ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ቦታዎች የተፈጸሙ ጥቃቶች በሰብኣዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።
“በጥቃቱ በተሳተፉ ሰዎችና ቡድኖች በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸሙት ጥቃቶች በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ባሕርያትን የሚያሟሉ ናቸው” ያለውና ዛሬ ይፋ የሆነው የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን፤ ለተከታታይ ጊዜያት ቢያንስ በ40 የተለያዩ ቦታዎች ፣ በአብዛኛው በቡድን የተደራጁ ሰዎች ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸው፣ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት ማድረሳቸው፣ ንብረት ማውደማቸውና ነዋሪዎችን ማፈናቀላቸው ለዚህ በቂ ማስረጃ ናቸው ብሏል።
ጥቃቱ በከፊል በብሔርና በሐይማኖታቸው ተለይተው የተመረጡ ሰዎችን ከየቤታቸው ለይቶ በማሳደድና በማጥቃት፣ በተጨማሪም ብሔርና ሃይማኖት ሳይለይ ሰላማዊ ነዋሪዎችን ወይም ሲቪል ሰዎችን ሆነ ብሎ በማጥቃት የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት እንደሆነም የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ አረጋግጠዋል።
በወንጀል ድርጊቱ ሲሳተፉ የነበሩት ሰዎች፤ ተግባራቸው ስልታዊና የተቀናጀ ወይም የሰፊ ጥቃት አካል መሆኑን በማወቅ የተሳተፉበት ነበር ያለው ኢሰመኮ፤ እነዚህ በቡድን የተፈፀሙት ጥቃቶች ጠቅላላ ድርጊቶቹና ውጤታቸው በሰብኣዊነት ላይ የተፈጸመ የግፍና ጭካኔ ወንጀል መሆኑን የተደረገው ማጠራት አመላክቷል ሲል ገልጿል።

























