በሽብርተኝነት ታስረው የተፈቱ ዜጎች በታከለ ኡማና በመንግሥት ተከድተናል አሉ
ወያኔ በፈጠረው እና በርካታ ዜጎችን ለሰቆቃ ሕይወትና ለአካል ጉዳተኝነት በዳረገው አስከፊው ፀረ ሽብር አዋጅ ተከሰው እስር ቤት የነበሩ እና ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ክሳቸው ተሽሮ ነጻ የወጡ 300 የሚደርሱ ግለሰቦች ተሰባስበው የአዲስ አበባ የፖለቲካ እስረኞች ማኅበር መስርተው ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም ብዙ እንግልት እየገጠማቸው መሆኑ ታውቋል።
የቀድሞ እስረኞቹ የህክምና፣ የትምህርት፣ የመኖሪያ ቤት፣ የመቋቋሚያና ሌሎችም ሊሟሉልን ይገባሉ የሚሏቸውን ካሳዎች ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ቢሮ ጥያቄ ቢያቀርቡም አጥጋቢ ምላሽ እንዳላገኙ ይናገራሉ። የአዲስ አበባ የፖለቲካ እስረኞች አስተባባሪ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ ዳሰማ ሶሪ ማኅበሩ 2010 ዓ. ም. መጨረሻ አካባቢ አብዛኞቹከእስር ከተፈቱ በኋላ ምንም የሚሰባሰቡበት ወይም በመንግሥት በኩል የተደረገላቸው ነገር ባለመኖሩ ማኅበሩ ሊመሠረት እንደቻለ አስታውቋል።
“ከተለያየ ቦታ ሰብስበው አሰሩን፤ ከዓመታት በኋላ ውጡ ተብለን፣ ወጣን። ሜዳ ላይ ነበር የተበተነው። 2011 ዓ. ምመስከረም አካባቢ የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት ፒያሳ አካባቢ መሰባሰብ ጀመርን። በማዕከላዊ ቆይታችን የተፈጸመብብን ግፍ አለ ፣ የተዘረፍነው ንብረትም እንዲሁ። ሌሎችም የመብት ጥያቄዎች አሉን ብለን ተሰባሰብን ፣ ብዙ መጠለያ የሌላቸው አሉ፤ እስር ቤት ለዓመታት የቆዩ ናቸው። ቤተሰቦቻቸው ተበትነዋል።” የሚለው የኮሚቴው ዋና ጸሐፊ ዳርሰማ ሶሪ ፤ “እነዚህን ወሳኝ ነገሮች እንዴት ከመብት አኳያ መጠየቅ አለብን? ብለን የተለያዩ ጠበቆችን አነጋገርን። ጥያቄያችንን ይዘን ጠቅላይ ሚንስተር ቢሮ ሄድን። ጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ያሉ ሰዎች ማመልከቻችንን ተቀበሉና አዲስ አበባ ከንቲባ ቢሮ ሂዱ በማለት ወደ እዛ መሩን” ሲል እየደረሰባቸው ያለውን እንግልት ለቢቢሲ ገልጿል።
“ከንቲባ ቢሮ ለሦስት ወራት ጥያቄያችንን ያለማቋረጥ አቀረብን። መጨረሻ ላይ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ጥር 26 ካፒታል ሆቴል ፕሮግራም ይዘውልን ጥያቄያችንን አሰማን። ጥያቄያችንን ሙሉ በሙሉ ተቀብለው፤ ያቀረባችኋቸው ጥያቄዎች በዓለም ዐቀፍ የሰብአዊ መብት ሕግም፣ በሕገ መንግሥታችንም አግባብ ያላቸው ጥያቄዎች ናቸው፤ ጥያቄዎቻችሁ በአስቸኳይ ይመለሳሉ አሉን። በናንተ በኩል ማድረግ ያለባችሁን አድርጉና አቅርቡልን የሚል ምላሽ ሰጡን። ከዛ እያንዳንዱ የፖለቲካ እስረኛ የት እንደታሰረ፣ መቼ እንደታሰረ፣ የተፈረደበትን ፍርድ፣ የደረሰበት በደል፣ የትምህርት መረጃውን እና የቤተሰብ ሓላፊ መሆኑን በ1215 ገጽ ጽፈን ለከንቲባው ቢሮ አስገባን።” ያለው ዳርሰማ ከንቲባው ቃል የገቡላቸውን እስካሁን ሊተገብሩ አለመቻላቸውን ይፋ አድርጓል::
ተፈቺ እስረኞቹ በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ በነበርንበት ጊዜ ተገደን የሰጠናቸው ቃሎች፣ አሻራ እና የተሰጠብን ፍርድ አለ። ይህ መንግሥት በወቅቱ ይቅርታ የጠየቀበትና “እኛ ነን ሽብርተኛ” ብሎ ያመነው በመሆኑ፤ ሙሉ በሙሉ አሻራችን እንዲሰረዝልን፣ የተፈረደብን በሽብር በመሆኑ ሥራ ለመግባት በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ ሙሉ በሙሉ እንዲነሳልን የሚሉትን ነጥቦች በቀዳሚነት ከመጠየቃቸው ባሻገር በማዕከላዊ የተወሰደባቸው ንብረትም እንዲመለስ፣ በተጨማሪም በማዕከላዊ፣ በቃሊቲ፣ በቂሊንጦም ሆነ በሌሎች እሥር ቤቶች ውስጥ በደረሰባቸው ድብደባ አካላቸው የጎደለ፣ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ስላሉ ህክምና የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻችም ጠይቀዋል።
ትምህርትን በተመለከተ በዩኒቨርስቲና የተለያዩ ተቋሞች ውስጥ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ እና ያላግባብ ያቋረጡ፣ ትምህርታቸውን የሚቀጥሉበት መንገድ እንዲመቻችላቸውም የጠየቁ ሲሆን፤ እስር ላይ የነበሩ የተለያዩ የቤት እድሎችን እንዳያገኙ በመደረጋቸው የመጠለያ ጉዳያቸውንም በከንቲባው በኩል ለመንግሥት አቅርበዋል:: መቋቋሚያን በተመለከተ እስር ላይ በነበሩበት ወቅት ቤተሰቦቻችን ስለተበተኑ፣ አሁንም ምንም ሥራ የሌላቸው ሰዎች ስላሉ ለነሱ ከተዘዋዋሪ ፈንድ መቋቋሚያ የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻችላቸውም አማራጭ ሰጥተው ነበር።
በተጨማሪም በ27 ዓመታት በኢሕአዴግ መንግሥት ሕይወታቸው ያለፈ ብዙ ሰዎች በመኖራቸው፣ እነዚህ አጽማቸው ተሰብስቦ አንድ ቦታ እንዲቀበርና የመታሰቢያ ሀውልት እንዲቆምላቸው በሽብርተኝነት ተጠርጥረው በእስር ሲማቅቁ የነበሩት ወገኖች ተደራጅተው መጠየቃቸው ተሰምቷል።
“ጥር 26 ከንቲባው በሰበሰቡን ወቅት አራት ጠበቆች ከኛ ጋር ተገኝተው ነበር። ጠበቃ አዲስ መሐመድ፣ ጠበቃ ተማም አባቡልጉ እና ሌሎችም ተገኝተው ከሕግ አንጻር አስፈላጊውን ትንታኔ አቅርበዋል። አብዛኞቹ የፖለቲካ እስረኞች ያ ነገር ሲፈጸምባቸው የነበረው፣ ሲጎዱ የነበሩት ተገደው ነው፤ ዓለም አቀፍ ሕጉም ያግዛቸዋል። ሕገ መንግሥቱ ላይም የእያንዳንዱ ዜጋ መብት እና የአካል ደህንነት የተከበረ ነው፤ መንግሥትምግዴታ አለበት ” ያሉት አቶ ዳርሰመረ ሶሪበመንግሥት ደረጃ ያሉ ሰዎች የሰውን አካል አጉድለው፣ የሰውን ንብረት ዘርፈው፣ ሰውን እንደ ዜጋ እንዳይኖር ከልክለውት፤ እነሱ በሕግ ሳይጠየቁና ይሄ ሰው ከተፈታ በኋላም ሕጋዊ ድጋፍ ወይም ሽፋን እንዳያገኝ ማድረግ አግባብ ባለመሆኑ ምላሽ ይገባቸዋል ፤ ወደፊት በሕግም እንሄድበታለን። አሁንም አንዳንድ የሕግ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ጊዜው ሲደርስ በይፋ እንገልጻቸዋለን።” ሲሉ የሄዱበትን ህጋዊ አግባብ በግልፅ አስቀምጠዋል::
“ከሚገባው በላይ ነው የተመላለስነው። መጀመሪያ ላይ ያቀረብናቸው ሰነዶች ኮፒ ጠፍቷል ተባለ። እንደገና ሌላ አዘጋጅተን ነው የሄድነው። ቤት የሌላቸው ዝርዝር አቅርቡ ተብለን፤ አዲስ አበባ ውስጥ ነዋሪ መሆናቸውን፣ ቤት እንደሌላቸው ከሚኖሩበት አካባቢ አጽፈው ያመጧቸውን ደብዳቤዎች ኮፒ ሰጥተን፤ በድጋሚ ጠፋ ከተባለ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ ነው ያስገባነው። ሆን ተብሎ ጥያቄያችንን ላለመመለስ የሚደረግ ጥረት እንደነበረ ነው የምረዳው። ትምህርትና ህክምናን በተመለከተ ጽፈንላችኋል ኑና ደብዳቤ ውሰዱ ብለውን ነበር። ሰው ግን ምን በልቶ ይማራል? ምን እየሠራ ይማራል? ቢሳካም እንኳን ደብዳቤውን ሲሰጡን የትምህርት ሰዓቱ አልፏል።” በማለት ለጥያቄያቸው ምላሽ ለማግኘት እየተጉላሉ መሆናቸውን ተወካዮ አብራርተዋል::
“አብዛኞቹ ተቋሞች የምዝገባ ጊዜያቸው ተጠናቋል። ትምህርትም ተጀምሯል። አምና በክረምት የጠየቅነውን ጥያቄ፤ ላለፉት ዘጠኝ ወራት ሲንከባለል የነበረ ጥያቄ፤ አሁን ጥቅምት ላይ ነው ለህክምናና ትምህርት ጽፈንላችኋል ያሉት። መቋቋሚያን በተመለከተ እያንዳንዱ የፖለቲካ እስረኛ በአምስት በአምስት ተደራጅተው፣ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ነድፈው እንዲያመጡ ተደርጎ፤ ፕሮፖዛል ሠርተው ካቀረቡ በኋላ ከተዘዋዋሪ ፈንዱ ላይ እንዲመራ ተደርጎ ነበር። ቢያንስ ቢያንስ ሥራ ሠርተው ሌሎች ችግሮቻቸው ቀስ እያሉ ይመለሳሉ ብለን እዚህ ጉዳይ ላይ አጣድፈናቸው ነበር። በኋላ ግን የጻፉልን ደብዳቤ አነስተኛ የሥራ እድል እና ፈጠራ እንዲሁም አዲስ ብድርና ተቋም በአግባቡ እንዳይረዱን የሚያደርግ ነው።” ሲሉም የበደሉን ጥልቀት ገሀድ አውጥተዋል::
ተዘዋዋሪ ፈንዱ የተፈቀደው እድሜያቸው ከ34 ዓመት በታች ለሆኑ ነው። ከንቲባው ያሉት፤ ምንም ይሁን ምንም በልዩ ትዕዛዝ፣ በልዩ ሁኔታ እንድትስተናገዱ ይደረጋል ነበር። በልዩ ሁኔታ የምንስተናገድ ከሆነ የእድሜ ገደቡ ለኛ ተነስቷል ማለት ነው። እኛጋ እድሜው ከ21 እስከ 78 ዓመት የሚደርስ ሰው ነው ያለው። ደብዳቤውን ሲጽፉልን ግን ተባበሯቸው የሚል እንጂ የእድሜ ገደቡ መነሳቱን የሚመለከት ምንም ነገር አልጻፉልንም። ስንደራጅ ደግሞ ሁሉም በእድሜ ከሚመጥነው ጋር ስለሆነ የተደራጀው ለመምረጥ አስቸጋሪ ነው በማለት ያለውን የህግ መፋለስ አሳይተዋል።
“ደብዳቤው ከተበተነ በኋላ አስፈላጊውን ትብብር ያደረጉልን ሰዎች አሉ። አነስተኛና የሥራ እድል ፈጠራ ላይ የሚገኙ ሰዎች፤ በአንድ ሳምንት 141 ሰው የተደራጀበትን ወደ 30 ምናምን ፕሮጀክት አጥንተው፣ የሚስተካከለውን አስተካክለው ወደ ታች እንዲወርድ አደረጉልን። ክፍለ ከተማ ስንሄድ፤ ታች ውረዱና በወረዳ ላይ ተደራጁ እንጂ እኛ አናደራጃችሁም ብለው መለሱን።” ያሉት አቶ ዳርሰማ ሶሪ፤ “ከላይ ፕሮጀክቱ ተሠርቶ አልቆ፣ ፕሮጀክቱ ታርሞ፣ ተስተካክሎ ነው የመጣው፤ እንዴት ከታች እንደራጃለን? ስንል ምንም የምናውቀው ነገር የለም ብለው መለሱን። ደብዳቤያችን በዚህ ምክንያት ተቀባይነት አጣ። ከዛ ደብዳቤውን አስተካክሉልን ብለናቸው፤ ደብዳቤው ተስተካክሎ ሲሰጠን ደግሞ ለተዘዋዋሪ ፈንዱ የተመደበው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ አልቆ ነው ያገኘነው። አልቋልና ድጋሚ ገንዘብ እስኪመጣ ጠብቁ ነው የተባልነው። ለዓመታት በእስር ሲማቅቅ የነበሩ ሰው፣ ቤተሰቦቹ የተበተኑ፣ አካሉ የጎደለ ሰው ነው ያለው። ይህን ሰው ለመርዳት ዳተኛ ከመሆን የመነጨ እንጂ ፍላጎቱ ቢኖር ኖሮ የአንድ እና ሁለት ሳምንት ሥራ ነበር።” ሲሉ በመንግሥት መዘንጋታቸውን ተናግረዋል::
የሰኔ 15ቱ የባለሥልጣናት ግድያ ተጠርጣሪዎችን ፍርድ ቤቱ ዛሬም በቀጠሮ ሸኛቸው
በባህር ዳሩ የሰኔ 15ቱ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና የፀጥታ ኃይሎች ግድያ ጋር በተያያዘ በ”እነ ሻምበል መማርጌትነት” መዝገብ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ፣ የክስ መቃወሚያቸውን በጽሑፍ ለፍርድ ቤቱ አቀረቡ:: ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ 55 ግለሰቦች ላይ የክስ ማመልከቻ (ቻርጅ) ከተደመጠ በኋላ ነበር ለዛሬ ቀጠሮ ተይዞ ነበር።።
በቀጠሮው መሠረት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ የተከሳሾችን የጽሑፍ የክስ መቃወሚያ ለመቀበል፤ ባለፈው ችሎት በህመም ምክንያት ያልቀረቡ አንድ ተከሳሽን የክስ ማመልከቻ ለማንበብ፣ እንዲሁም ባለፈው ችሎት ያልቀረቡ ሌሎች ተከሳሾችን ፖሊስ ስለማቅረቡ ለማረጋገጥ ነበር ለዛሬ ቀጠሮ የተሰጠው።
ቀደም ሲል በነበረው ቀጠሮ በህመም ምክንያት መቅረብ ያልቻሉትን 29ኛ ተከሳሽ ማንነትን ከተቀበለ በኋላ፣ በፍርድ ቤቱ ያልተገኙ ተከሳሾችን በተመለከተ ፖሊስ አለማቅረቡን አስታውቆ ለሚቀጥለው ቀጠሮ እንደሚያቀርባቸው ለችሎቱ አስረድቷል። የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው የክስ መቃወሚያቸውን ለፍርድ ቤቱ በጽሑፍ አቅርበዋል።
ክሶች ሊደራረቡ እንደማይገባ፤ በቴክኒክ ማስረጃነት የቀረቡ የስልክ ልውውጦች ባለመቅረባቸው የድምጹን ማንነት ለመለየት አስቸጋሪ መሆኑን፤ እንዲሁም የንብረት ውድመትን በተመለከተ አለ የተባለው የሲዲ ማስረጃ አለመቅረቡን እና በአማራጭ የቀረበው ክስ ከተደነገገው ክስ እና ፍሬ ነገሩ ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ተገቢነት የላቸውም የሚል መቃወሚያ የተጠርጣሪ ጠበቆች በዝርዝር ማቅረባቸውን ሰምተናል።
የ3ኛ፣ 11ኛ፣ 12ኛ፣ 13ኛ እና 52ኛ ተከሳሾች የባንክ ሒሳብ በምርመራ ወቅት የታገደ መሆኑን ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ ገልጸው፤ በዚህ ምክንያት ተጠርጣሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው ችግር ላይ በመውደቃቸው፤ የሒሳብ ቁጥሮቹ ከክሱ ጋር ተያያዥነት የሌላቸው እና በማስረጃነት ያልቀረቡ መሆናቸውን በመጠቆም እገዳው እንዲነሳላቸው ፍርድ ቤቱንጠይቀዋል።
ይህንን የጠበቆችን ቅሬታ የተመለከተው ፍርድ ቤትም ጠበቆች አቤቱታቸውን እግዱን ለሰጠው ፍርድ ቤት እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ ፤ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ያልቀረቡ ተጠርጣሪዎችን በሚቀጥለው ችሎት እንዲያቀርብ አዟል። በተከሳሾች የክስ መቃወሚያ ላይምዓቃቤ ህግ አስተያየት ያቅርብ ያለው ፍርድ ቤቱ፣ ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው ዋስትና የማያሰጥ በመሆኑ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ወስኗል። ይህን ተከትሎ የዓቃቤ ህግን አስተያየት ለመቀበልም ለጥር 6/2012 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።
በነሻምበል መማር ጌትነት መዝገብ ተጠርጥረው በማረሚያ ቤት ከሚገኙት መካከል ከተራ ቁጥር 1 እስከ 14 ስማቸው የተጠቀሱ ተጠርጣሪዎች የሰኔ አስራ አምስቱን የአማራ ክልል መንግሥት ግልበጣ በማደራጀት፣ በመምራት የክልሉን ከፍተኛ ባለስልጣናትና የፖሊስ አባላትን በመግደልና በማቁሰል ተሳታፊ መሆናቸውን የሚያመለክት ክስ እንደቀረበባቸው አይዘነጋም፡፡
ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ ከኖርዌይ አቻቸው ጋር ተወያዮ
ትናንት በአስደማሚ ንግግራቸው በዓለም ሕዝብ ፊት ደምቀው የታዮት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኖርዌዩ አቻቸው ኤርና ሶልበርግ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
በውይይታቸው ላይ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲን በማጠናከር እና የተጀመረውን የለውጥ ሂደት በማስቀጠል ላይ እያከናወነች ባለው ሥራ ላይ መምከራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል። በምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ሰላምና መረጋጋት ላይም ተወያይተዋል ነው የተባለው።
የኢትዮጵያን የባህር ኃይል በአቅም ግንባታ ድጋፍ ለማጠናከር፣ ኢትዮጵያውያን ሴት አመራሮች በፖለቲካ አመራር ላይ ልምድ እንዲለዋወጡ ለማስቻልና የእውቀት ሽግግር ለማካሄድ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ ላይ ድጋፍ ለማድረግ መሪዎቹ ከመግባባት ላይ ደርሰዋል።
በተያያዘ ዜና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኖርዌይ ፓርላማ ፕሬዚዳንት ቶን ትሮን እና በአኒከን ሁይትፊል ከሚመራው የውጭ ጉዳይና መከላከያ ቋሚ ኮሚቴ ጋርም መወያየታቸው ታውቋል።
በዚህ ውይይት በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ባሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ የልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ገልጿል።
ምርጫ ቦርድ ለዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕውቅና ሰጠ
ቀጣዮን ሀገራዊ ምርጫ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ለማካሄድ ሽር ጉድ እያለ የሚገኘው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ መስጠቱን ይፋ አድርጓል።
በወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ የሚመራው ቦርድ በፌስ ቡክ ገጹ ዛሬ ባወጣው መረጃ መሠረት በምዝገባ ሂደት ላይ ለነበሩ 9 ፓርቲዎች እውቅና ሰጥቻቸዋለሁ፣ በዚህም መሠረት ቀጣዮን ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ ይችላሉ ሲል አስታውቋል።
ከላይ በተገለጸው መንገድ ህጋዊ ዕውቅና ያገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች:-
1. አፋር ህዝባዊ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢህፍዴፓ)
2. አፋር ህዝብ ነጻነት ፓርቲ (አህነፓ)
3. ጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋዴፓ)
4. ሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሞዴፓ)
5. ቁጫ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁህዴፓ)
6. ካፋ አረንጓዴ ፓርቲ (ካአፓ)
7. ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ)
8. ዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን) እና
9. ሱማሌ አንድነት ፓርቲ (ሱአፓ) እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል።
ኢትዮጵያ የዘረ – መል ምርመራን በሀገር ውስጥ ልትጀምር ነው ተባለ
እስካሁን ድረስ በውጭ ሀገራት ይደረጉ የነበሩ የዘረ-መል ምርምራዎችን በሀገር ውስጥ ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት እተደረገ መሆኑ ተገለጸ።
ቀደም ሲል የሰው እና የዕፅዋት ዘረ-መል ምርመራ ለማድግ የሚያስችል አቅም ሀገር ውስጥ ባለመኖሩ ፣ ኢትዮጵውያን ተመራማሪዎች ሥራዎቻቸውን ወደ ውጭ በመላክ ለማስመርመር ይገደዱ እንደነበር አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት የዘር-መል ምርመራን በሀገር ውስጥ ለማድረግ የሚያስችለውን መሳሪያ “አሊያንስ ግሎባል ግሩፕ” ከተሰኘ ድርጅት በድጋፍ መልክ ማግኘቱን አስታውቆ ፤ በዚህ መሰረትም በቀጣይ ምርመራው በሀገር ወስጥ የሚከናወን መሆኑን አስታውቋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ጀማል በከር የዘረ-መል ምርመራ ሀገር ውስጥ ለማድረግ የሚያስችል አቅም መፈጠሩ የሀገር ውስጥ ተመራማሪዎችን ወጪና ድካም እንደሚቀንስ፣ ብሎም በዘርፉ የሚደረገውን ምርምር እንደሚያነቃቃው ነው ዕምነታቸውን የገለፁት።
የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች የዘረ-መል ምርመራ ለማድረግ የሚያወጡትን ወጪ በመቀነስ የውጭ ምንዛሬ ፍለጋንም እንደሚያስቀር ተስፋ ተደርጎበታል። ስምምነቱን የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር ካሳሁን ተስፋየ (ዶ/ር) እና “የአሊያስ ግሎባል ግሩፕ” ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ታመር ድግዲ መፈራረማቸው ታውቆል።
የዘረ-መል ምርመራ ማድረጊያ መሳሪያው ለምርመራ ወደ ውጭ የሚላኩ ዘረ-መሎች (የሠው፣ የእንስሳትና የዕፅዋት) የመሰረቅ አደጋ እንዳይገጥማቸው የነበረውን ስጋትምእንደሚቀርፍ ታምኖበታል:: የ”አሊያንስ ግሎባል ግሩፕ” 17ኛ ቢሮውን፣ “አሊያንስ ግሎባል ግሩፕ አቢሲኒያ” በሚል አዲስ አበባ ከፍቷል።
ኢትዮጵያዊቷ ሎዛ አበራ ትናንት በማልታ ፕሪምየር ሊግ ሰባት ጎሎችን አስቆጠረች
የመጀመሪያዋና ብቸኛዋ አውሮፓ የምትጫወተው ፕሮፌሽናሏ ለውዛ አበራ ትናንት በማልታ የሴቶች ሊግ ደምቃ አምሽታለች::
ለማልታው “ቢርኪርካራ” እግር ኳስ ቡድን የምትጫወተው ኢትዮጵያዊቷ ሎዛ አበራ ቡድኗ ትናንት ከሂበርኒያንስ ጋር ባደረገው ጨዋታ ላይ ሰባት ግቦችን በስሟ አስመዝግባለች።
ፍፁም በጨዋታ የበላይነት ቢርኪርካራ ክለብ ተጋጣሚውን 17 ለ 0 ያሸነፈ ሲሆን ለውዛ የምትጫወትበት ይህ ቡድንበ19 ነጥብ ሊጉን በአንደኛነት እየመራው ይገኛል።
ሰባት ልጆች ላፈሩት እናት እና አባቷ አምስተኛ ልጅ የሆነችው ሎዛ አበራ ተወልዳ ያደገችው የከንባታ ጠምባሮ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ዱራሜ ነው።
ሠፈር ውስጥ ካሉ ወንድ እኩዮቿ ጋር እየተጋፋች ከልጅነቷ ጀምሮ ኳስን ተጫውታለች። የሎዛ ፕሮፌሽናል ኳስ ተጫዋችነት ጉዞ የተጀመረው የከንባታ ዞንን ወክላ ስትጫወት ባይዋት መልማዮች አማካይነት መሆኑ ይነገራል::
በፍጥነት የሐዋሳ ሴቶች እግር ኳስ ቡድንን ተቀላቅላለች::ከሐዋሳ ጋር ዋንጫ ባታነሳም ቡድኑ ውስጥ በቆየችባቸው ሁለት ተከታታይ ዓመታት የክለቡ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ እንደነበረች የጨዋታ ሪከርዷ ያሳያል።
ሐዋሳን ከለቀቀች በኋላም በደደቢት አራት ዓመታትን ያሳለፈችው ሎዛ በሁሉም ዓመታት በተከታታይ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆና ከመጨረሷ ባሻገር ፤ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን ሆናለች ለእውቅና ካበቃት ደደቢት ጋር።
በዚህ ወቅት በማልታ ደሴት ከፍተኛ ሊግ ላይ ለሚሳተፈው ቢርኪርካራ የምትጫወተው ሎዛ በትዊተር ገጿ ላይ ባሰፈረችው መልእክት ”ዛሬ በነበረን ጨዋታ በማልታ ሊግ ላይ በአንድ ጨዋታ ብቻ ሰባት ጎል በማስቆጠር ሌላ ታሪክ መጻፍ እና መሥራት ስለቻልኩ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ላይ በአንድ ጨዋታ ብቻ ዘጠኝ ጎል አግብቼ ነበር” ስትል ደስታዋን አስፍራለች።
ከፍተኛ የሆነ መነቃቃት በታየበት የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ፈክታ ለመውጣት የቻለችውና በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥም ስኬታማ የሆነችው የደቡቧ ፈርጥ ሎዛ አበራ በአውሮፓ መድረኮች መድመቋ ለሌሎች የሀገሪቱ ሴት ተጫዋቾች የፕሮፌሽናል ተጫዋችነት በር ይከፍታል ተብሎ ታምኖበታል::