አርቲስት፣ ገጣሚ እና አክቲሽስት አጫሉ ሁንዴሳ ባለፈው ሰኞ በታጣቂዎች ህይወቱ መቀጠፉን ተክትሎ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ደግሞ በአ/አ እና በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ውስጥ የተስተዋለው እጅግ ዘግናኝ ኢሰብአዊ ድርጊቶች በትንሹ ከአንድ መቶ ስድሳ ስድስት በላይ ዜጎች ህይወታቸውን አሳጥቷል፣ በርካታዎች ቀላል እና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ በሺህ የሚቆጠሩን ለእስራት ዳርጓል፣ ለዘመናት የተገነባ የበርካቶች ሀብት እና ንብረት ወድሟል። ሁኔታው የብዙዎች ልብን ክፉኛ ሰብሯል፣ አስለቅሷል፣ አይምሮ ያላቸው ሰብአዊ ፍጥረቶችን ዛሬም አያላቀሰ ይገኛል።
ግድያውን ተከትሎ የደረሰው የሰብአዊ፣ቁሳዊ እና ሞራላዊ ኪሳራን በተመለከተ ብዙዎች በቁጭት እና በሀዘኔታ ገልጸውታል። ከሀጫሉ የቀብር ስነስርአት ጋር በተያያዘ ሀሙስ እለት የአሜሪካ ራዲዮ የአማሪኛው ክፍለ ጊዜ በስልክ ያነጋገረው የሀጫሉ ታላቅ ወንድም የሆነው ሀብታሙ ሁንዴሳ ” አስክሬኑ ማረፍ ያለበት በትውልድ አካባቢው ምዕራብ ኦሮሚያ፣ አንቦ ውስጥ ሳይሆን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ መቀበር አለበት “ተብሎ ስለተፈጠረው ግርግር እና አጠቃላይ ሁኔታ ሲገልጽ”አምቦ ከተማ ማለት የተወለደበት፣ እትብቱ የተቀበረበት፣ ወላጆቹ፣ ወንድሞቹ፣ እህቶቹ፣ ሚስቱ እና ልጆቹ የሚኖሩበት፣ በህይወት ዘመኑም ከሞትኩኝ አንቦ ወስዳችሁ ቅበሩኝ እያለን ነበር። እውነታው ይኼ ሆኖ ሳለ ከቤተሰቡ ፍላጎት ውጪ ለመቅበር የተደረገው ሙከራ አሳፋሪ ነው። ለወንድሜ ይኼ ሁሉ እንግልት አይገባውም፣ ትልቅ ቦታ ይደርሳል ብዬ አስቤው ነበር፣ እኛ የማንንም ፉከራን አንፈልግም፣ወንድሜ በአጭሩ ተቀጭቷል።” ሲል መሪር ሀዘኑን ገልጿል።
ብዙ ሰንቆ በአጭሩ የተቀጨው የስላሳ ስድስት አመቱ ልጃቸውን፣ ወንድማቸውን፣ አባታቸውን የተነጠቁት የሀጫሉ ቤተሰቦች ሀዘናቸውን በቅጡ ሳይወጡ በቀብር እለቱ አንቦ ከተማ ውስጥ በተፈጠረው አምባጓሮ የተነሳ የሀጫሉ የአባቱ ወንድም (የአጎቱ ልጅ) እንደዚሁ ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ኃይሎች ህይወቱን ማጣቱን የተናገረው የሀጫሉ ታላቅ ወንድም፣ ሀብታሙ “ሁሉም ሰው በስሜት ከመጓዝ፣ ቆም ብሎ ያስብ “ሲል አይናቸው እና ልቦናቸውን ለታወሩ ቡድኖች ምክር አዘል ወገናዊ ጥሪውን አስተላልፏል። የአንድ ወር ጨቅላን ጨምሮ የሶስት ልጆቹ እናት እና የትዳር ጓደኛው የሁኑት ወ/ሮ ፋንቱ ደምሴ በበኩላቸው ለአርቲስት ሀጫሉ ክብር እና መታሰቢያ ይሁን ዘንድ በአዲስ አበባ ከተማ እና አምቦ ውስጥ ሃውልት ይቆምለት ዘንድ ጠይቀዋል።
በሀጫሉ እና በቤተሰቡ ላይ የደረሰው ጥቃት እና አሳዛኝ ገጠመኝ በዚህ ብቻ አላበቃም። ግድያውን ተከትሎ ከመዲናዋ አዲስ አበባ ሁለት መቶ ሁለት ኪሎ ሜትር ደቡባዊ አቅጣጫ፣ ሻሸመኔ ከተማ ውስጥ ለአመጽ እና ለጥፋት የተንቀሳቀሱ ኃይሎች ካወደሟቸው በርካታ ንብረቶች መካከል የታዋቂው የሉሲ የትምህርት ማእከል ይገኝበታል።
የማእከሉ መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ዮሐንስ ወልዴ ማክሰኞ እለት ስለ ደረሰባቸው የገንዘብ እና የስነልቦና ኪሳራ ለአሜሪካ ራዲዮ ሲናገሩ” ለአገሪቱ በርካታ ዶክተሮችን እና ፕሮፌሰሮችን፣ ትልቅ ደረጃ የደረሱ ወጣቶችን ያፈራው አንጋፋው የትምህርት ማእከላችን ወደመ፣ይህም አልበቃ ብሎ አክራሪ ባለመሆኔ መኖሪያ ቤቴ ተለይቶ በእሳት አጋዩት፣ አሁን ምንም የቀረኝ ነገር የለም” ብለዋል።
ከኦሮሞ ብሔር እና ከሌላ ብሔር መወለዳቸውን ፣ከአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ባለቤት ጋር የስጋ ዝምድና እንዳላቸው የተናገሩት ኢንቨስተሩ አቶ ዮሐንስ ከሁሉም በላይ ሀዘናቸውን ያገዘፈው ሁኔታን በአርቲስት ሀጫሉ ሞት በብርቱ ሀዘን ላይ ወድቀው፣ ወደ አምቦ ሄደው ከቤተሰብ ጋር እርማቸውን ለማውጣት በዝግጅት ላይ ሳሉ ለዘመናት በኖሩበት፣ለበርካታ ወጣቶች የእውቀት ስኬት መንገድ የጠረጉበት አንጋፋው የሊሲ የትምህርት ማእከል፣ በራሳቸው ወገኖች ዶግ አመድ መሆኑ፣ መኖሪያ ቤታቸውም እንዲሁ ተለይቶ እና እቅድ ተይዞለት ሙሉ በሙሉ በመውደሙ”አምቦ ሀዘን ላይ የሚገኙት ቤተሰቦቼ ሀዘናቸውን በቅጡ ሳይወጡ እኔን በ ስልክ ለማስተዛዘን ሲሞክሩ በማየቴ ሞራሌ ተንክቷል፣ በእጅጉ አዝኛለሁ፣ ይሄ በኢትዮጵያ እና በልጆቿ ላይ የደረስ ትልቅ ውድቀት ነው “በማለት የነገሮች እንደዚህ ውስብስብ፣ ተደራራቢ እንቆቅልሽ መሆንን በሀዘኔታ እና በቁጭት ገልጸዋል ።
አርቲስት እና አክቲቪስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ለምን እንዲህ ተመርጦ የወረሃ ሰኔ ጭዳ እንዲሆን ተፈለገ? ፣በእነማንስ ተገደለ? የሚለው እና ተያያዥ ጥያቄዎችን በተመለከተ ብዙዎች የየራሳቸውን ቅድመ ግምት እና ጥርጣሬን ሰሞኑን በመስጠት ላይ ይገኛሉ። የአርቲስቱ እንደዚህ በአጭሩ መቀጨት ከቤተሰቦቹ፣ ከአድናቂዎቹ አልፎ በሰባዊነት ካልሆነ በአገር ልጅነት በጭራሽ የማይዛመዱት በሺህ የሚቆጠሩ የሙዚቃ አፍቃሪዎች የተመሳቸውን ጥልቅ ሀዘንን ሰሞኑን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
አርቲስት ሀጫሉ እኤአ 2017 ካሳተመው ድንቅ አልበሙ ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሙዚቃ አፍቃሪዎችን ልብ እና ጆሮዎችን የኮረኮረው ” አላችሁ/አለን ወይ? (ጅራ፣ጅራ፣ጅራ..)”በተሰኘው የዩቱይብ ዘፈኑ ስር ካዋሊ ገዲኢ የተባሉ ከጎረቤት ሶማሊያ ነኝ ያሉ የጻፉት አስተያየት “ጅራ፣ጅራ በሶማሊኛ ቋንቋ ማለት መኖር ማለት ነው ። ምሳሌ ያህል ዋን ጅራ ሲባል እኔ አለሁ እንደማለት ነው። ይህ ጀግና ወጣት ህይወቱ በመቀጠፉ በጣም እዝኛለሁ።
ወገኖቼ ሆይ :- በእንደዚህ አይነቱ መጥፎ አጋጣሚ መቆጨት ቢኖርም፣ ላለፉት ሰላሳ አመታት ሰላም እርቋት የምትገኘው አገሬ ሶማሊያን ቆም ብላችሁ አስቡ።
ዘመዶቼ:- በአገራችሁ ያለው አንጻራዊ ሰላምን አታውኩት፣ የብዞዎቻችን ችግር የሆነው ድህነትን እና ኃላቀርነትን በማስወገድ ረገድ ሁሉም የአፍሪካ ፖለቲከኞች አንድ አይነት እና ደካማዎች መሆናቸውን አትዘንጉ። መልካም እድል፣ ሰላም ይብዛላችሁ” በማለት አስታያየታቸውን ሰጥተል።
አሁንም ቢሆን መተኪያ የማይገኝለት የእናቱ፣ የአባቱ ልጅን፣ ታናሽ ወንድሙን ከጎኑ አጥቶ፣ ነገር በማያውቁት አሊያም ጥንቀቀው ባልተረዱት ፕሮፓጋንዳ ስሜት ብቻ በመነዳት ለጥፋት ኃይሎች መሳሪያ በመሆን ላይ የሚገኙ ወጣቶችን እና ፖለቲከኞችን “ትንሽ ቆም ብላችሁ አስተውሉ ” ብሎ የተማጸነው ሀዘንተኛው ሀብታሙ ሁንዴሳ፣ ሆነ ማየት ማመን ነው እንዲሉ “ውገኖቼ ከእኛ ተማሩ ” ያለው ሶማሊያዊወ የሀጫሉ አድናቂን ምክር ማዳማጥ ትልቅነት ነው።
ፈጣሪ በገፍ የወደቁ ወገኖቻችን ነፍሳቸው ይማርልን፣ ቤተሰቦቻቸውን ያጽናናልን። አገራችን ኢትዮጵያን እና ልጆቿን ይጠብቅልን።

























