የግድቡ ግንባታ 80 በመቶ መድረሱና ሲጠናቀቅም የቀጣናውን ኢኮኖሚ እንደሚያስተሳስር ተገለጸ!

የግድቡ ግንባታ 80 በመቶ መድረሱና ሲጠናቀቅም የቀጣናውን ኢኮኖሚ እንደሚያስተሳስር ተገለጸ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜናየውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ አስተባባሪ ምክር ቤት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር፣ በህዳሴው ግድብ የግንባታ ሂደት ላይ ከሃይማኖት ተቋማት ጉባኤና ከሲቪክ ማኅበራት ጋር እያካሄደ ባለው የምክክር መድረክ፣ የህዳሴው ግድብ አጠቃላይ የግንባታ ሂደት ከ80 በመቶ በላይ መድረሱን የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።

“ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ እየተከተለችው ያለችውን አካሄድና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ግልፅ ለማድረግ፣ እንዲሁም ሕዝቡን በተቋማቱ በኩል ተደራሽ ማድረግን ያለመ ነው” በተባለለት የውይይት መድረኩ፣ የህዳሴው ግድብ ሕጋዊ ሂደቶችና የድርድር አካሄዶች ተነስተው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያዎች ገለፃ የተደረገ ሲሆን፤ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የግድቡን ግንባታ ሂደት አስመልክቶ በሰጠው ማብራሪያም “የህዳሴው ግድብ አጠቃላይ የግንባታ ሂደት ከ80 በመቶ በላይ ደርሷል” ሲል መግለፁን ለማወቅ ተችሏል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች የሚኒስትሩ አማካሪ የሆኑት አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ በበኩላቸው “በዓባይ ውኃ ላይ ግብጽና ሱዳን ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር የሚያራምዱት ፍትሐዊ ያልሆነ አቋም ነው” በማለት ግብጽና ሱዳን ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር የሚያራምዱት ፍትሐዊ ያልሆነ አቋምና የሚከተሉትን የውኃ ፖሊስ መነሻ በማድረግ በሰጡት ገለጻ፣ ሀገራቱ በዓባይ ውኃ የበላይነትን ለመያዝ በተለያዩ ጊዜያት ያደረጉትን እንቅስቃሴን አብራርተዋል።

በተያያዘ፣ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የቀጣናውን ሀገራት በኢኮኖሚ እንደሚያስተሳስር ረዳት ፕሮፌሰር አንዳርጋቸው ተስፋሁን ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለችው ታላቁ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለቀጣናው ሀገራት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጠቀሜታ አለው። በዓለማችን ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር የሚሻገሩ በርካታ ወንዞች አሉ፡፡ ሀገራትም ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ለትራንስፖርት፣ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት፣ ለመስኖ ልማት፣ ለከተሞች ውኃ አቅርቦትና ለሌሎችም ተግባራት ይገለገሉባቸዋል” ያሉት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር አንዳርጋቸው ተስፋሁን፣ ኢትዮጵያ በዋናነት ታላቁን የህዳሴ ግድብ እየገነባች ያለችው ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት መሆኑን ጠቅሰው “ግድቡ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለዜጎቻቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ማድረግ ላልቻሉ የጎረቤት ሀገራት ጭምር አገልግሎት ይሰጣል። ከኤሌክትሪክ ጠቀሜታው በተጨማሪ የንግድና የመዝናኛ ማዕከል በመኾን ለቀጣናው ሀገራት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያስገኛል። ይህ ሂደትም የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ትብብራቸውን ለማጠናከርና ለመደጋገፍ ያግዛቸዋል” ብለዋል።

LEAVE A REPLY