ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ዩንቨርሲቲዎች መርዶ ነጋሪዎች ሆነዋል። የሳይንሳዊ ምርምር ውጤት ዜናዎች ሳይሆን ከየዩንቨርሲቲዎቹ እየተሰማ ያለው ለምርምርና ለትምህርት የሄዱ ተማሪዎች ከፎቅ እየተወረወሩ፣ በጩቤ እየተወጉ፣ በጅምላ እየተደበደቡ መገደላቸውን የሚገልጹ መርዶዎች ነው። ለትምህርት የወጤ ወጣቶች አስከሬናቸው ለቤተሰ እየተላከ ነው። ይህ እርምጃ ሆን ተብሎ ከአንድ ዩንቨርሲቲ ወደ ሌላ እየተዛመተ ተቋማቱ እንዲዘጉ እና የትምህርት ሂደቱም እንዲስተጓጎል በተቀናጀ መልኩ የሚሰራ ይመስላል።
ይህን ጉዳይ ማንም ከጀርባ ሆኖ ያስተባብረው ሁሉም ሰው በጋራ ሊያወግዘው የሚገባ እጅግ አስነዋሪ ተግባር ነው። ለማህበረሰቡ ችግሮች በሳይንሳዊ ጥናት እና ምርምር መፍትሔ ያመጣሉ ተብሎ የሚጠበቁ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚያስተምሯቸው ተማሪዎች መካከል ያለውን የሃሳብ ልዩነቶች እና አለመግባባቶችን ለመፍታት አቅም እና መላ ማጣታቸው ተቋማቱ የደረሱበትን ዝቅጠት ያመላክታል።
በሌላ መልኩ መንግስት የዩንቨርሲቲዎችን ጸጥታ እና የተማሪዎችን ደህንነት ማስጠበቅ ግዴታውን እየተወጣ አይመስልም። በአገሪቱ ውስጥ በስፋት የሚስተዋለው ሥርዓት አልበኝነት ከመንደሮች እና ከየመንገዱ አልፎ የትምህርት ተቋማት ውስጥም መንጸባረቁን በግልጽ እያየን ነው። በዚህ ሳምንት ብቻ ከድሬዳዋ እና ወሎ ዩንቨርሲቲዎች የተሰማው ዜና እጅግ የሚያሳዝን ነው። በሌሎች አንዳንድ የአገሪቱ ዩንቨርሲቲዎችም ተማሪዎች ለስጋት እና ለጥቃት መዳረጋቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። በቡሌ ሆራ ዩንቨርሲትም ውስጥ ተማሪዎች ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ከቀናቶች በፊት በመገናኛ ብዙሃን ሰምተናል።
+ መንግስት አሁንም ለተማሪዎቹ እና ለትምህርት ተቋማቱ አፋጣኝ የሆነ የደህንነት ጥበቃ ሊያደርግ ይገባል።
+ ተቋማቱን ዒላማ አድርገው አገሪቱን ለማተራመስ የሚፈልጉ ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና ፖለቲከኞችም እጃቸውን እንዲሰበስቡ እና ክትትል ተደርጎም ሕግ ፊት እንዲቀርቡ መደረግ አለበት።
+ የትምህርት ተቋማቱም በየዩንቨርስቲያቸው ውስጥ ተማሪዎችን በማሰባሰብ እና ምሁራንን በመጋበዝ ተደጋጋሚ ውይይቶችን በማድረግ ተማሪዎች ችግሮቻቸውን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲለምዱ መርዳት አለባቸው።
+ ግጭቶቹን ሆነ ብለው በሚያራግቡ፣ ቅስቀሳ በሚያደርጉ እና በሚያነሳሱ ሚዲያዎች አንድ ሊባሉ ይገባል።
የውይይት ባህል የራቃቸው ዩንቨርስቲዎች ተራጋጭ፣ እርስ በርሱ የሚገዳደል እና ተደባዳቢ ትውልድ ቢያፈሩ ምን ይገርማል? ውይይት ቁጣን ያበርዳል፤ አለመግባባትን ያጠባል፤ ግጭትን ይቀንሳል።
ለሞቱት ተማሪዎች ቤተሰቦች እና ወዳጆች መስናናትን እመኛለሁ!