ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በሀዋሳ ጉሙሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በኩል ወደ አዲስ አበባ ሊገቡ የነበሩ ሁለት የቴሌኮም ማጭበርበሪያ መሳሪያዎች መያዙን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡
ሁለቱ የቴሌኮም ማጭበርበሪያ መሳሪያዎች እያንዳንዳቸው 64 ሲም ካርዶችን የሚይዙ መሆናቸውንና እና ለዚሁ የቴሌኮም ማጭበርበሪያ ተግባር ማስፈጸሚያነት የሚውሉ የተለያዩ አጋዥ መሣሪያዎች አብረው መያዛቸውን የገለጸው ኤጀንሲው፣ ብዙ ጊዜ የቴሌኮም ማጭበርበሪያ መሳሪያዎች ወደሀገር ውስጥ እንዲገቡ የሚደረጉት በህገ-ወጥ መንገድ እንደሆነና ድርጊቱ የሚፈጸመውም የራሳቸውን የኢኮኖሚ ትርፍ መሠረት አድርገው በሚሰሩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች መሆኑንም አመልክቷል፡፡
የቴሌኮም ማጭበርበሪያ መሳሪያዎቹ ወደሀገር ውስጥ ገብተው ለመጡበት ዓላማ ቢውሉ ኖሮ፣ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሱ እንደነበረ የጠቀሰው ኤጀንሲው፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ በሰራው ስራ፣ 19 ሚሊዮን ብር የሚገመት የሀገር ሀብት ከኪሳራ መታደግ መቻሉን ተናግሯል።
ከዚህ ቀደምም ለስለላ አገልግሎት የሚውሉ ካሜራዎች፣ ለተለያየ አሉታዊ ተልዕኮ መዋል የሚችሉ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ኮምፒውተሮች፣ ድሮኖች፣ የኮሙዩኒኬሽን እቃዎች እና ሌሎች በርካታ የቴሌኮም ማጭበርበሪያ መሳሪያዎች በህገወጥ መንገድ ወደሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ከጉሙሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ጋር በመተባበር የቁጥጥር ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱንም ኤጀንሲው አስታውቋል።