ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከሰሜን ዕዝ ከማዕከል ጋር የሚኖረው የመገናኛ ሥርዓት እንዲቋረጥ በማድረግ በጁንታው የህወሓት የጥፋት ቡድን ጥቃት እንዲፈፀምበት ሲያመቻቹ የነበሩ ጀነራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንቶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው ከጁንታው ህወሓት ጋር በመጣመር ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ በትግራይ ክልል የሚገኘው የሰሜን ዕዝ ፤ ከማዕከል ጋር የሚኖረው ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጥ፣ የዕዙ የመገናኛ ሥርዓትም ለጁንታው ቡድን እንዲመቻች በማድረግ የተጠረጠረው ሜ/ ጀነራል ገብረመድህን ፈቃዱ (ወዲ ነጮ) በሀገር ክህደት ወንጀል ከነ ግብረ አበሮቹ በሀገር መከላከያ ሠራዊትና በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉ በይፋ ተገልጿል።
ይህ ጀነራል ከለውጡ በፊት በሀገር መከላከያ ሠራዊት የአጋዚ ኮማንዶና ልዩ ኃይሎች አዛዥ የነበረ ሲሆን፣ በሠራዊቱ ውስጥም በተለያዩ የሥራ እርከኖች ያገለገለ መሆኑን የጠቆመው መግለጫ፤ ለውጡን ተከትሎም በሀገር መከላከያ ሠራዊት የመገናኛ መምሪያ ሓላፊ በመሆን ሢሠራ እንደነበርም ገልጿል።
ይሁን እንጂ በሀገር መከላከያ ሠራዊት የተጣለበትን ከባድ አደራና ሓላፊነት ሀገር ለማፍረስና ለማተራመስ ከሚንቀሳቀሰው ጁንታ አካል በመሆን የሰሜን ዕዝ ከማዕከል ጋር ያለው ግንኙነት እንዲቋረጥና በከሃዲዎች ጥቃት እንዲፈፀመበት ከማድረጉም ባሻገር፤ በውስጣቸው ቦንቦችና የሚሳይል መሳሪያዎችን የያዙ 11 ሳጥኖችን “የግንኙነት መሳሪዎች ናቸው” በሚል ሽፋን ወደ ትግራይ ለመላክ ሲዘጋጅ፣ ከተለያዩ የጦር መሣሪያዎች ጋር እጅ ከፍንጅ መያዙን ተረጋግጧል።

























