ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ መጋቢት 14/2013 ዓ.ም በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የመንግስታቸውን የአፈጻጸም ሪፓርትና በምክር ቤት አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ እና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በምክር ቤቱ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፣ በመቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ሰዓት የወሰዱ ማብራሪያዎችን የሰጡ ሲሆን፣ የምክር ቤቱ አባላት ላነሷቸው ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎችም ምላሽ ሲሰጡ አርፍደዋል።
የዛሬውን የፓርላማ ውሎ የተከታተለው የኢትዮጵያ ነገ ዘጋቢ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰጧቸው ምላሽና ማብራሪያዎች መካከል ዋና ዋናዎቹን እንዲህ አቅርቦታል:-
* የአማራ ልዩ ሀይልን በሚመለከት፤
“…ችግሩ የሕዝብ እና የልዩ ኃይል ሳይሆን ችግር በማራገብ እንጀራ የሚጋግሩ የፖለቲካ ነጋዴዎች ነው። ሕዝቡ እኛ ከመፈጠራችን በፊትም ተዋዶ እና ተዋልዶ አብሮ ነበር… ከሹመኛ እስከ ፖለቲከኛ፣ ከምክር ቤት ጠያቂ እስከ ማኅበረሰብ አንቂ ጉዳዩን አታጋግሉት።…
የአማራ ልዩ ኃይል በሕግ ማስከበር ዘመቻው መሬቴን ላስመልስ ብሎ ተደራጅቶ ወደ ዘመቻው እንደገባ የሚያስመስሉ አሉ፣ ይህ ስህተት ነው፡፡ …ሶሮቃና ቅራቅር ላይ ጦርነቱን የጀመረው አማራ ልዩ ኃይል አይደለም፤ ልዩ ኃይሉ ባሕርዳር ተቀምጦ ነው ጦርነት የተከፈተበት ነው፡፡ ሀገር እየጠበቀ ያለው መንግሥት የሰጠውን ተልእኮ ለመፈጸም ነው የዘመተው…የአማራ ልዩ ኃይል ከሌላ ቦታ እንደመጣ አድርጎ መሳል ተገቢ አይደለም። …የአማራ ልዩ ኃይል መንግስት ከፈለገው ጅግጅጋ ጫፍ ላይ ማሰማራት ይችላል፡፡ የአማራ ልዩ ኃይል ጥፋት አጥፍቶ ከሆነ በሕግ ይጠየቃል”
* ከሰሞኑ በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን አካባቢዎች ተፈጠረውን የጸጥታ ችግርና ኦነግ ሸኔን በሚመለከት፤
“አሁን በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተበት አካባቢ በወሎ ክፍለ ሀገር የነበረ አንድ ህዝብ የነበረ ነው፣ የተጋባ ህዝብ ነው፣ ይህን ለመለያየት የሚደረገውን ስራ አጋዥ መሆን የለብንም፣ ይህ የጠላት ስራ ነው። …ኦነግ ሸኔ ከሁሉም በላይ የገደለው አሮሞን ነው፣ የሰው ጠላት ነው፤ የጁንታ ቡችላ ሆኖ ሰው የሚድገል እንጂ ብሄርን ለይቶ ብቻ የሚገድል አይደለም፣ ኦነግ ሸኔ እየገደለ ያለው አማራን ብቻ አይደለም፣ የተሳሳተ መረጃ መሰራጨት የለበትም።…ኦሮሞ እና አማራ ከተባላ ኢትዮጵያ የምትባል አገር የለችም ማለት ነው፤ የትኛዋን አገር ልታስተዳድሩ ነው ህዝቡን የምታባሉት፣ የፖለቲካ ነጋዴዎች ከዚህ ልትወጡ ይገባል፡፡… ኦሮሞ እና አማራን ለማባላት በጀት መድበው የሚለፉ ሀይሎች እያሉ ለእነዚያ ግብዓት መሆን የለብንም። ጉዳዩን የኦሮሞ እና የአማራ ጉዳይ ማድረጉ ለጠላት መሳሪያ መሆን ነው፣ ይህን አውቃቹህ ልትንቀሳቀሱ ይገባል”
* ጠቅላይ ሚንስትሩ ዛሬ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የኤርትራ ወታደሮች የትግራይን ድንበር መሻገራቸውን በሚመለከት ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስም “የኤርትራ ወታደሮች የትግራይን ድንበር መሻገራቸውን” ለመጀመሪያ ጊዜ አምነዋል።
“በትግራይ ክልል ለተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እጃቸው ያለበት የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች ተጠያቂ ይሆናሉ” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፣ “ጁንታውን እንዲያጠቃ እንጂ ሰላማዊ ሰው እንዲያጠቃ የተላከ ወታደር የለም። በአስገድዶ መድፈር እና በሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚጠረጠር ወታደር በሕግ ይጠየቃል። በኤርትራ በኩል ስለተፈጸመው ችግር ኤርትራ በራሷ በኩል አጥርታ እርምጃ ትወስዳለች” ብለዋል።
* የሱዳን መሬት ወረራን በተመለከተ፤
“ሱዳንን በሚመለከት በዲፕሎማሲው ሰፊ ስራ እየሰራን ነው፡፡ ከሱዳን ጋር ጦርነት መጀመር አያስፈልግም ኪሳራ ነው፤ ሱዳንም አሁን ባለው ሁኔታ ከጎረቤት አገር ጋር ለመዋጋት በሚያስችል ቁመና ላይ አይደለም ያለችው፡፡ ብዙ የውስጥ ችግር አለባት፤ ኢትዮጵያም አሁን ባለው ሁኔታ ከሱዳን ጋር ለመዋጋት ብዙ ችግር አለባት፤ ስለዚህ ጦርነቱ ለሁለታችንም አያስፈልገንም።… ችግሩን በንግግር፣ በውይይት፣ በድርድር መፍታት ነው የሚያስፈልገው። ያ ተጀምሯል… ከአጼ ሚኒሊክ ዘመን ጊዜ ጀምሮ እስከአሁን ድረስ በንግግር ያለጉዳይ ነው፤ በእኛ በኩል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ኮሚቴ በእነሱ በኩልም በሚኒስትር የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራበት ነው።… ላለፈው አንድ አመት ያህል ስራ ስንሰራ ቆይተናል። አሁን ይሄ የሕግ ማስከበሩ ስራ ሲጀመር ነው የተቋረጠው፡፡ በዚህ ወቅት እነሱ ወደማይገባ መንገድ ሄዱ። እኛ ለዚህ የሰጠነው ምላሽ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ውጊያ አያስፈልግም፤ በውይይትና በድርድር እንፍታው ነው ያልነው። ይሄን ስንልም የእኛ አርሶ አደሮች ተፈናቅለዋል፤ ማሳቸው ተቃጥሏል፤ ቤታቸው ተቃጥሏል፤ በደል ደርሶብናል። ያም ሆኖ አንዋጋ እያልን ነው፤ ውጊያ ስለማይጠቅመን። …ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ሱዳን ከሌሎች ጋ ወዳጅነት ፈጠረች የተባለው ሱዳን ከማንኛውም አገር ጋ ወዳጅ መሆን ትችላለች፤ የኢትዮጵያ ጠላት መሆን ግን አትችልም።… ሱዳን የሚለው ቃል በአርብኛ እና ኢትዮጵያ የሚለው ቃል በግሪክኛ አንድ ነው ትርጉሙ፤ አንድ ሕዝብ ነው፤ የትም አገር ሄዳችሁ ሱዳናዊ ብታዩ በአማርኛ ነው የምታወሩት። …ኢትዮጵያን ከሱዳን መለየት አይቻልም፤ ከማንኛውም አገር ጋ ወዳጅ መሆን ይቻላል፤ ችግር የለውም፡፤ እኛም ከሌሎች አገራት ጋር ወዳጅ መሆን እንችላለን፤ የሱዳን ጠላት መሆን ግን አንችልም። በብዙ ነገር አንድ ሕዝቦች ነን። ተከባብረንና ተዋደን የኖርን ወደፊትም አብረን የምንኖር ሕዝቦች ነን”
* ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገሪቱ አየተባባሰ የሄደውን የኑሮ ውድነትና የሸቀጦች ዋጋ ግሽበት በሚመለከት ምላሽ ሲሰጡ “መንግስት ሊሻገረው ያልቻለው ጉዳይ የዋጋ ግሽበትን ነው” ብለዋል።
መንግስት የዋጋ ግሽበትን ሊሻገረው እንዳልቻለና ዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል እየጎዳ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የዋጋ ግሽበት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች የምግብ ነክ ወጪ ከ54 እስከ 60 በመቶ ገቢያቸውን ይወስድባቸዋል፣ ቤት ኪራይ እና አልባሳት ደግሞ ለዋጋ ንረቱ መንስኤዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
“ሰው ሰራሽ እጥረት የሚፈጥሩ ነጋዴዎች አሉ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የምርት እጥረት እና አለም አቀፍ ሁኔዎችም ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ችግሮች ናቸው ብለዋል፡፡ መንግስት በኢኮኖሚው ላይ የሚፈጠረውን የዋጋ ግሽበት በተጠና መንገድ ለመፈታት የሚያስችሉ ራሳቸውን የቻሉ ግብረ ኃይሎች አቋቁሞ እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
* ግብርና ቴክኖሎጂ እና ጤናን በሚመለከት፤
“ዓለም ላይ ያላቸውን ደመናን ወደዝናብ የቀየሩ አገራት ጥቂት አገራት ናቸው፤ እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ መቼ አየዋለሁ ብዬ ከምቀናባቸው ነገሮች አንዱ ይሄ የተከማቸ ደመና በተመረጠ ሁኔታ ማዝነብ መቻልን ነው። አሁን ኢትዮጵያ ይሄንን አቅም ገንብታለች።
ባለፉት ሳምንታት በሰሜን ሸዋ እና በጎጃም ያያችሁት ዝናብ የተፈጥሮ ሳይሆን እኛ ያዘነብነው ነው። በግልጽ በሚቀጥሉት ሳምንታት እናስመርቀዋልን፤ ወይንም እናስጀምረዋለን። ኢትዮጵያ ደመናዋን ተጠቅማ ዝናብ ማዝነብ ችላለች፤ …አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ከተጀመረ ባጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ለውጥ አምጥተናል። በተለይ በግብርናው ዘርፍ። በጤና ዘርፍ በካንሰር በጣም አመርቂ ውጤት አግኝተንበታል።… በአዲስ አበባ ከተማ ግድያዎች እየተበራከቱ በመምጣታቸው፣ በቴክኖሎጂ በመታገዝ በቅርቡ በዝርዝር የምንገልጸው ይሆናል”,
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በዛሬ መጋቢት 14/2013 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሏቸው በሌሎች በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፋፊ ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል።