ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የሰላም ሚኒስቴርና የሲቪክ ማኅበራት በአጋርነት መሥራት የሚያስችላቸው የትብብር ማዕቀፍ መዘጋጀቱ ተገለፀ።
በዛሬው ዕለትም በተዘጋጀው ማዕቀፍ ላይ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ በመካሄድ ላይ ነው።
የተዘጋጀው ማዕቀፍ በሰላም፣ በግጭት መከላከል፣ በምርጫና በዴሞክራሲ መስኮች ላይ ከሚሠሩ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በትብብርና በአጋርነት መሥራት የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው፥ መንግሥት ከዚህ ቀደም የሲቪክ ማኅበራት ላይ የሚያካሂደውን አቋም መቀየሩን አስረድተዋል። አሁን መንግሥት ከሲቪክ ማኅበራት ጋር በጋራ የሚሠራበት ወቅት መሆኑንም ጠቁመዋል።
የሰላም ሚኒስቴርና የሲቪክ ማኅበራት በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን 10 የትብብር መስፈርቶችንም በማዕቀፉ አስቀምጠዋል። ከእነዚህም ውስጥ ሰብአዊ መብት፣ የዴሞክራሲ ግንባታ፣ ሴቶችና ሕጻናት፣ የህግ ማዕቀፎች አተገባበርን መፈተሽ፣ የህግ የበላይነትን ማስፈን እንዲሁም ግጭት እና ግጭት አፈታት የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።
በትብብር ማዕቀፉ ላይ የሚደረገው ምክክር ከተጠናቀቀ በኋላ የሚፀድቅ ሲሆን እስከ ታች ድረስ ወርዶ ተግባራዊ ይደረጋል መባሉንም ሰምተናል።

























