ታከለ ኡማ የመሬት ይዞታን ኦዲት ማድረግ ጀምሬያለሁ አሉ

ታከለ ኡማ የመሬት ይዞታን ኦዲት ማድረግ ጀምሬያለሁ አሉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና ግልፅ የሆነ የመሬት ወረራ ተረኝነትን ባነገበ ዘመቻ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ ሲካሄድ ያላየና ያልሰማ ይመስል ዝም ያሉት ከንቲባ ታከለ ኡማ ህገ ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል የሚያስችል ኦዲት ጀምሪያለሁ ብለዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው ምዝገባ ህገ ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል ያለመ ነው ያሉት ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ፤ የምዝገባ እና ኦዲት ሂደቱን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
ይህ አዲስ የተጀመረው የምዝገባ እና ኦዲት ሥራ ከመሀል ከተማ እስከ ዳር የአርሶ አደሮች ይዞታን ጭምር ያካተተ እንደሆነ፤ በተጨማሪም በህገ ወጥ ወረራ ተጋላጭ የሆነው የአርሶ አደሮች ይዞታን በመመዝገብ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ እንዲኖራቸው ለማድረግ ታልሟል ነው የተባለው።
ከንቲባው ይህን ይበሉ እንጂ አዲስ አበባ ዙሪያ ለዓመታት የኖሩ፣ ከግብርናና ከከብት እርባታ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን ሲገፉ የቆዮ ብዛት ያላቸው ነዋሪዎች “የኬኛ” ፖለቲካ በሚያራምዱ እና ከየት እንደመጡ በማይታወቁ የመንጋ አባላት በተደጋጋሚ ሲነጠቁ ታይቷል።
በቅርቡም በላፍቶና አቃቂ አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች ከሌላ ሥፍራ በመጡ የመንጋ አባላት መወረሩንና የመሬት ነጠቃው ላይ የወረዳውና የክፍለ ከተማው ከፍተኛ አመራሮች ቀጥተኛ እገዛ እንዳለበት ኢሳትን ጨምሮ ለተለያዮ መገናኛ ብዙኃን መግለጻቸው አይዘነጋም።
ምዝገባው በቴክኖሎጂ አሠራር የተደገፈ እንዲሆን ከሳይንስ እና ኢኖቬሺን ሚኒስቴር ጋር በጋራ የሚሠራ እንደሚሆን የተናገሩት ኢ/ር ታከለ ኡማ፤ በማስፋፊያ ፕሮጀክቱ አምስት ክ/ከተሞች ላይ የሚገኘው የአርሶ አደሮች መሬት ምዝገባ እስከ መስከረም 30 እንዲጠናቀቅ አቅጣጫ መቀመጡን አብራርተዋል።
ምዝገባው አርሶ አደሮች በደላላ ተታለው ያለአግባብ መሬታቸው እንዳይወሰድ ፣ በህገወጥ መንገድም እንዳይወረር ለመከላከል አስተዋጽዖ አለው ተብሎለታል።

LEAVE A REPLY