የከተሞች ሊዝ መነሻ ዋጋ በ2 ዓመት ውስጥ እንዲከለሱ የሚያስገድድ አዋጅ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ቀረበ
ከተሞች የሊዝ መነሻ ዋጋን ከሁለት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እንዲከልሱ የሚያስገድድ ረቂቅ የሊዝ አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡ ተሰማ። በሀገሪቱ ከፍተኛ የመሬት ፍላጎት እና ስርቆት መበራከቱ በ2004 ዓ.ም አዲስ የሊዝ አዋጅ እንዲወጣ ምክንያት ቢሆንም ከሚታየው ፍላጎት አንፃር አዋጁ በድጋሚ መሻሻል አስፈልጎታል ተብሏል።
አሁንም ከተሞች የሊዝ መነሻ ዋጋን ከሁለት አመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እንዲከልሱ የሚያስገድድ ረቂቅ የሊዝ አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ታዜር ገብረእግዜአብሄር ተናግረዋል። ሚኒስትር ዲኤታው እንዳሉትም የሊዝ ስርአቱ የዜጎችን የመሬት አገልግሎት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስችላል። የሊዝ ስርአቱ የዜጎችን ከመሬት አገልግሎት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው ልማትን ማረጋገጥ የሚችል መሬት ማቅረብ እና የመሬት ዝርፊያን መቆጣጠርን አላማው ያደረገ ነው።
አዲሱ ረቂቅ ከተሞች በምደባ ለማቅረብ ካዘጋጁት መሬት ውስጥ ከ10 እስከ 20 በመቶውን ለመኖሪያ ቤት መስሪያ አገልግሎት ማዋል እንዳለባቸውም ያስገድዳል፤ ይህም የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይረዳል ነው የተባለው። በተጨማሪም የሊዝ መነሻ ዋጋ ያልከለሱ ከተሞች መሬት በጨረታም ሆነ በምደባ ማስተላለፍ እንደማይችሉ በግልጽ ያሳያል።
በረቂቅ አዋጁ መሰረት አንድ ተጫራች በአንድ የጨረታ ዙር ለተመሳሳይ አገልግሎት ከአንድ ቦታ በላይ ለመወዳደር የጨረታ ሰነድ መግዛትና መወዳደር እንደማይችልም አስቀምጧል። ከዚህ በተጨማሪ ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት ሳያቀርብ በሁለት አመት ውስጥ ሁለት ዙር አሸንፎ ሳይዋዋል የቀረ የጨረታ አሸናፊ፣ በክልሉ ውስጥ በማንኛውም የከተማ መሬት ሊዝ ጨረታ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት እንዳይሳተፍ እንደሚደረግም ሓላፊው ተናግረዋል።
የጨረታ ማስከበሪያ ዋጋ እና የመነሻ ዋጋ ዝቅተኛ መሆን እና በፍጥነት አለመከለስ የ2004ቱ አዋጅ ክፍተት እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ፤ ይህም ተጫራቾች በቀላሉ የመሬትን ዋጋ ከፍ አድርገው በማስገባት እና ከጨረታው በመውጣት የመሬት ዋጋን እንዲለውጡ ያደርጋል ነው የተባለው። አዋጁ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥልቀት ያለው ምክክር እንዲያደርጉበት መንግስት ፍላጎት በማሳየቱ ምክንያት እንዲዘገይ መደረጉን ሚኒስትር ዲኤታው አስረድተዋል።
ለምዝበራ የተጋለጠው ጥረት ኮርፖሬት ተጠሪነቱ ለክልሉ ም/ቤት እንዲሆን ተወሰነ
የአማራ ክልል ምክር ቤት እያካሄደ ባለው 14ኛ በመደበኛ ጉባ፣ ከፍተኛ ሃብት አስመዝግቧል የሚባለው ጥረት ኮርፖሬት ተጠሪነቱ ለክልሉ ምክር ቤት እንዲሆን ወስኗል።
የክልሉ ምክር ቤት የህግ ፍትህ እና አስተዳደር ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አማረ ሰጤ ጥረት ኮርፖሬት ተጠሪነቱ ለክልሉ ምክር ቤት እንዲሆን የተባለበትን ዝርዝር ሁኔታዎች በስብሰባው ላይ አሰምቷል።
ጥረት ኮርፖሬት የክልሉ ህዝብ ሃብት መሆኑን፣ የአሠራር ግልጸኝነት ችግር የነበረበት በመሆኑ እና አሁን ባለው ሁኔታ 11 ሺህ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ እድል የፈጠረ መሆኑን አስታውሰው ፣ ይህን ተከትል ጥረት ኮርፖሬት ተጠሪነቱ ለክልሉ ምክር ቤት ቢሆን ከዚህ የተሻለ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያችል መሆኑን ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ አባለት በበኩላቸው አሁን ጥረት ያለበት ሁኔታንና ከዚህ በፊት በማን ሲመራ እንደነበር ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበዋል:: በተጨማሪም ጥረት በስሩ የሚያስተዳደራቸው ተቋማት፣ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች በግልፅ ሊታወቁ እንደሚገባ ሃሳብ አቅርበዋል። ተቋሙ ሁሉን ባሳተፈ መልኩ እንደገና ቢዋቀር መልካም መሆኑንም የምክር ቤቱ አባላት መክረዋል።
የጥረት ኮርፖሬት ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር አምላኩ አስረስ ፤ የተጠቃለለ ሪፖርት የሚቀርበው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር የፊታችን ታህሣስ ወር ላይ መሆኑን በመግለጽ በሚቀጥለው የምክር ቤት ጉባኤ ላይ የሂሳብ ኦዲትን ያካተተ መረጃ የሚቀርብ መሆኑን አስታውቀዋል። ጥረት ኮርፖሬት ተጠሪነቱ ለክልል ምክር ቤት እንዲሆን የቀረበወን ሃሳብ በአራት ተቃውሞ እና በአብላጫ ድምፅ ምክር ቤቱ ያፀደቀው መሆኑ ታውቋል።
በወልዲያው ዮንቨርስቲ ግጭት እጃቸው አለበት የተባ13 ተማሪዎች ተያዙ
ቅዳሜ ምሽት ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በተፈጠረው እና የሁለት ተማሪዎችን ሕይወት ከቀጠፈው ግጭት ጋር በተያያዘ 13 ተማሪዎች መታሠራቸው በመነገር ላይ ነው።
የሰሜን ወሎ ዞን ፀጥታ እና ሰላም ቢሮ ሐሠላፊ ኮሎኔል ኃይለማርያም አምባዬ ሌሎች ተጨማሪ ተማሪዎች በግጭቱ ተሳትፎ እንደነበራቸው ተጠርጥረው እየተፈለጉ መሆኑን አስታውቀዋል።
ትናንት የአማራ መገናኛ ብዙሃን የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መኮንን ወልደትንሳዔን በመጥቀስ ቅዳሜ ምሽት ግጭት የተከሰተው፤ ተማሪዎች በጋራ እግር ኳስ በቴሌቪዝን ተመልክተው ሲመለሱ በተፈጠረ ግጭት እንደሆነና በአደጋውም ሁለት ተማሪዎች ተገድለው ስምንት ተማሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱን መዘገቡ ይታወሳል።
የሰሜን ወሎ ዞን ፀጥታ እና ሰላም ቢሮ ሓላፊ ኮሎኔል ኃይለማርያም አምባዬ የአገር መከላከያ እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ወደ ዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ መግባታቸውን እና ይሄም እርምጃ መረጋጋትን ማምጣቱን ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ላይ ገልጸዋል። ኮሎኔል ኃይለማርያም በዛሬው ዕለት ዩኒቨርሲቲው የተረጋጋ ሁኔታ ላይ እንደሆነና በፀጥታው ሁኔታ ስጋት ገብቷቸው ወደየቀያቸው ለመመለስ የፈለጉ ተማሪዎች እንደነበሩ ሳይሸሽጉ ተናግረዋል።
ነገር ግን ከአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የዞኑ አመራሮች እና ከአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም ከወልዲያ ከተማ ከንቲባ ጋር ውይይት በማድረግ ደህንነት ተሰምቷቸው ትምህርታቸውን አንዲቀጥሉ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከሌላ ስፍራ ወደ ዩኒቨርሲቲው ያቀና ተማሪ ከሃገር ሽማግሌዎች አና የአካባቢው ነዋሪዎች አለንላችሁ እያሉን ቢሆንም ጥቃት አድራሾቹ ሲጋለጡ አላየንም ከማለቱ ባሻገር አሁንም ቢሆን ስጋት እንዳልተለየውና ወደትውልድ ቀዬው የመመለስ ፍላጎቱን እንዳልቀየረ ጠቁሟል። ግጭቱን ተከትሎ የደህንነት ስጋት የገባቸው ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ለመውጣት ሲሞክሩ መከልከላቸውን ተናግረዋል።
ትላንት የአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ላይ ተገኘተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ የሰላምና ሕዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር፤ በተማሪዎች መካከል የተነሳውን ግጭት የብሔር ለማስመሰል የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች አሉ ሲሉ ተደምጠው ነበር። “በግጭቱ ተማሪዎች ተጎድተዋል። በአሁኑ ሰዓት ጉዳዩን አረጋግተነዋል። በዚህ ወንጀል ላይ የተሳተፉ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውለናል። አልፎም አማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በሙሉ ሰላም ለማደፍረስ የሚሠሩ አካላትን ለይተን እርምጃ ለመውሰድ እየተንቀሳቀስን ነው።” ሲሉም መደመጣቸው ይታወሳል::
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ትናንት በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የተፈጸመውን ክስተት አውግዟል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲስ ትናንት ከሰዓት በጽሑፍ በሰጡት መግለጫ፤ “አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ እና አስተሳሰቦቻቸውን በኃይል ህዝብ ላይ ለመጫን ጥረት እያደረጉ ነው” ካሉ በኋላ ለክስተቱ ተጠያቂ ናቸው የተባሉት ለፍርድ እንዲቀርቡ ከፌደራል እና ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር አብረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
12 ሃገራት የተሳተፉበት የግጭት አፈታት ስልጠና በአዲስ አበባ ተጀመረ
በግጭት አፈታት ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገ ስልጠና በአዲስ አበባ እየተሰጠ ይገኛል:: ስልጠናው የጃፓን መንግስት ከኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ተቋም እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር ያዘጋጀው መሆኑም ታውቋል::
ግጭትን በመፍታትና በመሠረታዊ ምንጮቹ ላይ ትኩረት ባደረገው ስልጠናው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ12 የአፍሪካ ሃገራት የተውጣጡ ተሳታፊዎች እየተካፈሉበት ሲሆን ዛሬን ጨምሮ ለ10 ተከታታይ ቀናት ይቆያል ተብሏል::
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳይሱኬ ማትሱናጋ ስልጠናው በአፍሪካ ያለውን ሰላምና ደህንነት በተሻለ ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ጠቁመው ፤ ተሳታፊዎችም በስልጠናው የቀሰሙትን ክህሎትና ዕውቀት ማጋራት እንደሚገባቸው፣ በሰላምና ፀጥታው ዘርፍ ለማሳካት ለተያዘው ዕቅድ ስኬትም ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።
አስከፊውን የትራፊክ አደጋ ለመታደግ “እንደርሳለን” ሀገራዊ ንቅናቄ ይዘጋጃል
በህዳር ወር ” እንደርሳለን“ በሚል መሪ ቃል ሀገራዊ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ንቅናቄ እንደሚካሄድ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ። ከጊዜ ወደ ጊዜ በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣውን የትራፊክ አደጋ መሠረት ባደረገ መልኩ የሚከናወን ሀገራዊ ንቅናቄ በተመለከተም የኢፌዴሪ የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል።
መተኪያ የሌለውንና ክቡር የሆነውን የሰውን ህይወት የሚቀጥፈው፣ የአካልና የንብረት ውድመትን የሚያስከትለውን የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካል ድርሻዉን እንዲወጣ ሚኒስትሯ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የመንግስት ቁጥጥርና ሕግን የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ወይዘሮ ዳግማዊት፤ የመንገድ ደህንነት ሥራን ወጥ በሆነ መልኩ የሚሠራ አንድ መንግስታዊ ተቋምም በቅርብ የሚቋቋም መሆኑንም አመላክተው፣ በተለይም በዋነኛ የትራፊክ አደጋ መንስኤዎች በሆኑት ከፍተኛ ፍጥነት፣ ጠጥቶ ማሽከርከር እና ከመንገድ መሠረተ ልማት ዲዛይን ችግሮች ዙሪያ ላይም በልዩ ትኩረት ይሠራል ብለዋል።
ከ2013 በጀት ዓመት ጀምሮ የመንገድ ደህንነት በትምህርት ካሪኩለም የሚካተተት መሆኑንና ሁለተኛ ዲግሪ በመንገድ ደህንነትና ትራንስፖርት ፐላኒንግ ለማሰጀመር ዝግጅቱ መጠናቀቁን የተናገሩት ወይዘሮ ዳግማዊት፤ የፍጥነት ገደብ በተሸከሪካሪዎች ላይ መገጠም መጀመሩን፣ የደህንነት ቀበቶ ሁሉም ተሳፋሪ እንዲያስር የሚሰገድድ ህግ የሚተገበር መሆኑን እና በአጠቃላይ ለአደጋ ማይጋለጥ ኅብረተሰብ ለመፍጠር ታስቦ በስፋት እየተሠራ እንደሆነም አረጋግጠዋል።
ኀብረተሰብ ለሀገር ብልፅግናና ዕድገት መንስኤና መነሻ በመሆኑ በቅንጅት ከተሠራ ችግሩ እየቀነሰ እንደሚሄድ የቅርብ ጊዜ አፈፃፀም ያሳያል ያሉት ሚኒስትሯ፤ በዓለም ባንክ በተገኘዉ ብድር በመንጃ ፍቃድ፣ በተሸከርካሪ ምርመራ እና የትራፊክ ቁጥጥርን ለማዘመን በልዩ ትኩረት እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል::
ለደብረ ብርሃን ቋሚ ችሎት የሚሠሩ አራት ዳኞች በአማራ ም/ቤት ተሾሙ
የአማራ ክልል ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ጉባኤ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለደብረብርሃን ቋሚ ምድብ ችሎት የሚሰሩ የ4 ዳኞች ሹመት በመስጠት እና የተለያዮውሳኔዎችን በማፅደቅ ተጠናቋል።
ሹመቱ የተሰጣቸው ዳኞች በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በሥራ ልምዳቸውና በብቃታቸው ተለይተው የተመረጡ መሆናቸውን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተወካይ ፕሬዚዳንት አቶ አብዬ ካሳሁን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።
በዚህ መመዘኛ መሠረት የዳኝነት ሹመት የተሰጣቸውወይዘሮ መሰረት መንግስቱ፣ አቶ ማህተመ ሰይፉ፣ አቶ ቸርነት ገብረጻዲቅና አቶ ማዕረግ ሰንደቁ ሲሆኑ፤ ተሿሚዎቹም ዛሬ ከሰዓት በኋላ በክልሉ ምክር ቤት ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ አቅራቢነት ሹመታቸው ትናንት የፀደቀላቸው ሰባት የካቢኔ አባላትም ዛሬ በተመሳሳይ ሁኔታ በክልሉ ምክር ቤት ፊት ቃለ መሀላ መፈጸማቸው ታውቋል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በተጓደሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እና ዶክተር አምላኩ አስረስ አባል እንዲሆኑ መመረጣቸውን ከምንጮቻችን ማረጋገጥ ችለናል።
በኬሚካል ኢንጂነሪንግ የተመረቀው ወጣት ሊስትሮ መሆን እያነጋገረ ነው
በኬሚካል ኢንጂነሪንግ ዘርፍ በዲግሪ ቢመረቅም ዕውቀቱን የሚተገብርበትን እና ሃገሩን የሚያገለግልበት የሥራ ዕድል በማጣቱ በሊስትሮነት መሠማራቱ እያነጋገረ ነው።
ቸኮለ መንበሩ የተወለደው ናበጋ ጊዮርጊስ በምትባል ቦታ ነው።በህጻንነቱ ነበር አባቱን በሞት ያጣ ሲሆን እናቱም ሌላ በማግባቷ ታዳጊው ከአያቶቹ ጋር ለመኖር ተገደደ።ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ መማር እንደሚፈልግ ለአያቱ ቢነገርም ‘ማን ያስተምርሃል?’ በሚል ውድቅ ተደርጎበታል:: በቀጣይ አጎቱ ቤት በማቅናት በእረኝነት ማገልገል ጀመረ። ጓደኞቹ ትምህርት ቤት መግባታቸው በድጋሚ “አስተምሩኝ?” ብሎ እንዲጠይቅ ምክንያት ሆነው። ካልተማረ አብሯቸው መኖር እንደማይፈልግ ገልጾ ጥያቄውን በማቅረቡ አያቱ ሁለተኛውን ጥያቄ ግን ውድቅ ሳያደርጉ ትምህርቱን እንዲጀምር አደረጉ። ሁለት ዓመት ያህል አያቱ ዘንድ ተቀምጦ ከተማረ በኋላ መግባባት ባለመኖሩ ምክንያት ከአያቱ ቤት እንዲወጣ ሆነ።
የሚረዳው ሰው ባለመኖሩ ራሱን ማስተማር ብቸኛው አማራጭ ሆነ:: አንድ ጫማ የሚጠርግ ጓደኛውን ችግሩንሲያወያየው አብሮት እንዲሠራ መከረው። አባቱ የተከሉትን ባህር ዛፎች በሃያ ብር ሸጦ ጫማ ለመጥረግ የሚረዱትን ቁሳቁሶችን ገዝቶ ሥራ ጀመረ። ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ ከትምህርት ሰዓቱ ውጭ ጫማ እየጠረገ ትምህርቱን መከታተሉን ቀጠለ።
“ለመማር የተሻለ ያግዘኛል ብዬ ያሰብኩት ሥራ ጫማ መጥረግ ነው። ግማሽ ቀን እየሠራሁ ግማሽ ቀን ለመማር ማለት ነው። የሞባይል ካርድም ሸጫለሁ። አብዛኛውን ሊስትሮ ነው የሠራሁት። በወቅቱ ኑሮም ከባድ ስላልነበረ ሊስትሮ ሠርቼ መማር እችል ነበር። አንዳንድ የሚያውቁኝ ሰዎች እያበረታቱ ‘እነእከሌ እኮ እንደዚህ ተምረው ነው ዶክተር እና መሃንዲስ የሆኑት’ እያሉ ስለሌሎች ስለሚነግሩኝ ከኋላ ያለው ስቃይ አይታየኝም ። የወደፊቱን ነበር የሚታየኝ። ” የሚለው ወጣት ፤ “ትምህርት ዋጋ ነው ያስከፈለኝ። ስቅይት ብዬ ነበር የተማርኩት። በተለይ በዓል ሲደርስ የነበረው ስሜት ይከብዳል ። ዳቦ በልቼ አድር ነበር። ለነገም ከዳቦው ለቁርስ አስተርፋለሁ። በተለይ 7ኛ እና 8ኛ ከፍል እያለሁ” ሲል የህይወቱን ውጣ ውረድ ያስታውሳል።
የደንብ ልብስ ለመግዛት ጫማ መጥረጉ ብቻ ስለማይበቃው ሥራ ፍለጋ ወደ በረሃ አቅንቷል። ሥራ ስላልነበረ ወደ ሁመራ ያደረገው ጉዞ ስኬታማ አልነበረም። ከጓደኛው ጋር አንድ ሱሪ እና ቲሸርት ብቻ ገዝተው ተመልሰዋል።
ብዙ አስቸጋሪ ወቅቶችን ቢያሳልፍም 8ኛ እና 10ኛ ክፍልን ሲያልፍ አዲስ የደንብ ልብስ ማሰፋት ስለሚያስፈልገው እንዲሁም ዩኒቨርሲቲ ሲገባ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት ፈተናው ከባድ ነበር ይላል። “እነዚህ ሦስቱ ለእኔ ልዩ ናቸው። ማለት በጣም የተጨናነቅኩባቸው ጊዜያቶች ነበሩ” በማለት ይገልጻቸዋል።
ከ3ኛ ክፍል እስከ 12ኛ ድረስ ጫማ በመጥረግ ተምሮ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚያስገባውን ውጤት በማምጣቱ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ገባ። ህይወት ግቢ [ዩኒቨርሲቲ] ውስጥ የተሻለ ነበር የሚለው ወጣት ቸኮለ “ከቀበሌ ረዳት የሌለው የሚል ማስረጃ አጽፌ በወር 200ም ሆነ 100 ብር እየተሰጠኝ፤ ክረምት ደግሞ እዛው [ዩኒቨርሲቲ] እየሠራሁ ተከፍሎኝ ከርሚያለሁ። ጓደኞቼም አብዛኛውን ነገር ይሸፍኑልኝ ነበር። ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተሻለ ነበር። ጥሩ ጓደኞች ነበሩኝ። ደብተር ጭምር ይገዙልኛል። ስመረቅም ሱፌ እንደተጀመረ ማስጨረሻ ብር ስላጣሁኝ የዶርም ልጆች አግዘው አሰፉልኝ።” በማለትም የችግር አጋርቹን በመልካም አንስቷል::
ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከገባ በኋላ የትምህርት ክፍል ለመምረጥ መስፈርት ያደረገው ቶሎ የሚያስቀጥረውንነበር። በዚህ መሠረትም ኤሌክትሪካል ምህንድስና የመጀመሪያ ምርጫው ሲሆን በሁለተኛነት ደግሞ ኬሚካል ምህንድስና። በውጤት እና በተለያዩ መመዘኛዎች መሠረት ሁለተኛ ምርጫው የሆነውን የኬሚካል ምህንድስና የትምህርት ክፍልን ተቀላቀለ።”የኢንዱስትሪ ወሬ ነበር። በሃገሪቱ ይህን ያህል መሐንዲስ ያስፈልጋል ሲባል ስለነበር ጥሩ ይሆናል ብዬ ነበር የመረጥኩት። ስለ ሥራ ዕድልም ማንም የሚነግርህ የለም። ቀደም ሲል የተዘጋጅቼ የመጣሁት ለመቀጠር ነው። . . . ሥራ አለው የለውም አልተነገረንም። የዲፓርትመንት [ትምህርት ክፍል] ምርጫ ጊዜ ሁሉም የውጭ ዲዛይን ያመጣና ኬሚካል ይሄን ይሠራል ስለሚባል በዚያ እየተሳብን ነው የምንገባው።እውነት ለመናገር እኔ የተቀረጽኩትም ሆነ ሊስትሮ ስሠራም ሳስበው የነበረው የመቀጠር ነው አባዜ የነበረኝ” የሚለው ወጣት “እሠራለሁ ብልም ገንዘብ ስለሌለኝ ሃሳቡም የለኝም። መቀጠር እና መሥራት ነው የምፈልገው” በማለት ምኞቱን በትዝታ ለቢቢሲ አስቃኝቷል።
ዩኒቨርሲቲ ሲገባ የነበረውን ደስታ ያህል መመረቂያው ሲደርስ ደ ግሞ ጭንቀቴ ጨመረ ፤ምክንያቱ ደግሞ ምን እሠራ ይሆን? ከሚል ነው የሚለው የተማረው ሊስትሮ ቀድመዋቸው ከተመረቁት ተማሪዎች ብዙዎቹ ሥራ አለማግኘታቸው ስጋቱን ከፍ አንዳደረገው ያስረዳል። “ግቢ ስገባ የተደሰትኩትን ያህል ልመረቅ አካባቢ ጭንቀቴ እየጨመረ ነው የመጣው። ምክንያቱም ነገ ደግሞ ሥራ አጥቼ ከዚያ ሊስትሮ ድጋሚ ልቀመጥ ነው። ያሰብኩት ላይሳካ ነው። ተመርቄ ቶሎ ሥራ ላልይዝ ነው። ይኼን ሳስብ ይጨንቀኝ ነበር” ሲል ተናግሯል።
በ2010 ዓ.ም ከተመረቀ በኋላ ሥራ መፈለግ ጀመረ:: “አዲስ አበባ ሥራ ለመፈለግ 3 ወር ነበርኩኝ። በየኢንዱስትሪ ፓርኩ በእግሬ እየዞርኩ ሥራ ስጠይቅ የነበረው።ወልዲያ እና አዲስ አበባ ድረስ ሄጃለሁ። አንድ ፋብሪካ ውስጥም በሃያ ዘጠኝ ብር የቀን ሥራ ጀምሬ ነበር። ግን አላዋጣኝ አለ” የሚለው ወጣት ቸኮል፤ ከመጀመሪያ ዲግሪ በታች የሚጠይቁ ሥራዎች ላይም ቢያመለክትም ቀጣይ እድገት ይጠይቃል በሚል ማመልከቻው በተደጋጋሚ ውድቅ እንደሆነበትም ገልጿል።
ሥራ አጥ ወጣቶች ተደራጅተው በየቀበሌው የሚከፈትላቸውን የሥራ ዕድል ለመጠቀም ከጓደኞቹ ጋር ቢያመለክትም “በኬሚካል ምህንድስና የተመረቃችሁ አትመደቡም’ ተብለው ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ አዎንታዊ ምላሽ ተሰጣቸው። ሥራውን ለማግኘት ዕጣ ስላልወጣለት በዕድሉ መጠቀም ሳይችል ቀርቷል።
የተወሰኑት አብሮ አደጎቹ እና የትምህርት ክፍል ጓደኞቹ ሥራ አግኝተዋል።ከወራት ሥራ ፍለጋ በኋላ ሥራ ባለማግኘቱ ያለው አንድ አማራጭ ብቻ መሆኑን አወቀ። አማራጭ ሲያጣ ሊስትሮ መሥራት ጀመረ። ጫማ እየጠረገም ቢሆን አሁንም ሥራ መፈለጉን አልተወውም። “ጫማ እየጠረግኩም ሥራ እፈልጋለሁ። የምጠርገውን ጫማ ጨርሼ ማስታወቂያ ለማየት እጓጓለሁ። ማስታወቂያ መለጠፊያው አካባቢ ስለሆንኩኝ አሁንም እፈልጋለሁ። እየዞርኩኝም ሥራ እፈልጋለሁ” ይላል።
ሥራ ያላገኘው ባለው አነስተኛ ነጥብ ምክንያት እንደሆነ ለቀረበለት ጥያቄም “ውጤቴ ለእኔ ምንም አይልም። ወደ ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት ብቻ የተላከ ይኖራል። እኔ ግን ከትምህርት በተጨማሪ የኑሮ ውጣ ውረድ ስለነበረብኝ የተመረቅኩበት ነጥብ ለእኔ ጥሩ ነበር” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
“ለእኔ ትልቅ ዋጋ ተከፍሎበት ዋጋ ያላገኘሁበት ቢኖር ትምህርት ነው ብዬ አስባለሁ” ያለው ቸኮለ ከዚህ ይልቅ በፖለቲካው አለመረጋጋት ምክንያት የመንግሥት ትኩረት ወደ ፖለቲካ መዞሩ፤ ክፍት የሥራ ቦታዎች በዝምድና መያዛቸው እና ያሉት የሥራ ዕድሎች እና የተመራቂዎች ቁጥር አለመጣጣምን በምክንያትነት ያነሳል።
” የሚያውቁኝ መምህራኖቼ ከእኔ ይልቅ እነሱ ናቸው የሚደነግጡት። ሲያገኙን አንገታቸውን ደፍተው ከእኔ በላይ በጣም ስቅቅ ብለው ይሄዳሉ።አንዳንዶቹ ደግሞ ቀርበው አይዞህ ብለው አበረታተውኝ የተወሰነ ገንዘብ ሰጥተውኝ ይሄዳሉ። ጓደኞቼ ሲያገኙኝ ሳይፈልጉም ቢሆን አሠርተው ያላቸውን ሰጥተውኝ ይሄዳሉ። ይህን ትውልድ ተስፋ ታስቆርጣለህ ከዚህ ተቀምጠህ የሚሉም ሰዎች አሉ።” በማለትም ገጠመኙን ለቢቢሲ ይፋ አድርጓል::
“ብዙ ጊዜ ባልማር አልናደድም ብዬ አስባለሁ። ይህን ያህል ዋጋ መክፈል አልፈልግም። ምን አሰቃየኝ?። አንደኛዬን የለየልኝ ጥሩ ወይም መጥፎ ሰው እሆናለሁ ብዬ የማስብበት አጋጣሚ አለ” ሲል ስሜቱን ያመላከተው ባለ ዲግሪው ወጣት ቸኮለ አሁንም ራሱን ለመለወጥ ከለጋ ዕድሜው አንስቶ የለፋበትን ሊስትሮነት አሁንም በባህርዳር ከተማ በመሥራት ላይ ይገኛል።

























