ሰው ሲሞት “እኔ ለራሴ፣ እኔ ለራሴ” እያሉ የሚያለቅሱ ሰዎች አሉ። አባባሉ በጣም ይማርከኛል። ሰዎች ግላዊ እና ማኅበራዊ እንስሶች ናቸው። ለግል ጥቅማቸው ማኅበራዊ ኑሮ ይመሠርታሉ። ማኅበራዊ ኑሮ በጎደለ መሞላላት ነው። ማኅበራዊ ኑሮ ባይኖር ኖሮ፥ በምድር ላይ ካሉ ሀብት ንብረቶች፣ መዋቢያው፣ አልባሳቱ ሁሉ አንዳቸውም ከመሠረታዊ ቁርና ሀሩር መከላከል፣ እንዲሁም ከርስ ከመሙላት የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም ነበር። የሆነ ሆኖ ማኅበራዊ ኑሮ አለ፤ ሰዎችም በየማኅበራቸው ተቀባይነት ኖሯቸው ተከብረው የመኖር ፍላጎት አላቸው። እናም በዚህ ባሕል አንድ ሰው ሲሞት “እኔ ለራሴ፣ እኔ ለራሴ” እየተባለ የሚለቀሰው፥ በጎደለን የሚሞላ አንድ ሰው በመጉደሉ ነው ብዬ አምናለሁ። ትግልም እንደዛው ነው፤ እኔ ለራሴ።
“ለሕዝቤ ብዬ፣ ለወገኔ ብዬ” የሚል መፈክር ስሰማ እንደ ግብዝነት ነው የምቆጥረው። በርግጥ ሰዎች ለራሳቸው ብለው የሚያደርጉት ትግል (ትግሉ የነፃነት፣ የእኩልነት /የእኩል ክብር/ ከሆነ) ለሌሎችም ሊደርስ ይችላል። ነገር ግን ዘርፎ ለመክበር፣ ገድሎ ለመኖር ከሆነ ያው ለራስ ከሚደረጉ ትግሎች በሙሉ የከፋ ትግል ይሆናል።
የሆነ ሆኖ ሰዎች በውስጣቸው የገነቧቸው ወይም ማኅበረሰባቸው የገነባባቸው እሴቶች አሏቸው። እነዛን እሴቶች መሠረት አድርገው ሲታገሉ እስከሞት ሊደርሱ ይችላሉ። “ለራስ መሞት?” የሚል ጥያቄ ሊመጣ ነው። ማርቲን ሉተር ኪንግ (ትንሹ) “ሊሞቱለት የሚፈቅዱለት ዓላማ የሌላቸው ሰዎች ለመኖር ብቁ አይደሉም” ይላል ነገሩን በአንድ ዓረፍተ ነገር ሲጠቀልለው። “ሥም ይሸታል ከስብ”፣ “ሥም ከመቃብር በላይ ይውላል” እያሉ ለሚተርቱ ሐበሾች “ለራስ ሲሉ” የመሞት ነገር አይጠፋቸውም።
ይህንን ሁሉ ለመዘብዘብ የዳረገኝ የሰሞኑ ሙግት ነው። ፌሚኒስቶቻችን ላይ ከሰሞኑ እየተሰነዘሩ ያሉ ሙግቶች “የምትደፈር ሴት ባለችበት አገር፣ ያለዕድሜዋ የምትዳር ሴት ባለችበት አገር… ወዘተ. አንቺ ሆዬ ተለከፍኩ፣ ወይዘሪት፣ ወይዘሮ ተባልኩ ብለሽ ቅር ይልሻል” የሚሉ “ትችቶች” ሲደጋገሙ ነበር። ለነገሩ ሰሞኑን ስኬታማ ዘመቻዎች ስለነበሩ “ትችቶቹም” በረቱ እንጂ፥ ቀድሞም ነበሩ። ከሁለት ሦስት ሳምንታት በፊት፣ አክቲቪስት ደረጄ ገረፋ “እናንት የከተማ ሴቶች ግን በገጠር ሴቶች ችግር ካፒታል እያፈራችሁ ነው ወይ?” የሚል (ቃል በቃል አላስታወስኩት ይሆናል) ጥያቄ አንስቶ ነበር። መሠረቱ ተመሳሳይ ነው። “ትችቱ” በስርዓተ ፆታ ጉዳይ አይወሰንም። “አራት ሚሊዮን ሰው በሚራብበት አገር እናንተ፣ የብሔር እኩልነት፣ ሊበራሊዝም፣ ሶሻሊዝም ትላላችሁ” ሲባል ነው የኖረው።
“የትልልቆቹ” እና “ትንንሾቹ” ችግሮቹ ሥረ አንድ ነው ይለያያል የሚለውን ወደ ጎን ብንተወው እንኳ፥ ለዘረፋ እና ለተረኛ ጨቋኝነት ከሚደረጉ ትግሎች በቀር ሌሎቹ የግል ጭቆናን፣ መገለልን፣ መበደልን በመቃወም የሚደረጉ ትግሎች ሁሉም ሰዎች ነፃነት እና ክብር እስኪቀናጁ ድረስ ይጥላሉ እንጂ ከፊል ሰዎች ብቻ ተመርጠው ነጻ የሚወጡበት ዘዴ የለም። ይሁን እንጂ እዚያ ክርክር ውስጥ አሁን አንገባም። ርዕሳችን “ለማን ነው የምትታገዪው?” ነው የሚለው።
ሰዎች ወደ ምድር ሲመጡ ፈቃዳቸው ተጠይቆ አይደለም። ነገር ግን ከሰውነታቸው ጋር አብሮ የሚመጣ በክብር የመኖር ፍላጎት አለ። ፈቃዳቸው ሳይጠየቅ ከመኖር ጉጉት ጋር ወደ ምድር የመጡ ሰዎች ሲጀመር ይህንን የተበላሸ ማኅበራዊ ኑሮ እና መስተጋብር ለማስተካከል የመታገል ግዴታ የለባቸውም። ነገር ግን ሰዎች ከመኖር ጎን በክብር መኖር ነው እና ዓላማቸው፥ ሰብኣዊ ክብር የጎደለውን ማኅበራዊ ግንኙነት እታገላለሁ ብለው ከተነሱ፥ እሰዬው! የሚታገሉት ለራሳቸው ሰብኣዊ ክብር ነው! የትግላቸው ፍሬ ለእኛ ከተረፈ አሁንም እሰዬው! ነገር ግን “እነ እከሌ ባሉበት፥ እናንተ ምናችን ተነካ ብላችሁ ነው የምትንጫጩት” (‘የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ’ እንደሚሉት) ያለው አባባል እኛን አይመጥንም።
ለመዝጊያ ያክል አንድ ተረት ላውራ። ዝንጀሮዋ እሾህ ሰውነቷ ላይ ተሰካክቶ ሳለ፥ “ከየት ጀምሮ ይነቀልልሽ?” ስትባል “መጀመሪያ የመቀመጫዬን” አለች ይባላል። እና መጀመሪያ ለራስ!

























