የጁዋር መሐመድ የዜግነትጉዳይ፣”የጠ/ሚ/ርነት ” ወንበር… | ታምሩ ገዳ

የጁዋር መሐመድ የዜግነትጉዳይ፣”የጠ/ሚ/ርነት ” ወንበር… | ታምሩ ገዳ

የኦሮሞ ፊደራል ኮንግረስ (ኦኤፍኮ)ን በቅርቡ የተቀላቀለው አክቲቪስት እና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ስራ አስኪያጅ፣ ጁዋር መሐመድ የዜግነት ጥያቄ ጉዳይን በተመለከተ ድርጅቱ (ኦፌኮ) ምላሽ ሰጠ።

የድርጅቱ ከፍተኛ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሆኑት አቶ ጥሩነህ ገመታ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሁለተኛ ጊዜ የማብራሪያ ደብዳቤ መጠየቃቸውን በማስታወስ “ጅዋር የአሜሪካዊ ፓስፓርቱን መልሷል ፣ የአሜሪካ ፖስፖርቱን መመለሱን አ/አ ከሚገኘው ኢምባሲው የተሰጠውን እኤአ ጥር/ጀነዋሪ 6/2020 የተጻፈው ደብዳቤ እና ተያያዥ ሰነዶች፣ የኢትዮጵያ ዜነቱንም በተመለከተ ለኢምግሬሽን እና ጉዳዮች መ/ቤት እኤአ ጥር 22/2020 የላከው ደብዳቤን አቶ አትክልቲ አብረሐ በተባሉ ሹም እጅ መድረሱ እና በተመሳሳይ ቀንም የኢትዮጵያዊ ዜግነትን ለማግኘት መጠየቁ ተረጋግጧል” ብለዋል።

ባለፈው ነሐሴ 2018 እኤአ ከሚኒሶታ፣አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ በ ቀይ ምንጣፍ አቀባበል የታጀበው የጁዋር መሐመድ የዜግነት ጉዳይ እና የፖለቲካ ተሳትፎው ዙሪያ ማጥሪያ ይሆን ዘንድ ለኦፌ ኮ እስከ መጪው የካቲት/ፌበርዋሪ 7/ 2020 እኤአ ድረስ የጊዜ ገደብ የሰጠው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጥያቄዎችን ያወሱት አቶ ጥሩነህ” ደብዳቤውን ለጅዋር የሰጠነው ሲሆን ጅዋርም በቅድሚያ ወደ አገሩ ተመልሷል፣በመቀጠልም የአሜሪካ ዜግነቱን መልሷል፣በስተመጨረሻም የኢትዮጵያ ዜግነቱን እንዲመለስለት ጠይቋል ።ከዚህ ውጪ በህጉ መሰረት ለተጨማሪ ጉዳይ ጁዋር የሚጠየቅበት ነገር አይኖርም።ጅዋር በዜግነቱ ኢትዮጵያዊ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

እኤአ 2003 የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ ያወጣው ህግ የውጪ ዜግነት ያለው ማንኛውም ግልሰብ የፖለቲካ አባል መሆን አይችልም፣ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ በቀጥታ ሊሳተፍ አይችልም፣የመምረጥ እና የመመረጥም መብት አይኖረውም ይላል። ለሁለት ጊዜያት ደብዳቤ የጻፈው የምርጫ ቦርድ እስከ አሁን ድረስ በጉዳዩ ዙሪያ ያለው ነገር የለም።

በኢትዮጵያ ውስጥ በመጪው ነሐሴ 16 ,2020 እኤአ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የምርጫ ዘመቻ ላይ ሙሉ በሙሉ ለመሳተፍ አቋሙን በተለያዩ መድረኮች ላይ የገለጸው ጀዋር መሐመድ እንቅስቃሴን የገመገመው የግብጾቹ አሀራም ድህረ ገጽ ሰሞነኛ ዘገባ “ከጠ/ሚ/ር አብይ አስተዳደር ጋር ይወግናል ተብሎ በብዙዎች የተጠበቀው ጁዋር ፣በተቃራኒው የዶ/ር አብይ የመድምር ፍልስፍናን ተቃዋሚ ከመሆን በተጨማሪ ጠ/ሚ/ሩን ወደ አምባገነነት እያመሩ ነው በማለት አብጠልጥሏቸዋል” ያለው ዘገባው “ኦፌኮ በምርጫው አብላጫ ወንበር ካገኘ ድርጅቱን በቅርቡ የተቀላቀለው የፌደራሊስት አስተዳደር አቀንቃኙ ጅዋር መሐመድ የቀጣዩ የአገሪቱ ገዢ ፓርቲ መሪ ሊሆን እንደሚችል ማን ያውቃል?” ሲል ግምቱን የሰነዘረ ሲሆን የመገንጠል ዜማን የሚያቀነቅኑ ኃይሎች ወደ ስልጣን ከመጡ በቋፍ ላይ ላለው የአገሪቱ የአንድነት ዋልታ መልካም ዜና አይሆንም ሲል ምክሩን አክሏል ።

ጅዋር መሐመድ ባለፈው ጥቅምት ወር አዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ የሚገኘው መኖሪያ ቤቱን ይጠብቁ የነበሩት የመንግስት የጥበቃ ሰራተኞች ” በድቅድቅ ጨለማ ሊነሱብኝ ነው” የሚል መረጃን በወዳጆች መገናኛ መረብ (ፌስ ቡክ) ገጹ ላይ ማስፈሩን ትከትሎ በተነሳው ያለመረጋጋት በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ውስጥ ከሰማኒያ ስድስት በላይ ሰላማዊ ስዎች ላይ ለደረሰው የህይወት መጥፋት እና በርካታ የንብረት ውድመት ብዙዎች ጀዋርን በዋንኛ ተጠያቂነት በመወንጀል እና ለፍርድ እንዲቀርብ ቢጠይቁም፣ እርሱ ግን ስሞታውን ለማስተባበል መሞከሩ አይዘነጋም።

LEAVE A REPLY