የአድዋ ነገር ውስጤ! ነበረና ገና ከማለዳው ነበር ወደ ምንሊክ አደባባይ ያቀናሁት፡፡ የአድዋ በዓል ድባቡ ደስ ይላል፤ ሕዝቡ ለታሪክ ያለው ከበረታ ሳይ እንኳን ኢትዮጵያዊ ሆንኩ ያስብላል፡፡ ደስታንና ተስፋን ይፈንጥቃል፡፡ እንኳን ለ124ኛው አድዋ በዓል በሰላም አደረሰን!!!
በሌላ በኩል፦
“በዚህ ባንድራ ነበር ጣሊያንን ያሸነፍነው” የሚሉ ወጣቶች በብስጭት አይናቸው ቀልቷል፡፡” እኔና አቶ ተክሌ በቀለ ወደ ወጣቶቹ ጠጋ አልንና ነገሩን ለማጣራት ሞከርን፤ በተቻለ መጠን ለማረጋጋት ጥረት አድርገናል፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፦
እኔ (ዳንኤል ሺበሺ) እና አቶ ተክሌ በቀለ ፒያሳ ባለው ጀኔብ ካፌ ነበር ለመገናኘት የተቀጣጠርነው፡፡ በካፌው በረንዳ ሆነን ለተወሰነ ደቂቃዎች የህዝቡን ስሜት ከራሳችን ስሜት ጋር እያጣጣምን ነው፡፡ ሕዝቡ በቸርችል ጎዳና ሽቅብ ወደ ላይ የአባይ ጎርፍ መስሏል፡፡ ከአራዳ ህንፃና ከአራት ኪሎ በኩል የተመመው ሕዝብ መገናኛው ጀኔብ ካፌ ፊለፊት ወደ ንጉሳችን ሚኒልክ አደባባይ በሚወስደው መንገድ ለፍተሻ ከተደረደረው ፖሊስ ሠራዊት ጋር ይገጥማል፡፡
በዚህን ጊዜ ነበር ፈታሾቹ በባንድራ ቀለም የተሰሩ የራስ ጥምጣሞችን፣ ከጨርቅ የተሰሩ የእጅ አምባሮችን፣ ራስ ሪባን፣ የወገብ መቀነት፣ ልሙጥ ባንድራዎችን እየቀሙና እየፈቱ ወደ ፖሊስ መኪና ይወረውሩ ነበር ፡፡ በድርጊቱ እጅጉን አዘንን፡፡ እኔና ወንድሜ ተክሌ በቀለ ወደ ታርጋ ቁ ፖሊስ አአ0212AA በሆነች ፖሊስ ፓትሮል መኪና ጎን ቆሞ አመራር እየሰጠ ወዳለው ፖሊስ አዛዥ በትህትና ቀረበንና ራሳችን ካስተዋወቅን በኋላ ይህ ለምን ይሆናል? ዛሬኮ ቀኑ ነው! የሕዝቡን ስሜት አድምጡ እንጂ! ሕዝቡ የሚፈልገውን ባንድራ፣ ሎጎ ወይም ስካርፍ ቀድሞ ይዞ የገባ መሆኑን በማስታወስ ለምን ትከለክላላችሁ ወዘተ በማለት ጠየቅነው? “አይ! የበላይ ትዕዛዝ ነው” ብሎ መለሰልን፡፡ እኛም ማዘናችንን ገልፀንና መስተካከል አለበት ያልነውን አስተያየት ምክር ለግሰን ወደመጣንበት ተመልሰንና አሁንም ቆመን ትዝብታችንን ቀጠለን፡፡
በሆነ አጋጣሚ አቶ ተክሌ በእጁ የያዘውን ሞባይል ስልክ ከእጁ እንቅስቃሴ ጋር ከፍ ሲያደርግ ያየው የፖሊስ አዛዥ ተንደርድሮ በመምጣት ፎቶ አንስተሃል ብሎ ሞባይሉን ከእጁ ቀማው፡፡ በፎቶ ማከማቻ ጋላሪ ውስጥ ፈትሾ አጣና መለሰለት፡፡ የትናንቱን ህወሓት አገዛዝ ለመመለስ የሚታተሩ፤ ከሕዝቡም ጋር እልህ የተጋቡ ይመስላሉ፡፡ የጭቆና ስሜት እያቆጠቆጠ ይመስላልና መንግሥት ጠንቀቅ ማለቱ አይከፋም! ወደ ኋላ አንመለስም!!!

























