ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በዳኞች ላይ የሚፈጸም ጥቃት እየተበራከተ መምጣቱ ተገለጸ። ይህ ጥቃት በተለያዩ የክልሉ የፍትሕ መዋቅር ውስጥ በመሆን ሕግን እንዲተረጉሙ በተመደቡ ዳኞች ላይ እየተፈጸመ መሆኑን ዳኞችና የክልሉ ፍትህ ቢሮ ገልጿል።
የክልሉ መንግሥትም ይህንን ድርጊት በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ አስፈላጊውን ሕጋዊ እርማጃ ለመውሰድ ምርመራ እኣካሄደ መሆኑንም አመልክቷል።
በቅርቡ የወረዳ ፍርድ ቤት የፍትሐ ብሔር ዳኛ የሆኑት አቶ ኤፍሬም ኪዳኔና ባልደረቦቻቸው ተመሳሳይ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። አቶ ኤፍሬም ከሁለት የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር አረፍ ብለው ስለ ውሏቸው እና ሥራቸው እየተጫወቱ ነበር።
“የካቲት 18 ከሥራ በኋላ ቤተክርስቲያን ጸሎት አድርገን አረፍ ብለን ነበር” ያሉት ዳኛ ኤፍሬም ባላሰቡት እና ባልጠበቁት ሁኔታ መምጣታቸውን ያላስተዋሏቸው ግለሰቦች ከኋላ ደርሰው ጥቃት እንዳደረሱባቸውና ጥቃት አድራሾቹ ሁለት መሆናቸውን ይገልጻሉ።
“ከፍተኛ ጉዳት ነው ያደረሱብን ፤ በተለይ አንደኛው ዳኛ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ነው የደረሰበት። የዱላ ድብደባ ነው። እኔን ማጅራቴ አካባቢ ነው የመቱኝ። ሌላውን ጓደኛዬን ራሱን ነው የመቱት። ሦስተኛው ጥርሱ ረግፏል፤ ዓይኑ አካባቢ ጉዳት ደርሶበታል፤ አፍንጫውም ተሰብሯል። በጣም ዘግናኝ ጉዳት ነው የደረሰበት” ሲሉ የጉዳቱን መጠን ገልጸዋል።
አቶ ኤፍሬም ጥቃት አድራሾችንም ሆነ ምክንያታቸውን እንደማያውቁ ለቢቢሲ የተናገሩት የህግ ባለሙያ ባሉበት ድንገተኛ የሆነ ጥቃት እንደደረሰባቸው እንጂ ከጥቃቱ ጀርባ ስላለው ሁኔታ መናገር እንደማይችሉ ጠቁመዋል።
ጥቃቱ የደረሰባቸው ከሥራቸው ጋር ተያያዥ በሆነ ምክንያት እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “ከሥራ ውጭ ምን ሊሆን ይችላል? ጸብ የለንም። ከሥራችን ውጭ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ከማንም ጋር ግላዊ ጸብ የለንም። ለዚህ ሊያደረስ የሚችል ነገር የለንም። መቶ በመቶ ባይባልም በሥራችን ምክንያት ነው ሊባል ነው የሚችለው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ጥቃቱን “አስነዋሪ፣ አሳዛኝ እና አንገት የሚያስደፋ ድርጊት ነው” ያሉት ደግሞ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ታዘባቸው ጣሴ ናቸው። “በዱላ እና በድንጋይ ነው ጥቃቱ የተፈጸመው። ተዘናግተው በተቀመጡበት ከኋላ መጥተው ነው ያጠቋቸው። ራሳቸውን መከላከል የሚችሉበት ሁኔታም አልነበረም” ብለዋል።
“ዳኞች የድርብ ችግር ሰለባ ሆነዋል” እንደሆኑ ያመላከቱት አቶ ታዘባቸው፤ “ውስብስብ መዝገቦችን በአግባቡ ለመወሰን ቀን ከሌት ከመሥራታቸውም ሌላ ሕገ ወጦች ጥቃት እያደረሱባቸው ነው ፤ በርካታ ዳኞች ጉዳት እየደረሰባቸው ነው። ስለሆነም በቀላሉ መታየት የለበትም። እልባት ማግኘት አለበት። ጥቃቱም መታየት እና መፈተሽ አለበት።” ካሉ በኋላ ይህ ጥቃትም የመጀመሪያ አለመሆኑንናሁኔታውም ዳኞችን ተስፋ እስከማስቆረጥ እንደደረሰ አስታውቀዋል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ይህን ምክንያት አድርጎ መግለጫ አውጥቶ ነበር። የክልሉ ዳኞች ሓላፊነታቸውን ለመወጣት እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ስጋት ላይ ወድቆ በነበረበት ጊዜ ሳይቀር ያለማንም ተጽዕኖ በሕግ ብቻ ውሳኔ በመስጠት የዳኝነት አገልግሎቱ ላቅ እንዲል እየሠሩ መሆኑን በመግለጫው ይፋ አድርጓል።
በተለያዩ ወቅቶች በማዕከላዊ ጎንደር፣ በሰሜን ጎንደር፣ በደቡብ ጎንደር፣ በአዊ ብሔረሰብ፣ በሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ በሚገኙ ዳኞች ላይ የተለያዩ ጥቃቶች እና ተፅዕኖዎች መድረሳቸውን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ገልጿል።
“ጥቃቱ በተመታው ዳኛ ላይ ብቻ ሳይሆን በፍትህ ሥርዓቱና በሕዝቡ ላይ እንደደረሰ ታስቦ መንግሥት እና ኅብረተሰቡ ርብርብ በማድረግ ጥበቃ ሊያደረግላቸው ይገባል” የሚሉት አቶ ታዘባቸው፤ “በዚህ መልኩ ከተሄደ [የፍትህ] ሥርዓቱ ችግር ውስጥ ይወድቃል” ሲሉ ስጋታቸውን በግልጽ አስቀምጠዋል::
“ጠባቂያችን ሕዝብ፣ ህሊናችንና ሥራችን ነው ባሉበት ጥቃት እየደረሰባቸው ነው። መንግሥት የደህንነት ጥበቃ ማድረግ አለበት። መሣሪያ ሰጥቶ ራሳቸውን እንዲከላከሉ በማድረግ ኃፊነቱን መወጣት አለበት” ሲሉ ሓላፊው መፍትኄ ያሉትን አስቀምጠዋል።
በዚህ ሃሳብ ዳኛ ኤፍሬምም ይስማማሉ። “ለዳኞች ጥበቃ ሊደረግ ይገባል ምክንያቱም በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ነው ውሳኔ የሚሰጠው። መንግሥት በተለየ መንገድ ለዳኞች ጥበቃ ማድረግ አለበት። ትኩረት መሰጠት አለበት። ጉዳት አድራሾቹም ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለባቸው። በመንግሥት በኩል የዳኞች ጉዳይ ያን ያህል ትኩረት የሚሰጠው አይደለም። ጥቃቱ በፍትህ ሥርዓቱም ሆነ በዳኞች ላይ ትልቅ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል። ዳኞች ነጻ ሆነው ሕግን መሠረት አድርገው ውሳኔ እንዳይሰጡ ነው የሚያደርገው። መጀመሪያ የዳኞች ደህንነትና ህልውና ካልተረጋገጠ እንዴት ተብሎ ትክክለኛ የሆነ ፍትህ ሊሰጥ ይችላል?” በማለትም ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቶች መቶ በመቶ እንከን አልባ አለመሆናቸውን የሚገልጹት አቶ ታዘባቸው፤ “ተበድለናል ወይም ፍርዱ ትክክል አይደለም ካሉ በይግባኝ መጠየቅ ይቻላል። የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው ዳኞች ይኖራሉ። ዳኞች ላይ እርምጃ ይወሰዳል። እርምጃ የተወሰደባቸውም አሉ። የተባረሩ፣ የታሰሩም አሉ።” ሲሉም እየተሠራበት ያለውን መንገድ አብራርተዋል::

























