እንቁ ጣጣሽ – ምን አመጣሽ ?! || አሥራደው (ከፈረንሳይ)

እንቁ ጣጣሽ – ምን አመጣሽ ?! || አሥራደው (ከፈረንሳይ)

  • ዞረሽ ዞረሽ ! ተሽከርክረሽ – ተሽኮርምመሽ፤
    ተሽቀርቅረሽ ! ተሞናሙነሽ – ተኳኩለሽ፤
    ቀናት ቆጥረሽ_ ወራት አዝለሽ – ዓመት ሞልተሽ፤
    እኛን እረስተሽ_ ካለው ውለሽ – ካለው ቀብጠሽ፤
    እንዳልነበርን – እንደሌለን ፤
    አፈር ትቢያ – ጭቃ ለብሰን፤
    ምናምንቴ – ከንቱ ሆነን፤
    ውልብ ላንል – በትውስታሽ፤
    ከምናብሽ_ ከመዝገብሽ – እኛን ፍቀሽ፤
    እነ አባባ – እነ እማማን፤
    ወንድም ጋሼ – እ’ት ዓለምን፤
    ዘመድ አዝማድ – ጎረቤቱን፤
    ሁሉን ትተሽ – ሁሉን ረስተሽ፤
    ቀን አስልተሽ – ወራት ቆጥረሽ ፤
    ዓመት ሞልተሽ – ዘመን አዝለሽ፤
    እንቁጣጣሽ ምን አመጣሽ ? – ለምን መጣሽ ?!
    ምን ትሠሪ ? – ምን ትፈጥሪ ?
    ምን ታወሪ ? – ምን ትነግሪ ?
    እኮ ለምን ?! ተናገሪ !!
    ለወገኔ ለተራበው – በደል ጥቃት ላባዘነው፤
    ኑሮ ጨሶ ለሚያጨሰው – በ’ንባዎቹ ለሚያጠቅሰው፤
    ጠኔ ጥሎት ለወደቀው – በጎዳና ለሚተኛው
    ለእኔ ብጤ_ ለሷ ብጤ _ ለኛ ብጤው፤
    እንቁጣጣሽ – ምን አመጣሽ ?!
    ተጠየቂ እስቲ እንስማሽ !!
  • መሬት ነጥቀሽ – አርሶ አደሩን፤
    ሥራ ነፍገሽ – ላብ አደሩን፤
    ለነጥቆ አደር ወለል አርገሽ _ በር ከፍተሽ፤
    ለዘራፊ፤ ለነጣቂ፤ ለሙሰኞች _ አዠርግደሽ፤
    ብዙሃኑን አስጨንቀሽ – በኑሮ ጣር አጎሳቁለሽ፤
    አንገላተሽ – ገለሽ ቀብረሽ፤
    ከደላው ጋር – እያሽቃበጥሽ፤
    ቀን አስልተሽ – ወራት ቆጥረሽ፤
    ዓመት ሞልተሽ – ዘመን አዝለሽ፤
    እንቁጣጣሽ ለምን መጣሽ ?! ምን አመጣሽ ?
    ተናገሪ እሲቲ እንስማሽ ?!
    ምን ትሠሪ ? ምን ታወሪ ?
    ምን ትፈጥሪ ምን ትነግሪ ?
    እኮ ለምን ?! ተናገሪ !!
    አንድ ቀን !!
    ኑሮን ሳይኖሯት፤ በቀዳዳ ብቻ እያጮለቁ፤ ለብዙ ዓመታት ሲመለከቷት ለቆዩት፤ ጎስቋሎች
    ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ መታሰቢያ ትሁንልኝ

LEAVE A REPLY