ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ኦነግ ሸኔ በሰሜን ሸዋ አጣዬ ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ በከፈተው ጥቃት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱ ከአካባቢው ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
ዛሬ ከረፋዱ ጀምሮ ለኢትዮጵያ ነገ ሲላክልን ከነበረው በርካታ መረጃዎች መካከል ቀዳሚው ብዙ አስጨናቂ መልእክቶች በውስጥ መስመር ደርሰውናል “ኦነግ ሸኔ ከመንዝ ገበሬ ጋር አጣዬ ላይ ገጥሟል። ምንም አይነት የመንግስት ኃይል የለም። የከተማው ነዋሪ ወደ ፈርድ ውሃ፣ ሳር አምባ እና አጎራባች ገጠር ቀበሌዎች ሸሽቷል። ቤተ ክርስቲያን እንዳያቃጥሉ እየተከላከልን ነው” የሚል ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ ከደረሱን መልዕክቶችም “አጣዬ ላይ ከባድ መሳሪያ የታጠቁ የኦነግ ወታደሮች ቤት እየሰበሩ ገብተው ብዙ ሰው ገድለዋል። ባንክ ዘርፈዋል። ቤቶች አቃጥለዋል። ማረሚያ ቤት ሰብረው እስረኞችን ለቀዋል” የሚል ይገኝበታል።
“በአጣዬ፣ በማጀቴና ሌሎች የሠሜን ሸዋ አካባቢዎች ያሉ አርሶ አደሮች፣ የተቃጣባቸው ጥቃት ከፍተኛ ቁጣ ውስጥ አስገብቷቸዋል፡፡ በወሰዱት እርምጃም ሽብር ፈጣሪዎችን ካሰቡበት እንዳይደርሱ አድርገዋል። በማድረግም ላይ ናቸው” የሚል ሌላ ወቅታዊ መልዕክትም የደረሰን ሲሆን፣ እስከ ቅርብ ሰዓት ከዓይን እማኞች ሲደርሱን ከነበሩ መልዕክቶች “የአካባቢው ነዋሪ ከትላንት ምሽት 4 ሰዓት ጀምሮ የድረሱልን ጥሪ ማሰማቱን፣ አጣዬ ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶ ብዙ ንፁሀን የሞትና የአካል ጉዳት ሰለባ ሆነው መዋላቸውን፣ በማጀቴም በተመሳሳይ እስከ 6 የሚደርሱ ንፁሀን መገደላቸውን፣ በአጣዬ ሆቴሎች እንደተቃጠሉና ቤቶች እንደተዘረፉ፣ አሁን የፀጥታ አካላት መግባታቸውን፣ የአጣዬ 01 ቀበሌ ሙሉ በሙሉ በኦነግ ሸኔ ቁጥጥር ስር መሆኑን፣ ከደብረ ብርሃን ጀምሮ የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ መቋረጡን” ለመረዳት ተችሏል።
ኢትዮጵያ ነገ ከመንግስት በኩል ጎዳዩን በሚመለከት ምላሽ ይሰጡኛል ያለቻቸውን አካላት በስልክ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም ሊሳካ አልቻለም።
ይሁንና፣ ጉዳዩን በሚመለከት “እነማን ምን አሉ?” በሚል ባደረግነው ዳሰሳ፣ የአማራ ክልል ኘሬዝዳንት የህግ አማካሪ የሆኑት አቶ ውብሸት ሙላት “አጣዬ እና አካባቢው ኦነግ እንዲህ ሲፈነጭ፣ ከተሞቹን ከብቦ በተኩስ ሰላማዊ ዜጎችን ሲገድል የፌደራል ፖሊስ ሰንበቴ ከተማ ነበረ። ሰንበቴ የፌደራል ፖሊስ እያለ ነው ይህ ሁሉ የተፈጸመውና የሚፈጸመው! ሰንበቴ እና አጣዬ የሚራራቁት 6 ኪሜ ብቻ ነው!” በማለት ያሰፈሩትን ቁጭት አዘል አስተያየት አግኝተናል።
አቶ ውብሸት በሌላ አስተያየታቸውም “በአጣዬና አካባቢው የኦነግ ወታደሮች በድንገት አልተከሠቱም። ከሰማይ አልወረዱም። በገሃድና በጠራራ ሰላማዊ ኗሪዎች ላይ ተኩስ መክፈት ከጀመሩ እንኳን ቀናት ተቆጥረዋል። ለዚህ ደግሞ ማጀቴ ላይ ያደረጉት በቂ ማስረጃ ነው። በአጠቃላይ በአካባቢው የኦነግ ወታደር በግላጭ መንቀሳቀስና መታየት ከጀመሩ ቀናት ተቆጥረዋል። አይደለም መንግሥትና (የፌደራሉም የክልሉም-ደኅንነቱም ፖሊሱም ወታደሩም ሁሉም) ይቅርና እኔ በግሌ፣ አንድ ተራ ግለሰብ፣ አጣዬና አካባቢው በአካል ሳልኖር ወይም ሳልሔድ እነዚህን መረጃዎች ሰምቻለሁ። አጣዬና አካባቢው ኦነግ በዚህ መጠን በዐደባባይ ሲፈነጭ ጥቃት ለመፈጸም ሲዘጋጅና ሲፈጽም የፌደራልም የክልሉም መንግሥቶች ለምን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ሳይፈልጉ ቀሩ? የፌደራል ፖሊስ በአካባቢው እያለ በተለይ ትናትና ለምን ወደ አጣዬ ሳይገባ አደረ? አጣዬና አካባቢው ስለተከሠተው የኦነግ የግላጭ ጥቃት በአግባቡ ሊመረመር ይገባል!” ብለዋል።
“አጣዬ ከሚገኝ የአማራ ክልል ልዩ ሀይል ጋር የአንድ ደቂቃ የስልክ ቆይታ ነበረኝ” ያሉ አንድ ሌላ አክቲቪስት በበኩላቸው “በአካባቢው ልዩ ሀይል አልነበረም ወይ እንዴት ይህ ሊፈጸም ቻለ? በማለት ለጠየኩት ጥያቄ ልዩ ሀይሉ ሲመልስልኝ… ሶስት ሻለቃ ጦር ነበር ሁለቱ ለግዳጅና ስልጠና ወደ ጎንደር ተጠርተው ሄዱ። የኦነግ ታጣቂዎች ይህን በማሰብ የነበረው አንድ ሻለቃ ስለሆነ ዘልቀን አጣዬ እንግባ በማለት ለሊት ገብተው ተኩስ ከፈቱ። የቻለውን ተከላክለን ተኩሱን አስቁመን ነበር። ችግሩ ቦታው ተራራማ ስለሆነ እነሱ ለማጥቃት ይመቻቸዋል። በየተራራው ነው ያሉት፤ ያለን አማራጭ መንገዶቹን ዘግተን ሀይል ማስጨመር ነው። ያለነው ሙሉ ጦርነት ላይ ነው:: አሁን ተጨማሪ የአማራ ክልል ልዩ ሀይል ገብቷል። የተወሰነ ይቀራል እነሱም ይገባሉ…ብሎኛል” በማለት ገልፀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሰሜን ሸዋ “የአጣዬ ወገኖቻችን በኦነግ መጨፍጨፍ የመንግሥት ፈጥኖ አለመድረስ ነው” በሚል የደብረብርሃን ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞ ማሰማቱ ታውቋል።
ኦነግ ሸኔ በአጣዬ በከፈተው ጦርነት የተበሳጨው የደብረ ብርሃን ህዝብ ግልብጥ ብሎ እደባባይ በመውጣት ቁጣውንና ዝግጁነቱን በይፋ በገለፀበት በዛሬው ሰልፍ “እንዴት መንግስት የህዝቡን ደህንነት ማስከበር ያቅተዋል?” የሚል በቁጭት የተሞላ ጥያቄ በስፋት ተንፀባርቋል::