲስ ለተቋቋመውና በፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ለሚመራውና የሰባት ፓርቲዎች ውህድ በመሆን ለተመሰረተው ኢ.ዜ.ማ ሀገራዊ ፓርቲ እንዲሆን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መልካም ፍቃዳቸውን ሰጥተዋል፡፡

ታላቁ የፖለቲካ ሰውና የቀድሞ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ መስራች አባል የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ በወያኔ የፀጥታ ኃይሎች የመን ላይ ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ አንድ ዓመት ከሶስት ወር የደህንነት መ/ቤቱ ስውር ቪላ ባለ አንድ ክፍል ውስጥ ከማንም ጋር ሳይገናኙ እንዲታሰሩ መደረጋቸው ይታወሳል፡፡

LEAVE A REPLY