አድዋ ህያው ነው || አንተነህ መርዕድ

አድዋ ህያው ነው || አንተነህ መርዕድ

ጀግኖች አባቶቻችን ባደረጉት ተጋድሎ ኢትዮጵያ በነጻነት ኮርታ ኖራለች፤ አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና በቅኝ አገዛዝ ቀንበር የነበሩ የዓለም ሃገራት የነጻነት ተስፋ የሰነቁትና የቅኝ አገዛዝን ፍጻሜ ትግል የጀመሩት በአባቶቻችን አብሪ ድል ብርሃን አግኝተው ነው።

የአውሮፓን ሃያል አገር ድል የነሱት ጀኞቻችን ሃያልና ሃብታም ሆነው አይደለም። የተነሱበት ዓላማ እውነትነት፣ የነበሩ ልዩነቶቻቸውን አቻችለው እንደሃገር በአንድነት መቆማቸው፣ ጦርነቱን ሆነ ዲፕሎማሲውን በጥበብ በመያዝ ጠላታቸውን ልቀው በመገኘት ድል አድርገውታል።

ዛሬ በእኛ ዘመን ከድህነት መውጣትና አባቶቻችን ያስረከቡንን ነጻነት አስጠብቀን የመኖር ግዴታ አለብን። ኢትዮጵያ ከአድዋ ወዲህ ብዙ ፈተናዎችን አሳልፋለች። ዛሬም ከባድ ፈተና ገጥሟታል። ነገም እንዲሁ። ያለፈውን አባቶቻችን በአቅማቸው የሚችሉትን አድርገው ተወጥተውታል። ነገ የመጪው ትውልድ እዳ ነው። ዛሬ ግን የእኛ ነው።

የአድዋ ተጋድሎ በቀጥተኛ ወረራ የተከሰተ ሲሆን የዛሬው ደግሞ በድህነት፣ በክፍፍል፣ በትርምስ እንድንቆይ ከሚፈልጉ ሃይሎች በተዘዋዋሪ የመጣ ነው። የአድዋ ድል በተከናወነ በ124ኛ ዓመት ላይ ኢትዮጵያ በራሷ ወንዝ በአባይ ላይ ያላትን ተጠቃሚነት ለማሳጣት ድህነታችንን፣ መከፋፈላችንን የተመለከቱ ወገኖች ሊጨፈልቁን፣ ከአባቶቻችን ያነስን ሊያደርጉን ተነስተዋል።

አባቶቻችን ድሃ ነበሩ። ድህነታቸው ከማሸነፍ አላገዳቸውም። ልዩነቶችም ነበሩባቸው። ነገር ግን ልዩነታቸውን አቻችለው በአንድነት መቆማቸው ጠላታቸውን ያደባየው ክንዳቸው ፈረጠመ። ዛሬ የመጣው ነገር ለበጎ ሊሆን ይችላል። እኛም በግብጽና በአሜሪካ ሆነ በመሰሎቻቸው በህብረት የተከፈተብንን ጥቃት በህብረት የመመከት ግዴታ ከፊታችን ተደቅኗል። በመንደርና በጎጥ፣ በሃይማኖትና በቋንቋ፣ በድንበርና በመናኛ የሃብት ክፍፍል መራኮት የሚቻለው ሃገር ሲኖር ነው። ልዩነቶቻችንን አቻችለን እንደሃገር በመጣ ጠላት ፊት በአንድነት እንቁም።

የአባይ ግድብ የታሪካዊ ጠላቶቻችን ትኩረት ሆኗል። ማንኛውንም ደካማ ጎናችን የመሰላቸውን ነገር ለዓላማቸው ስኬት ከመጠቀም ወደ ኋላ እንደማይሉ ከታሪካችን እናውቀዋለን። ይህ ግድብ የእኛም የሉዋላዊነታችን መገለጫ፣ የድህነታችን መውጫ አድርገን መመልከትና ለተግባራዊነቱ በጋራ እንድንቆም ግድ ይለናል።

ግብጾች እ ኤ አ 1874 _ 1876 ዓ ም ጉንደትና ጉራዐ ለመውረር የመጡት የአሜሪካና የአውሮፓ ቅጥረኛ ወታደሮችን መልምለው ነበር። ለነጋሪ እንዳይተርፉ ያደረጓቸው አባቶቻችን ተፈርተን በነጻነት እንድንቆይ ስለአስቻሉን እኛም ለልጆቻችን ነጻነቷ ያልተደፈረ አገር የማስረከብ ሃላፊነት የአባት እዳ አለብን። እነሆ ከ144 ዓመታት በኋላ አሁንም ግብጾች አሜሪካንን ተንተርሰው የአባይን ግድብ ለመግታት መጥተዋል። ግብጾች አባይን ህልውናችን ነው ብለዋል። እውነታቸውን ነው። እኛም ጌጣችን ብቻ ሳይሆን ህልውናችንና ነጻነታችን መሆኑን አስረግጠን ልናሳውቃቸው ይገባል። በመጡበት መንገድ ሁሉ ባለቤትነታችንን ለማሳወቅ የጉንደትንና የጉራእ አባቶቻችን ልጆች መሆናችንን ለማሳየት እንደበፊቱ የግድ የኤርትራንና የአፋርን በረሃ መውረድ አይጠበቅብንም። በአንድነት መቆማችን ብቻ በሉአላዊነታችን የሚመጡትን በጋራ ለመመከት መዘጋጀት እንጂ።

ኢትዮጵያን በነጻነቷ ለማኖርና ህዝቧንም ከድህነት ለማውጣት አሁንም አድዋ ህያው ነው። ትውልድ በአባቶቹ ታሪክ መኩራት ብቻ ሳይሆን አባቶቹን ሆኖ የራሱን ታሪክ እየሰራ ማለፍ አለበት። የአድዋ ድል የዛሬ 124 ዓመት ተጀመረ፣ ብዙ ሃገሮች ነጻ ለመውጣት የተስፋ ብርሃንና አርአያ ሆኗቸው ነጻ ወጡበት፤ አድዋ የዓለንም ታሪክ ቀየረ። እውቁ የታሪክ ጸሃፊ ሬይሞንድ ጆናስ ‘የአድዋ ጦርነት በዘመነ ኢምፓየር የአፍሪካውያን ድል’ በሚለው መጽሃፉ “አድዋ የዘመናዊዋ ኢትዮጵያ መሰረቷ ብቻ፣ ወይም የታዳጊዋ ኤጣልያ ውርደቷን የተከናነበችበት ብቻ አይደለም።

አድዋ የዓለም ህዝቦች ቅርስ ነው ብዬ እሞግታለሁ። አድዋ ‘አንደኛው የዓለም ኩነት’ ብለን የምንቀበለው ነው። ምክንያቱም አድዋ ‘የኛዋ ዓልም’ የምትሄድበትን አቅጣጫ ቀይሮታልና” ከማለቱም በላይ “አድዋ የአፍሪካን ቀለም የወሰነ ኩነት ነው” ሲል ይደመድመዋል። ነጮቹ በአድዋ ባይገደቡ ኖሮ አፍሪካውያን አሜሪካ ውስጥና አውስትራልያ እንዲጠፉ እንደተደረጉት ነዋሪዎች (አቮሪጅናልስ) ጠፊ ነበሩ።

አፍሪካዊ ቀለሙና ዘሩን ከመጥፋት የዳነው በአባቶቻችን ተጋድሎ መሆኑን ፈረንጆች ሳይቀሩ ሲመሰክሩ በራሳችን ታሪክ የሚያፍሩ ጉዶችንም የያዘች ኢትዮጵያ ትግሏ ከውስጥም ነው። አድዋ ድሉ እኛ ላይ ደርሶ ላይቆም የትውልድ ሃላፊነት አለብን። ስለሆነም ተቻችለን በአንድነት ከመቆም የተሻለ አማራጭ የለንም።

LEAVE A REPLY