የኢትዮጵያ ሰበአዊ መብት ጉዳይ! ኦሮሚያን አስመልክቶ || ታዬ ደንደአ

የኢትዮጵያ ሰበአዊ መብት ጉዳይ! ኦሮሚያን አስመልክቶ || ታዬ ደንደአ

በሀገራችን ሰበአዊ መብቶች ይከበሩ ዘንድ ውድ ዋጋ ያስከፈለ ትግል ተካሄዷል። በተለያዬ ደረጃ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በትግሉ ተሳትፏል። ከረጅም ጊዜ በኋላ ትግሉ ለፍሬ በቅቶ አለምን ያስደመመ ለዉጥ መጥቷል። መንገድ ላይ ደግሞ ተግዳሮት ገጥሟል። ችግሩን በትብብር በመፍታት የሰዉ ልጆች ክብር የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን መፍጠር የሁሉ መልካም ዜጎች ኃላፊነት ይሆናል።

ትላንት የኢትዮጵያ ሰበአዊ መብት ኮሚሽን አንድ መግለጫ አዉጥቷል። መግለጫዉ መንግስት በኦሮሚያ ክልል ሠላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ ከልክ ያለፈ ኃይል መጠቀሙን ያትታል። በእርግጥ ተቋሙ ከተመሠረተበት ዓላማ አንፃር በሀገሪቱ ስላለዉ የሰበአዊ መብቶች ሁኔታ በአግባቡ ሊከታተል ይገባል። ነገር ግን መግለጫ ሲወጣ ሚዛን መጠበቅ ያስፈልጋል። የትላንቱ መግለጫ በግልፅ ሚዛን የሳተ መሆኑን በቀላሉ ማሳየት ይቻላል!

ከሰበአዊ መብቶች መከበር አኳያ መንግስት ድርብ ኃላፊነት አለበት። አንደኛዉ በራሱ የሰዉ ልጆችን መብት ማክበር ነዉ። በህግ የተሰጠዉን ኃላፊነት ሲወጣ የዜጎችን ሰበአዊ ክብርና መብት ማክበር ይኖርበታል። ይህ ሀይል አለመጠቀምን ይጠይቃል። መንግስት ሀይል ሲጠቀም የመብት ጥሰት ይከተላል። በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት በግዛቱ ዉስጥ ሰበአዊ መብቶችን ማስከበር ይጠበቅበታል። ጉልበተኛ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች የዜጎችን ሰበአዊ መብት እንዳይጥሱ ለመከላከል የህግ የበላይነት ማስከበር ማለት ነዉ። ይህ ደግሞ ሀይል መጠቀምን ይፈልጋል። ተመጣጣኝ ሀይል በዚህ መሀል ይመዘናል!

ከለውጡ በኋላ በኢትዮጵያ በአጠቃላይና በኦሮሚያ በተለይ የሰበአዊ መብቶች ለአደጋ የተጋለጡት በጉልበተኛ ግለሰቦች እና ቡድኖች መሆኑን አለም ያዉቃል። መንግስት ሰበአዊ መብቶችን ለማስከበር አስፈላጊዉን ሀይል አልተጠቀመም ማለት ነዉ። በዚህ ምክንያት የደረሱ ጉዳቶችን ማሳየት ጥሩ ይሆናል። ጥቅምት ላይ አንድ አክቲቪስት “ተከበብኩ” ብሎ በሰራዉ ድራማ የ 97 ዜጎች ህይወት ጠፍቶ የበርካቶች አካል ጎሏል። ሰኔ 23 /2012 የአርቲስት ሀጫሉን የሴራ ግድያ ተከትሎ የ 167 ዜጎች ህይወት ተቀጥፎ በርካቶች አካላቸዉን አጥቷል። በብዙ ቢሊየን የሚገመት የዜጎች እና የሀገር ሀብትም ወድሟል። ይህ ሁሉ በጉልበተኛ ግለሰቦች እና ቡድኖች ተፈፅሟል። መንግስት በዚህ ላይ ተተችቷል።

ካለፈዉ ማክሰኞ (12/12/12) ጀምሮ ደግሞ ፅንፈኞች በኦሮሚያ ላይ የሽብር አዋጅ አስተላልፈዋል። አዋጁ የብልፅግና አባላትን፣ ሌሎች ብሔሮችን እና የአመራር ቤተሰቦችን ግድያ ይጨምራል። በክልሉ ያሉ መንገዶች እንዲዘጉ ብቻ ሳይሆን የዉሃ፣ የመብራት፣ የባቡር፣ እና የስልክ መሰረተ ልማቶች እንዲወድሙ በመደበኛና በማህበራዊ ሚዲያ ትዕዛዝ ተላልፏል። መንግስት ይህን ግልፅ አደጋ በማስቆም የዜጎችን ሁለንተናዊ ደህንነት ማረጋገጥ ይኖርበታል። ይህ ደግሞ ሀይል መጠቀምን ይጠይቃል። ከዚህ አንፃር መንግስት የወሰደዉ እርምጃ እንዴት “ከልክ በላይ ነዉ” ይባላል? ተመጣጣኝነትስ በምን ይለካል? ኮሚሽኑ ስለመንግስት እርምጃ ከማህበራዊ ሚዲያ የተረዳዉን ያህል በማህበራዊ ሚዲያዉ የታወጀዉን እልቂት እና ዉድመት ለምን ይስታል? ዜጎችን በተግባር የገደለና የሀገርን ንብረት ያወደመ ሽብር እንዴት “ሰላማዊ ተቃውሞ” ይባላል? ያስተዛዝባል!

LEAVE A REPLY