
ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በዓለም ላይ ግዙፉ የመድኃኒት አምራች ኩባንያ አስትራዜኔካ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ሁለት አዳዲስ ስምምነቶች መፈራረሙ ተነገረ።
ስምምነቶቹ ኩባንያው በአንድ ጊዜ ለኮሮናቫይረስ ክትባት 2 ቢሊዮን ጠብታዎችን ለማምረት የሚያስችለው እንደሆነ እየተነገረ ነው።
አስትራዜኒካ በአንድ ጊዜ 1 ቢሊዮን ጠብታዎችን ማምረት እንደሚችል ቀደም ሲል በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ለተያዘውና ተስፋ ለተጣለበት የኮቪድ-19 ክትባት ምርምር እየተደረገ ካለው ዝግጅት ጋር በተያያዘ መግለጹ ይታወሳል።
ትልቁ የመድኃኒት አምራች ትናንት ሐሙስ ተጨማሪ ሁለት አዳዲስ ስምምነቶችን የተፈራረመ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ አንዱ በቢሊየነሩ ቢልጌትስ የሚደገፍ ፕሮጀክት እንደሆነ በመነገር ላይ ነው።
የእንግሊዙ አስትራዜኒካ በቅልጥፍና ያመርተዋል የተባለው ይህ የኮሮና ቫይረስ ክትባት መድኃኒት በዋናነት እንዲደርስ የታሰበው ደግሞ መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው አገሮች (አፍሪካና ላቲን ሀገራት) እንደሆነም ተገልጿል።
አስትራዜኒካ በበኩሉ መድኃኒቱን በፍጥነት ለማድረስ በስሩ፣ ሴሩም ኢንዲያ ፣ ቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ የተሰኙ ከፍተኛ መድኃኒት የማምረት አቅም ካላቸው ድርጅቶች ጋር በቅንጅት ለመሥራት የ750 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት መፈጸሙ ተሰምቷል።
ቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ የተሰኙት ሁለቱ ካምፓኒዎች የሚደገፉት በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋቪ እና ሴፒ የሚባሉ ሲሆን ፤ 300 ሚሊዮን ብልቃጥ ክትባት የማምረት ሂደቱን እንዲያሳልጡና የምርት ግብአቶችን እንዲያቀርቡ ስምምነቱ ይፈቅድላቸዋል።
ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ያለው የክትባት መድኃኒቱ በዚህ ዓመት መጨረሻ ይደርሳል ተብሎ በከፍተኛ ጉጉት እየተጠበቀ ነው።
የአስትራዜኔካ ሥራ አስፈጻሚ ፓስካል ሶሪዮት በነሐሴ መጨረሻ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ እየሞከረው ያለው ክትባት ውጤታማነት ይረጋገጣል ያሉት የአስትራዜኔካ ሥራ አስፈጻሚ ፓስካል ሶሪዮት ይህ ክትባት ላይሠራም የሚችልበት ዕድል እንዳለ መገንዘብ ያሻል ሲሉ ጠቁመዋል።
























