ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመጋቢት 2011 ጀምሮ እንዳይበር የታገደውን ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ዛሬ ለ4 ሰዓት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች አበረረ፡፡
አየር መንገዱ ወደ ታንዚያ ኪሊማንጃሮ ተራራ ለማብረር የነበረውን ዕቅድ ሰርዞ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ሲበር የዋለው። በዚህም አውሮፕላኑ በኢትዮጵያ አየር ክልል ውስጥ ለ4 ሰዓት በረራ አድርጎ አዲስ አበባ ማረፉን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ አየር መንገዱን ጠቅሶ ዘግቧል።
የጀርመን ድምፅ በዘገባው ወደ ኪሊማንጃሮ ለማድረግ ያቀደውን በረራ የተሰረዘው በአየር መበላሸት ምክንያት ሲሆን በዝቋላና በባሌ ተራሮች አናት ላይ ሲበር ነበር ብሏል፡፡
በመጋቢት 2011 ከአዲስ አበባ 157 ሰዎችን አሳፍሮ ወደ ኬንያ ለመብረር በተነሳ 6 ደቂቃ ውስጥ መከስከሱን ተከትሎ ነበር የአውሮፕላኑ ሞዴል በዓለም ዐቀፍ ደረጃ እንዳይበር ታግዶ የቆየው፡፡
አየር መንገዱ ከሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላንን የተለያዩ አገራት ማብረር መጀመራቸውን ጠቅሶ እርሱም ወደ በረራ ለመመለስ ቀናት ብቻ እንደቀሩት ማሳወቁ ይታወሳል፡፡