በሳዑዲ እስር ቤቶች በሚገኙ እስረኞች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ የአውሮፓ ኅብረት አወገዘ

በሳዑዲ እስር ቤቶች በሚገኙ እስረኞች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ የአውሮፓ ኅብረት አወገዘ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላይ የሚፈጸመውን አስከፊ አያያዝና የሰብኣዊ መብት ጥሰት እንዲሻሻል ጠየቀ ።

ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው በሳዑዲ አረቢያ፣ በኤርትራና በኒካራጓ ውስጥ ያሉ የሰብኣዊ መብት ጉዳዮችን በተመለከተበት ጉባኤ ላይ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው ፓርላማው፤ በዚህም በሳዑዲ ያሉ ኢትዮጵያዊያን አያያዝ ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ በማንሳት እንደሆነም ገልጿል።
የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት አሁን ድረስ በሳዑዲ እስር ቤቶች ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ተይዘው ሰብኣዊ መብቶቻቸው ተጥሶ እንደሚገኝ በመግለፅ ድርጊቱን አውግዞታል። ኅብረቱ ያስተላለፈውን የውሳኔ ሀሳብ ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረት ልዑኮች በሳዑዲ አረቢያ ማጎሪያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ስደተኞችን በቀጣይ እንደሚጎበኙ የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ አባል የሆኑት ሰሚራ ራፋኤላ አረጋግጠዋል።
ከሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች እየወጡ ያሉ ምስሎችን እንዲሁም ሪፖርቶችን መመልከታቸውንና የስደተኞቹ ጉዳይም እጅግ አሳሳቢ መሆኑ አስቸኳይ የውሳኔ ሀሳብ እንዲሰጥ ማድረጉ ነው የተነገረው።
የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርትን የጠቀሰው ፓርላማው ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር አንስቶ በግድ ከየመን ተገፍተው እንዲወጡ የተደረጉ ነፍሰጡር ሴቶችና ሕጻናት የሚገኙባቸው 30 ሺኅ የሚደርሱ ኢትዮጵያዊያን ያለፍርድ በአሰቃቂ ሁኔታ ሳዑዲ ውስጥ ባሉ እስር ቤቶች እንደሚገኙ  ገልጿል።
ይህን ተከትሎም የአውሮፓ ሕብረት ምክር ቤት አባላት የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት ሴቶችና ሕጻናትን ጨምሮ ለችግር የተጋለጡትን ቅድሚያ በመስጠት በአስቸኳይ እንዲለቁ ጠይቋል።
 የሳዑዲ ባለሥልጣናት በጦርነት ውስጥ ከምትገኘው ጎረቤት የመን ሸሽተው ወደ ግዛታቸው የሚገቡ ሰዎችን ደኅንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ ተቀብለው ዓለም ዐቀፍ ደረጃቸውን ወደጠበቁ የማቆያ ማዕከላት እንዲገቡ ማድረግ እንዳለባቸውም ከተላለፈው የውሳኔ ሀሳብ መረዳት ተችሏል።

LEAVE A REPLY