ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ዛሬ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጹ እንዳስታወቀው፣ በእነ እስክንድር የክስ መዝገብ ጉዳዩን በዋነኛነት የያዘው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አስቀድሞ በሰጠው ቀጠሮ መሰረት፤ ዛሬ በዋለው ችሎት የምስክር አቀራረብ ሒደት ላይ የግራና ቀኝ የህግ ክርክር በመመርመር ፍ/ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል።
“የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዐቃቤ ህግ በእነ እስክንድር ነጋ ላይ እንዲመሰክሩ ያዘጋጃቸው 16 ምስክሮች በግልጽ ችሎች እንዲመሰክሩ ወስኗል” ያለው ፓርቲው “የከፍተኛው ፍርድ ቤት አንደኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም ውሳኔውን ያሳለፈው፤ ምስክሮች፣ ለደህንነታቸው ሲባል በዝግ ችሎት ከመጋረጃ ጀርባ እንዲሰሙ በዐቃቤ ህግ በኩል የቀረበውን ጥያቄ በተከሳሾች እና በደጋፊዎቻቸው በኩል ለዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ምንም አይነት በቂ የሆነ በምክንያት እና በእውነት አስረጂ የሆኑ የደህንነት ስጋት አላገኘሁም፤ በማለት ፍ/ቤቱ የዐቃቤ ሕግ የመጋረጃ ጀርባ ምስክርነት ጥያቄ ውድቅ አድርጓል” ሲል አስታውቋል።
የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ሐምሌ 8 እና 9 እንዲሁም ሐምሌ 14፣15እና 16 በአምስት ቀናት ውስጥ እንደሚሰማ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሰጠቱንም ባልደራስ አመልክቷል።