የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ታህሳሥ 22 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ታህሳሥ 22 ቀን 2011 ዓ.ም

ከኦሮሚያ በሚመጡ የተደራጁ ሰዎች የተወረረው የአ/አ መሬት ላይ እርምጃ ሊወሰድ ነው

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢጅነር ታከለ ኡማ ህገወጥ የቤቶች ግንባታ ላይ በሚወሰደው እርምጃ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በአዲስ አበባ መጣ የሚባለውን አገራዊ ለውጥና የእርሳቸውን የከተማዋ ከንቲባ ሆኖ መሾምን ተከትሎ ባለፉት 20 ወራት ከተለያያዮ የኦሮሚያ ከተሞች እየተደራጁ የሚመጡ የኦሮሞ ተወላጆች የአዲስ አበባ ዙሪያና የከተማዋ የተለያዮ ክፍት ቦታዎችን በመቀራመት አጥረው መቀመጣቸው በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ ሲያስነሳ ሰንብቷል።

እስካሁን ድረስ በቀጠለውና ውስጥ ውስጡን “የፊንፊኔ ኬኛ”ን ፖለቲካ ባነገበው የሕገ ወጥ መሬት ወረራ ላይ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃንና  የከተማው ነዋሪዎች ጥያቄ ቢያቀርቡም የታከለ ኡማ መስተዳደር አንድ ዓመት ከመንፈቅ በላይ ምንም ምላሽ ካለመስጠቱ ባሻገር አንዳችም እርምጃ አልወሰደም።

ባሳለፍነው ሳምንት ራሱ በመካኒሳና በቦሌ ሚካኤል አካባቢ ያሉ ቦታዎች ላይ ሕገወጥ ግንባታ ሲካሄድና ከየት እንደመጡ የማይታወቁ የኦሮሞ ተወላጆች የመሬት ወረራ ሲያካሂዱ ፖሊስ ምንም ዓይነት እርምጃ አለመወሰዱንና ሰዎቹም ባጠሩት ቦታ ላይ ተደላድለው መቀመጣቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢትዮጵያ ነገ ዘጋቢ ገልጸዋል።

ዛሬ የህገወጥ ግንባታዎችን በተመለከተ የተደረገው ጥናት እና ህግን የማስከበር እርምጃው ማስፈጸሚያ መንገዶች ዙሪያ ተደርጓል የሚባለውን ውይይትም ለይስሙላ የተደረገ ነው በሚል እንደሚጠራጠሩት የገለጹት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የታከለ ኡማ አስተዳደር በቀጣዮ ምርጫ በከተማዋ እንደማያሸንፍ መገንዘቡን ተከትሎ አዲስ አበባን በመሬት ወረራ የራሱን ደጋፊዎችና ጽንፈኛ ብሔርተኝነት ላይ የተመረኮዘን ፖለቲካ በማራመድ እየተበቀለን ነው ሲሉ ይከሳሉ፡፡

በቅርብ ጊዜያት እየተስፋፋ የመጣውን ህገወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት እያደረገ ሲሆን በቅርብ ቀናትም ወደ ትግበራ እንደሚገባ ከተማ አስተዳደሩ እየገለጸ ይገኛል፡፡ እርምጃው በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ 116 ወረዳዎች ላይ የሚወሰድ ሲሆን የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ፖሊስና የከተማዋ አጎራባች ወረዳዎች ይሳተፋሉ ነው የተባለው።

በየወረዳው በህገወጥ መልኩ የተገነቡ ቤቶችን የመለየት ስራም እየተሠራ እንደሚገኝ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ቢጠቁምም የታከለ ኡማ አስተዳደር እርምጃ ለመውሰድ እስካሁን የዘገየንበትን ምክንያት አላብራራም::

ከውይይቱ በኋላ በጉዳዩ ላይ መግለጫ የሰጡት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አራጋው ህገወጥ ግንባታዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ህግን ከማስከበር ጋር ብቻ የተያያዘ እንደሆነ ጠቁመው፤ ከዚህ በኋላ በሚኖሩ ጊዜያትም የከተማ አስተዳደሩ ቀድሞ የመከላከል ሥራዎች ላይና ህገወጦች ላይ ጠንካራ እርምጃ የመውሰድ ተግባሩ አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ገልጸዋል።

ከህገወጥ ግንባታው ጋር የተያያዙ የሥራ ሓላፊዎችም ይሁን የተለያዩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ እንዲሁም ከህገወጥ ግንባታዎች በተጨማሪ ለገነቡት ግንባታ በህገወጥ መንገድ የተገኘ ማስረጃ ያገኙ ግለሰቦች ላይ ማጣራት እየተደረገ መሆኑም ታውቋል::

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንቦት ወር ያልቃል የተባለውን የሸገር ወንዝ ፕሮጀክት ጎብኝተዋል 

ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ በሸራተን ሆቴል አካባቢ እየተገነባ የሚገኘውን የሸገር የወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ልማት ፕሮጀክትን በሥፍራው ተገኝተው ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት የሥራ ሓላፊዎችም ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል፡፡ በቻይና መንግሥት ድጋፍ የሚከናወነው እና የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት አካል የሆነው ይህ የወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት ግንባታ፣ መስከረም 20 ቀን 2012 ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት መጀመሩ አይዘነጋም፡፡

በፕሮጀክቱ ከእንጦጦ ተራራ እስከ ባምቢስ ድልድይ ያለው 12 ኪሎ ሜትር ወንዝ እና የወንዝ ዳርቻዎች የሚለማ መሆኑ ተነግሯል። በተጨማሪም ከሸራተን ሆቴል ፊት ለፊት ያለው 42 ስኩዌር ኪሎ ሜትር መሬት በፕሮጀክቱ ይለማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በእንጦጦ ተራራ እስከ 100 ሺህ ሰው የሚያስተናግድ የመሮጫ እና የእግር ጉዞ መከወኛ ስፍራ እንደሚገነባም ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት:: በፕሮጀክቱ አምስት ግዙፍ ማዕከላት የሚገነቡ ሲሆን በዚህም መሰረት የስብሰባ፣ የጥበብ ማቅረቢያ ሥፍራ፣ የህጻናት መዝናኛ ማዕከል እና የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ማዕከላት ይካተቱበታል፡፡

ከተጀመረ ሦስት ወራትን ያስቆጠረው ፕሮጀክቱ 45 በመቶ መጠናቀቁ እና ቀሪውም በግንቦት ወር እንደሚጠናቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጉብኝቱ ወቅት ገልጸዋል፡፡ በ29 ቢሊየን ብር ወጪ የሚከናወነው የአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻዎች ልማት ፕሮጀክት በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

የአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻዎች ልማት ፕሮጀክት አዲስ አበባ ከተማን ለሁለት ከፍለው የሚፈሱ ወንዞች ላይ ያተኮረ ሆኖ፤ ከሰሜን አዲስ አበባ እንጦጦ ተራራ እስከ አቃቂ ወንዝ ያለውን 56 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ነው።

በፕሮጀክቱ በሦስት ዓመታት ውስጥ 4 ሺህ ሄክታር መሬት እንደሚለማ ይጠበቃል:: ድልድዮች፣ ሰው ሰራሽ ሐይቆች፣ አረንጓዴ ቦታዎች፣ የመዝናኛ ማዕከላት፣ የውኃ ትራንስፖርት እና የንግድ ማዕከላትን ያካተተ ግንባታ እንደሚካሄድም ከደረሰን መረጃ ተገንዝበናል:: ፕሮጀክቱ የአዲስ አበባ ከተማን የአረንጓዴ ሽፋን ከ0 ነጥብ 3 ወደ 7 በመቶ ከፍ ያደርጋል ተብሏል።

የሕግ ባለሙያው በኦሮሚያ ፖሊሶች ራሳቸውን እስኪስቱ ተደበደቡ

ከፍተኛ ሥርዓት አልበኝነትና ግልፅ የሆነ የተረኝነት ፖለቲካ ይስተዋልበታል የሚባለው የኦሮሚያ ፖሊስ በየጊዜው የሚፈጽማቸው ጥፋቶችና ጥቃቶች እየተባባሱ መምጣታቸውን የሚያሳዮ መረጃዎች እየወጡ ናቸው።

ሰሞኑን በቡራዮ ከተማ አስተዳደር ወረዳ ፍርድ ቤት በሚገኝ የአሠሪ እና ሠራተኛ ክርክር ነገረ ፈጅ የሆኑት አብዲ ኢብራሂም ደንበኛቸው አልፈፀሙትም በተባለ የአፈፃፀም መዝገብ ምክንያት ፍርድ ቤቱ “ተከሳሽ እና ነገረ ፈጁ (ጠበቃው) ይታሰሩ” ሲል ባዘዘው መሰረት ለሦስት ቀናት ታስረው የነበሩት የሕግ ባለሙያው አብዲ አብርሃም ራሳቸውን እስኪስቱ ድረስ በኦሮሚያ ፖሊሶች ጣቢያው ውስጥ ተደብድበዋል።

ሰኞ ታህሳስ 13 ቀን ለደንበኛቸው ክርክርና በድርጅቱ ላይ የተከፈተውን የአፈፃፀም መዝገብ ውሳኔውን በመፈፀም ለማጠናቀቅ ጠበቃ አብዲ በፍርድ ቤት በተገኙበት ወቅት ፖሊሶች የእስር ትዕዛዝ እንደወጣባቸው በመግለፅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወስደዋቸዋል:: በወቅቱ ጠበቃው ድርጅቱን በሕግ ጉዳዮች የሚወክሉ እንጂ ሥራ አስኪያጅ አለመሆናቸውን ጠቅሰው ተከራክረው የነበረ ቢሆንም ፖሊስች ሊሰሟቸው አልቻሉም።

ይህንን ጉዳይ ለጣቢያው ሓላፊ ከማስረዳታቸው ባሻገር ፍ/ቤት እንዲያቀርቧቸው ቢጠይቁም  “ከቀጠሮ ቀን በፊት አናቀርብህም” የሚል ምላሽ እንደደረሳቸው እና ለኹለት ቀናት በእስር እንዲቆዮ መደረጋቸውን ይገልፃሉ።  ሦስት በሦስት በሆነው ጠባብ እስር ቤት ውስጥ ከ15 ያላነሱ ተጠርጣሪዎች አብረው አብረው መታሰራቸውን ፣ መፀዳጃ ቤት ለመሔድ ፈቃድ እንኳን ለማግኘት አስቸጋሪ እንደነበርም አስታውሰዋል።

ረቡዕ ታኅሳስ 15 ቀን በቀጠሮው መሰረት ፍርድ ቤት የቀረቡት ጠበቃው እና የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ቀደም ሲል ፍርድ ቤቱ ያወጣውን ትእዛዝ መፈፀማቸውን ተከትሎ ዳኛው እንዲፈቱ ትእዛዝ አስተላልፈው ነበር።  “ከችሎት ከወጣን በኋላ ወደ ፖሊስ ጣቢያ የጽሑፍ ትእዛዝ እስኪደርስ ድረስ  ወደማረፊያ ቤት እንደሚወስዱኝ  ሲነግሩኝ እንድለቀቅ መወሰኑን በመግለፅ አልሄድም በማለቴ ድብደባና መንገላታት ደርሶብኛል” ብለዋል የሕግ ባለሙያው።

በፍርድ ቤት ትእዛዝ መሰረት ልለቀቅ ይገባል ያሉት የሕግ ባለሙያ ክፉኛ በመደብደባቸውና ጭንቅላታቸው በመጎዳቱ ለሰዐታት ራሳቸውን ከሳቱ በኋላ ሲነቁ ጣቢያው እስር ቤት ውስጥ መሆናቸውን መረዳት ችለዋል:: “የፍርድ ቤት ትእዛዝ እንዳይፈፀም ከልክለኻል በፖሊስ ላይ ፀብ አስነስተኻል በተጨማሪም በመጠላለፍ በመጠርጠርህ በቁጥጥር ማረፊያ ቤት ትቆያለህ” በሚል የእምነት ክህደት ቃል መስጠታቸውን ጭምር ተበዳዮ ይናገራሉ።

በዚህ መልክ ሐሰተኛ ክስ ተመስርቶብኛል የሚሉት ጠበቃው በጉዳዮ ፍርድ ቤት ቀርበው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አቅርበው በተሰጠው ተለዋጭ ቀጠሮ  ምክንያት በእዛው ዕለት ከእስር መፈታታቸውን አስታውቀዋል::

የትምህርት ስልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅትና ትግብራ ምክር ቤት ስብሰባ ዛሬ ተጀመረ

የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅትና ትግበራ ምክር ቤት ስብሰባ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው። በስብሰባው የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅትና ትግበራ የአፈፃፀም ሂደት፣ እንዲሁም ረቂቅ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበትም ታውቋል።

አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ፤ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ በዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ትንሹ ቆይታ 4 ዓመት ሲሆን፣ በቆይታቸውም በመጀመሪያው ዓመት በጋራ የሚወሰዱ ኮርሶችን እየወሰዱ ናቸው ተብሏል።

ከያዝነው 2012 ዓ.ም ጀምሮም ለ10ኛ ክፍል ሲሰጥ የነበረው የአጠቃላይ ትምህርት ማጠቃለያ ፈተና የሚቀር ሲሆን፥ ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረው የትምህርት ሕግም ከትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታው ጋር ተጣምሮ በተግባር ላይ እንዲውል መደረጉን በተከፈተው የትምህርት ትግበራ ውይይት መድረክ ላይ ሰምተናል።

ይህ አሠራር በየደረጃው ውይይት ከተካሄደበት በኋላ በረቂቅ ሕግ ተዘጋጅቶ የሚቀርብ መሆኑም በውይይቱ ላይ ተገልጿል። አሁንም ቢሆን የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታውን ዓለም ዐቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ አሳትሞ ለማውጣት ቅድመ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ይፋ ካደረገው መግለጫ ማረጋገጥ ችለናል ።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ  ከ300 ፕሮጀክቶች 22ቱን መረጠ

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በ300 ፕሮጀክቶች ላይ ያካሄደውን የፕሮፓዛል ግምገማ ማጠናቀቁን ገለጸ፡፡ የዳያስፖራ ትረስት ፈንዱ በፈረንጆቸ መስከረም አጋማሽ ከቀረቡለት 300 ፕሮጀክቶች መካከል ባካሄደው ግምገማ 22 ፕሮጀክቶችን ለይቼ መርጫለሁ ብሏል፡፡

በቀጣይ የተለዩትን 22 ፕሮጀክቶች የአፈፃፀም አቅም እና የበጀት ግምገማ እንደሚያደርግ ጠቁሞ ግምገማው በተቋማቱ ሃብት፣ አስተዳደር እና  ያቀረቡትን ዕቅድ ለመፈፀም ባላቸው አቅም ዙሪያ የሚያተኩር እንደሆነም በመግለጫው ላይ ሰምተናል፡፡

የፕሮጀክቶቹ ፕሮፖዛል ግምገማ በኢትዮጵያ በሚገኙ እና ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ በተለያዩ ዘርፎች በተሰማሩ በጎ ፈቃደኛ ኢትዮጵያዊያን እንደተካሄደ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ይፋ አድርጓል፡፡

የግምገማው ዋና መስፈርቶችም የቀረበው ፕሮጀክት ቀጣይነት፣ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ፣ ፈጠራ፣ ተጠያቂነት፣ ግልጽነት፣ የማደግ አቅም እና ኮሚዮኒኬሽን ናቸው፡፡

የፈንዱ የቦርድ ዳይሬክተር አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ በቅድመ ፕሮጀክት ዳሰሳው ለተሳተፉት አካላት ምስጋና አቅርበው የፈንዱን መስፈርት እና የነጥብ ሥርዓቱን ያሟሉ ውጤታማ አና ጥራት ያላቸው ፕሮጀክቶች ተለይተዋል ከማለታቸው ባሻገር፤ የመጨረሻዎቹ ድጋፍ የሚደረግላቸው ፕሮፓዛሎች ከመለየታቸው በፊት በገለልተኛ አማካሪዎች የተቋማቱ አቅም እና በጀት ግምገማ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

በመጀመሪያው ዙር የተሻሉ ተብለው ለተመረጡ ፕሮጀክቶች 4 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ይደረጋል።  ዝቅተኛው ድጋፍ 6 ሚሊየን 400 ሺኅ ብር፣ እንዲሁም ከፍተኛው 11 ሚሊየን 200 ሺህ ብር መሆኑና፤ አሸናፊ ፕሮጀክቶቹ ከአንድ ወር በኋላ ይፋ የሚደረጉ መሆኑን ተገንዝበናል።

የባህር ዳሩ ፈለገ ሕይወት  ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ችግር ላይ ነው ተባለ

በባህር ዳር የሚገኘው የፈለገ ህይወት ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመሰረተ ልማት እና በሕክምና ግብዓቶች እጥረት ምክንያት በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት እንዳልቻለ አስታወቀ።

ሆስፒታሉ ከተመላላሽ ሕክምና ጀምሮ የካንሰር ሕክምና፣ ኩላሊት እጥበት አገልግሎት እንዲሁም የቀዶ ሕክምናን ጨምሮ ከ16 በላይ የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶች የሚሰጡበት ትልቅ ማዕከል ነው፡፡

አሁን ግን ሆስፒታሉ ባጋጠሙው የክፍል ጥበት፣ የአልጋ ውስንነት፣ በተለይም የህክምና ግብዓት እጥረት ችግሮች ምክንያት የሚፈለገውን ያህል አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን የሆስፒታሉ የድንገተኛ ክፍል ሓላፊ ዶክተር አዲሱ አስታውቀዋል።

እንዲሁም የበጀት እጥረት እና ሆስፒታሉ ያለበት የ30 ሚሊየን ዕዳ በዋናነት የሚጠቀሱ ችግሮች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ ምክንያቶቹ እና ያስከተሉትም ችግሮች ታካሚዎቹ የሕክምና አገልግሎትን ማግኘት እንዳይችሉ እንዳደረጋቸው ነው የተገለጸው።

የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዐቢይ ፍስሀ በበኩላቸው፤ ሆስፒታሉ 600 አልጋዎች ቢኖሩትም ከታካሚው ጋር ሊመጣጠን አለመቻሉ ተጨማሪ ችግር ሆኗል ብለዋል።

ስለችግሮቹ የተጠየቀዉ የክልሉ ጤና ቢሮ የሆስፒታሉን የመሰረተ ልማት ችግር የሚፈታ ከ600 በላይ አልጋዎች ያለው ማስፋፊያ እየሠራሁ ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል። የግብዓት እጥረቶቹን እና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አሠራርም እንደተዘረጋም አስታውቋል።

ከተመሰረተ ከ50 አመት በላይ ያስቆጠረው በባህርዳር ከተማ የሚገኘው የፈለገ ህይወት አጠቃላይ ስፔላይዝድ ሆስፒታል በዓመት ከ 5 እስከ 7 ሚሊየን ለሚደርሱ ህሙማን የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ትልቅ የሕክምና ተቋም ነው።

LEAVE A REPLY