በሞያሌ በፀጥታ ኃይሎች እና በኦነግ ሸኔ መካከል ግጭት ተከስቶ እንደነበረ ተገለጸ

በሞያሌ በፀጥታ ኃይሎች እና በኦነግ ሸኔ መካከል ግጭት ተከስቶ እንደነበረ ተገለጸ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገር ኬንያ ጋር በምታዋስነው የንግድ መዳረሻዋ ሞያሌ ከተማ አካባቢ፤ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር (ኦነግ) ብሎ በሚጠራው ቡድን መካከል ግጭት ተከስቶ እንደነበረ የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣን አስታወቁ።

ባለሥልጣኑ ግጭቱ ከቅዳሜ ምሽት እስከ እሑድ አጥቢያ ድረስ ዘልቆ እንደነበርም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እኚህ ባለሥልጣን እንደገለፁት፤ ከመንግሥት ኃይሎች ጋር የተኩስ ልውውጥ ያደረጉት ታጣቂዎች መንግሥት ሸኔ እያለ የሚጠራቸው የኦሮሞ ነፃነት ጦር አባላት ናቸው ያሉ ሲሆን፤ ነገር ግን የደረሰውን ጉዳት ከመናገር ተቆጥበዋል።

የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ ኦዳ ታርቢ፤ በደቡባዊ ኦሮሚያ መልካ ለሚ በሚባል ሥፍራ የመንግሥት ኃይሎች “ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል” ሲሉ ዛሬ በትዊተር ገጻቸው ላይ ፅፈዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከቀናት በፊት “በአሸባሪው የሸኔ ቡድን ላይ የማያዳግም እርምጃ እየተወሰደ ነው” ሲል በፌስቡክ ገፁ ማስታወቁ ይታወሳል።

የመከላከያ ሠራዊት የደቡብ ዕዝ የኋላ ደጀን አስተባባሪ ኮሎኔል ግርማ አየለን ዋቢ አድርጎ “የሽብር ቡድኑ ሲጠቀምባቸው የነበሩ የተለያዩ ዓይነት የጦር መሣሪያዎች እና ተተኳሽችን ጨምሮ ለሽብር ቡድኑ አመራሮች ሲጓጓዝ የነበረ መድሃኒት በቁጥጥር ሥር ውለዋል” ብሏል።

ኮሎኔሉ “የአከባቢው ማሕበረሰብ የሽብር ቡድኑን እኩይ ሴራ በማጋለጥ እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በመስጠት በኩል የተወጡት ሚና ከፍተኛ ነው” ማለታቸውንም ዘግቧል።
በኦነግና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መካከል በተለይ በደቡብና ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭት ሲቀሰቀስ ይህ የመጀመሪያው አለመሆኑም ይታወቃል።

LEAVE A REPLY