ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ ሆቴል አዲስ ስለሚያቋቁመው የሳተላይት ቴሌቪዥን ከአጋሮቹ ጋር ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት በተዘጋጀበት ወቅት በፖሊስ የተከለከለው ጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ በነገው ዕለት አርብ ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ለማወቅ ችለናል፡፡
በቅርቡ በአዲስ አበባ ጉዳይ ሰፊ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ባላአደራ የተሰኘ ም/ቤት በቅርቡ ያቋቋመው እስክንድር ነጋ የኢ/ር ታከለ መስተዳድር ሲቃወም እንደነበር ይታወቃል::
በሕዝብ ያልተመረጠ መሆኑን በመግለጽ የአዲስ አበባ ነዋሪ የራሱን ከንቲባ እስኪመርጥ ድረስ አ/አበባን በተመለከተ ምንም አይነት ድርድር እንዳይደረግ ጠይቋል:: ይህንን ተከትሎ ስልጣን ላይ ካለው አካል ጋር ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ መግባቱና የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችና የሚጠራቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች በተደጋጋሚ በሕገወጥ መንገድ ሲሰረዝበት መቆየቱ ይታወቃል፡፡
“ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ቢደረግብን ወደኋላ መመለስ የለም፤ ወድቀን ተነስተን፣ አፈር ልሰንም ቢሆን ግፈኞችን የሚጋልጥ፣ የተገፉና ፍትህ ያጡ ወገኖቻችን ድምጽ የሚሆን እውነተኛ የሕዝብ ሚዲያ እናቋቁማለን” ብሏል እስክንድር ነጋ::
እስክንድር ነገ የአዲሱን የሳተላይት ቴሌቪዥን ምስረታ አስመለክቶ ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት በኢትዮጵያ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ይፋ አድርጓል፡፡ እስክንድር ከሰናይ ሚዲያና ከጌች አማካሪ ድርጅት ጋር በኢትዮጵያ ሆቴል ሊሰጥ የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ በሕወሓት የስልጣን ዘመን ሆኖ በማያውቅ መልኩ በሕገወጥ መንገድ መከልከሉ አስታውሷል::

























