መስከረም 2012
ኅሊና የምትባል የመስከረምን ወፍ የመሰለች ቆንጆ ወጣት፣ በቀለ ገርባ የሚባል የወህኒ ቤት አክሊል አእምሮውን የደፈጠጠበት አምሮተኛና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓቢይ አህመድ በአንድ መድረክ ላይ ተገኛኙ፤ በቀለ ገርባ የሾህ አክሊሉን ደፍቶ ራሱ እሳት ጭሮ ባቀጣጠለው ሰደድ እሳት ምኑም ሳይቀር ተቃጠለና ደቀቀ!
ኅሊና በቀዘቀዙ ቃላት የአእምሮውንና የመንፈስዋን ኃይልና ምጥቀት መገንዘብ ለሚችል ሁሉ አሳየች፤ ዓቢይ አህመድ ሳይተነፍስ በታዛቢነት ተቀምጦ ነበር፤ የተቃጠለውን እያየ አዘነ፤ በኅሊና ቃላት ውበት፣ ምጥቀትና የተስፋ ጽንስ ውስጡ የረካ ይመስላል፤
በቀለ ገርባ ከኅሊና ግጥም የመረጣቸው ቃላት ታች ታቹን የሚያይ ሰው የሚያጋጥሙ ናቸው፤
በቀለ ገርባ በእሾህ አክሊሉ ስር የረበረበው መደላድል ለመሸከሚያ እንጂ ለማበጠሪያ አይረዳም፤ ያለፉት የአምባ ገነን ሥርዓቶች ተመልሰው እንዲመጡ በፍርሃት መልኩ ጠንካራ ፍላጎት ያለው በበቀለ ገርባ ውስጥ ነው፤ የጥንቱን ሥርዓት ለመመለስ የሚለው የበቀለ ገርባ ጩኸት ሀሳበ-ቢስ ነው፤ የጃንሆይን ነው? የደርግን ነው? የወያኔን ነው? ምናልባት ከቃሊቲ ለማንገሥ ታስቦ ይሆናል፤ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አይጥላትም፤ ሰውም አያሳጣትም፤ በቀለ ገርባን ፊት ለፊት ገጥሞ የሚቃወመውና በዝርር ከትግሉ ሜዳ የሚያስወጣው ቱባ ኦሮሞ የሆነው ታየ እሳት ለብሶ፣ እሳት ጎርሶ ብቅ አለበትና የኦሮሞን ሰውነትና ኢትዮጵያዊነት በቁመቱ ልክ አሳየው!!