ሻሸመኔ ነው ያለነው || ያሬድ ሹመቴ

ሻሸመኔ ነው ያለነው || ያሬድ ሹመቴ

የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ እንደታጎለ ነው።

~ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናቸውን ጥሪ ተቀብለው ለክርስትናችን ምሳሌ የኾኑ ሰማዕታትን ቤተሰቦች ለመጠየቅ እና ለቅሶ ለመድረስ ሻሸመኔ ደርሰናል

በርካቶች በግፍ ወደ ተገደሉበት የሻሸመኔ ቅዲስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ደጃፍ ደረስን። የቤተክርስቲያኑ በሮች ተጠርቅመዋል። ቅጥር ጊቢው ውስጥ ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም። ጸጥ ረጭ እንዳለ ነው። ከተዘጋው የግቢ በር ወዲህ መንገዱን አቋርጦ የሚያልፍ ምዕመን ኹሉ ዳጃፉን እየተሳለመ ያልፋል። እኛም እንዲሁ አደረግን።

ከተዘጋው በር ሻገር ብሎ ሌላ በመሰራት ላይ ወይም በእድሳት ላይ ያለ የሚመስል ዋና መግቢያ በር ዙሪያው በቆርቆሮ ታጥሮ ይታያል። እሱም ዝግ ነው።

ወደ ሰማዕቱ አባታችን ቀሲስ ሐረገወይን ቤት ሊወስዱን በስልክ ቀጠሮ ያስያዝናቸው ካሕን ጋር ተደዋወልን። እኛ የጠበቅነው ከቤተ ክርስቲያን ወጥተው ያገኙናል ብለን ነበር። እሳቸው ግን ከመንገደኛው መሐል ተራምደው መጥተው አገኙን። መስቀላቸውን ተሳልመን እየተጨዋወትን ወደ ለቅሶ ቤት አመራን።

ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ከዚህ ቀደም በ4 መደብ ሰርክ ቅዳሴ የሚቀደስበት ምዕመናን ዘውትር የማይለዩበት ደብር ነበር። አሁን ግን ቅዳሴ ታጉሎ የቤተ መቅደሱ በር ከተዘጋ ሰነባበተ።

ካህናቱ በየቦታው ተበታትነዋል። ቤተ ክርስቲያኑ በማን ቁጥጥር ስር እንደኾነ የታወቀ ነገር የለም። የክርስቲያኖች ደም የፈሰሰበት የቅዱስ ሚካኤል ደብር ቅጥር ጊቢ የሰማዕታቱ ደም በውሃ ሲታጠብ እንደቆየ ሰማን።

ክቡር የኾነው የሰው ደም የፈሰሰበት ቤተ ክርስቲያን በድጋሚ ጸሎት ተደርጎበት በብጹዓን አባቶች ሳይባረክ ወደ አገልግሎቱ የሚመለስ ካህንም ኾነ ምዕመን እንደማይኖር የታወቀ ነው።

የሰማዕቱ ቀሲስ ሐረገወይን ቤተሰቦች ሰፈር ደረስን፤ አካባቢው በትክክል የእሳቸው ቤት መኾኑን እርግጠኛ ብንኾንም እንኳ ግራ እና ቀኝ ድንኳን ስንፈልግ ትንሽ ተዟዟርን፤
በኋላም አንዲት መንገደኛን “ለቅሶ ቤቱ የቱ ጋር ነው?” ስንል ጠየቅናት።
“የቄሱን ነው?”
“አዎ”
“ከዚህ በታች ወርዳችሁ በግራ በኩል ስትታጠፉ ነው”

አመስግነናት ባሳየችን አቅጣጫ ታጠፍን፤ ለቅሶ ቤቱ አልታየንም። በኋላ አንድ ገርበብ ብሎ የተከፈተ የብረት መዝጊያ በር ያለው ግቢ አየን። ወደ ውስጥ ገባን። ጊቢው ውስጥ የለቅሶ ቤት ምልክት የሚያሳይ ነገር የለም።

ከውስጥ ሁለት እናቶች ወደ አንድ ሰርቪስ በር አመላክተው አስገቡን። ጠባብ አንዲት ክፍል ቤት ውስጥ የሰማዕቱ ቀሲስ ሐረገ ወይን ባለቤት ወ/ሮ ቃልኪዳን እና እሳቸውን ለማጽናናት የመጡ አንድ የ85 ዓመት መነኩሴ ብቻ ቤቱ ውስጥ አገኘን።

ዝርዝሩን ለጊዜው እናቆየውና ለቅሶ ደርሰን ከወይዘሮ ቃልኪዳን ጋር ተመካክረን ሀዘናችንን ገልጸን ተመለስን። የሁለት መንታ ልጆች እናት የኾኑት ወ/ሮ ቃልኪዳን መደገፍ በእጅጉ የሚገባቸው እንደኾኑ ይሰማናል። ይህንን ማድረግም ትልቅ በረከት ነው።

የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስደዳደር ጉባዔ በትላንትናው ዕለት ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት የሰማዕታቱን ቤተሰቦች ለማቋቋም እና በህክምና ላይ ያሉትን ለመርዳት ዓለም አቀፍ የልገሳ አሰባሳቢ ኮሚቴ በአስቸኳይ ተቋቁሞ የእርዳታ ማሰባሰቢያ ቁጥሮች እስኪያሳውቀን ድረስ እንጠብቃለን።

የሰማዕታቱን ዝርዝር ታሪክ ሰምተናል።

ይቀጥላል….

LEAVE A REPLY