ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢትዮጵያ መንግሥት በየመን በተለያየ ችግር ውስጥ የሚገኙ 1ሺኅ 200 ኢትዮጵያውያንን ሊያስወጣ መሆኑ ተነገረ።
በውጪ አገር ስለሚገኙ ኢትዮጵያ እና ስለ ሕዳሴው ግድብ ዛሬ መግለጫ የሰጡት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ በሊባኖስ የሚገኙ 180 ኢትዮጵያኖችን ወደ አገር ውስጥ ለመመለስ ሰነድ መዘጋጀቱንና ዜጎችም በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱም አያይዘው ጠቁመዋል።
አሁን ላይ በየመን ባለው የፀጥታ ችግር ምከንያት ኢትዮጵያኖችን በአንድ ስፍራ ሰብስቦ ማግኘት አስቸጋሪ ቢሆንም፤ ከአውሮጳ ሕብረት ተወካዮች ጋር በመተባበር 1ሺኅ 200 ኢትዮጵያውያን የጉዞ ሰነድና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች እየተመቻቹላቸው ነው ተብሏል።
ከሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ጋር መልካም መግባባትና ግንኙነት ኢትዮጵያ ያላት መሆኑን ተከትሎ፤ ከየመን ወደ ሳዑዲ አቋርጠው የገቡ ኢትዮጵያኖች በሳዑዲ መንግሥት ጥበቃ የሚደረግበት ስምምነት እንደተደረገም ከመግለጫው መረዳት ተችሏል።
ዓለም ዐቀፍ የሰብኣዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ሂይውማን ራይትስ ዎች ባወጣው ሪፖርት በሳዑዲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ መናገሩን ተከትሎ የመንግሥትን አቋም የተጠየቁት ዲና ሙፍቲ፤ “እንዲህ አይነት ችግር የለም ማለት ይከብዳል፤ ይሁን እንጂ በሳዑዲ ያሉት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ለኢትዮጵያውያን ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሠሩ ከመንግሥት ትዕዛዝ ተላልፏል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።