የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም

በወልዲያ ዮንቨርስቲ በተከሰተ ብሔር ተኮር ግጭት ሁለት ተማሪዎች ተገደሉ

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው እና ባለፈው ዓመት በተለያዮ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብሔር ተኮር ግጭት ዘንድሮም ከጅምሩ ቀጥሏል:: ትናንት ቅዳሜ ምሽት በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት እስካሁን ድረስ ሁለት ተማሪዎች መሞታቸው ታውቋል።

መረጃውን ለኢትዮጵያ ነገ በስልክ ያደረሱን የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የብሄር መልክ በያዘው ግጭት የሁለት ተማሪዎች ህይወት ማለፉን እና በርካቶች መቁሰላቸውን በመናገር ላይ ናቸው:: ትናንት ምሽት በተፈጠረው ግጭት ሁለት ተማሪዎች ከመሞታቸው ባሻገር በርካቶች በከፍተኛ ደረጃ መቁሰላቸውንም ሰምተናል::

ከሆስፒታል  ታማኝ ምንጮች የተገኘ መረጃ ደግሞ ወደ ወልዲያ አጠቃላይ ሆስፒታል 15ተማሪዎች ምሽት ላይ ተጎድተው መምጣታቸውን ያረጋግጣል:: በተማሪዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ከቀላል እስከ ከባድ መሆኑን የጠቀሱት ምንጮች ጉዳቱ ያጋጠመው በድብደባ  እንደሆነም አመላክተዋል።

ትናንት ምሽት በዮንቨርስቲው ተማሪዎች መሀልየተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በተፈጠረባቸው የደህንነት ስጋት ከዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ለመውጣት የሞከሩ ተማሪዎች ከግቢው እንዳይወጡ መከልከላቸውን ያነጋገርናቸው ተማሪዎች ለኢትዮጵያ ነገ ገልጸዋል።

 “ትናንት የተፈጸመውን አይተን እንዴት ነው ዶርም ውስጥ የምንተኛው?” ያለው ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ የወልዲያ ዮንቨርስቲ ተማሪ “ማታ የተፈጸመው አሳዛኝ ችግር ዳግም ላለመከሰቱ ምንም ማረጋገጫ የለንም” በማለት ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ እንዳይወጡ መደረጉ አግባብ አለመሆኑን ይናገራል።

ግጭቱን አስመልክቶ የአማራ መገናኛ ብዙሃን የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደትንኤ መኮንን በመጥቀስ ትናንት ምሽት ተማሪዎች በጋራ እግር ኳስ በቴሌቪዝን ተመልክተው ሲመለሱ በተፈጠረ ግጭት ሁለት ተማሪዎች መገደላቸውን እና ስምንት ተማሪዎች ላይ ደግሞ ጉዳት መድረሱን በዜና እወጃው ይፋ አድርጓል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ላይ ተገኘተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ የሰላምና ሕዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር፤ በተማሪዎች መካከል የተነሳውን ግጭት የብሔር ለማስመሰል የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች አሉ በማለት ለማጣጣልና እውነታውን ለመሸፋፈን ሞክረዋል:: “በግጭቱ ተማሪዎች ተጎድተዋል። በአሁኑ ሰዓት ጉዳዩን አረጋግተነዋል። በዚህ ወንጀል ላይ የተሳተፉ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውለናል። አልፎም አማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በሙሉ ሰላም ለማደፍረስ የሚሠሩ አካላትን ለይተን እርምጃ ለመውሰድ እየተንቀሳቀስን ነው።” በማለትም መንግስታዊ አቋምን የተላበሰና በገሀድ ከታየው የተራራቀ መግለጫ ሰጥተዋል::

የኢጋድ አስቸኳይ ስብሰባ በሽግግር መንግሥት ላይ ከስምምነት ደረሰ

69ኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብስባ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው:: በተጀመረው ስብሰባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የወቅቱ የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀመንበር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የአባል ሃገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም የደቡብ ሱዳን ሠላም ተደራዳሪ አካላት መገኘታቸው ተረጋግጧል፡፡

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የስምምነቱ ፈራሚ አካላት ቀደም ሲል በፈረንጆቹ ህዳር 12 ቀን 2019 የሽግግር መንግስት ለመመስረት መስማማታቸውን ጠቁመው ፤ በዚህም በተካሄዱ ቀጣይነት በነበራቸው የክትትል ውይይቶች አበረታች ውጤት መመዝገቡን እና ለመንግስት ምስረታው ወሣኝ የሆኑ ቁልፍ ጉዳዮች እንዳልተፈቱ ግን አመላክተዋል።

በተለይም ውህድ የሆነ ሠራዊት መገንባት አለመቻሉ፣ ለመቋቋም አስፈላጊ የሆኑ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተሟልቶ አለመገኘት ስምምነት በተደረሰበት ቀነ ገደብ የሽግግር መንግሥት መመሥረት እንዳልተቻለ ነው የገለጹት::

ከዚህ በመነሳት የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባደረገው የምክክር ስብሰባ በኢንተቤ በዩጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ እና የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልቡርሃን አደራዳሪነት፥ በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና ዶክተር ሪክ ማቻር መካከል የሽግግር ጊዜ ምስረታዉን በመቶ ተጨማሪ ቀናት ለማራዘም የተደረሰው ስምምነት የሚበረታታ እርምጃ ነው ብለዋል። ሚኒስትሩ ስምምነቱ በሁሉም ፈራሚዎችና የሠላም ዋስትና ሠጭዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ መስራት እንደሚያስፈልግ፣ በተራዘመው ቀናት ቀሪ ተግባራትን አፋጥኖ መከወን እንደሚገባ አሳስበዋል::

“27 ዓመት ” የግጥም መድበል፣ ከጫኑት ሹፌርና ረዳት ጋር  በሱልልታ ፖሊስ ከታገተ 1ወር ሞላው

የ”27 ዓመት” የግጥም መድበል ደራሲ ሰብስቤ ሃሰን መጽሐፍቱን ለሥርጭት በሚያጓጉዝበት ጊዜ በሱሉልታ ከተማ ፖሊስ እንደታገቱበት ተናገረ። መጽሐፉ ከታገተ 1 ወር ከ10 ቀን አካባቢ እንደሆነም ደራሲው አስታውቋል።

“መጽሃፉ የመጀመሪያዬ ስለነበር በአካባቢው የሚያውቁኝ ሰዎች ይገዙኛል ብዬ አስጭኜ እየወሰድኩ ነበር” ያለው ደራሲው፤ ከታተመበት አዲስ አበባ ወደ ሌላ ስፍራ በመጓጓዝ ላይ ሳለ ሱሉልታ ላይ በፖሊሶች እንደታገተ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከመጽሐፎቹ ብቻ በተጨማሪ የጫኑት ሹፌርና ረዳቱ በፖሊስ መታሰራቸውንና መጽሐፉም መታገቱን ከ8 ቀናት በኋላ መስማቱን ጠቁሟል:: በወቅቱ መጽሐፉን ሌላ ዕቃ ከጫነ መኪና ጋር ልኮ እርሱ በሌላ መኪና ለመድረስ ተሳፍሮ እንደነበርም አስታውሷል።

በአዲስ አበባ ማንኩሳ ማተሚያ ቤት የታተመው ይሄው ’27 ዓመት’ የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ የታገተው በዋናነት የፖለቲካ ይዘት ሊኖረው ስለሚችል ይገምገም በማለት እንደሆነም ተናግሯል። እንደ ደራሲ ሰብስቤ ከሆነ በአጠቃላይ 2 ሺህ ቅጂ መጽሐፍትን ያሳተመ ሲሆን ወደ አካባቢው ለማጓጓዝ ጭኖት የነበረው መጽሐፍ 800 ኮፒ ነበር።

“መጽሐፌ መታገቱን እንደሰማሁ የአዕምሮ ንብረት ባለቤትነት ማስረጃ ይዤ ሄጄ ባሳያቸውም፤ አንተን አንፈልግህም ስንፈልግህ ትመጣለህ በማለት፣ መጽሐፉ ግምገማ ላይ መሆኑን ገልጸው አሰናበቱኝ” ብሏል:: መጽሐፉ ከመታተሙ በፊት በደቡብ ወሎ ባህልና ቱሪዝም አስገምግሜና ‘ይታተምለት’ የሚል የትብብር ደብዳቤም አስጽፌ ነው ያሳተምኩት የሚለው ደራሲው፤ መጽሐፉ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚያጠነጥን አስታውቋል።

’27 ዓመት’ የተሰኘው መጽሐፍ 152 ገጽ ሲኖረው ከ93 በላይ ግጥሞችን አካቷል። ደራሲው የሱሉልታ ፖሊስ የሰጠውን ምላሽ ይዞ የአዲስ አበባ ኦዴፓ ቢሮ በመሄድ ማመልከቱን፤ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም አቤት ማለቱንና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወደ ኦሮሚያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እንደላከው ተናግሯል።

ደራሲ ሰብስቤ “የኦሮሚያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በአግባቡ አስተናግዶ ጉዳዩን ለያዘችው ፖሊስ ደውሎ መጽሐፉ እንዲሰጠኝ ቢያዛትም የተለያየ ምክንያት እየደረደረችና መጽሐፉ ተገምግሞ አላለቀም በማለት ሳትፈቅድ ቀረች” በማለት የአሠራሩን ውስብስብነት ያማርራል።

ጉዳዩን ለያዘችው ፖሊስ መጽሐፍቱ የእሱ መሆናቸውን ባሳየበት ወቅትም “መረጃው እንደምትጽፍ እንጂ መጽሐፉ የአንተ መሆኑን አይገልጽም” የሚል ምላሽ እንደሰጠችው በመግለፅ መፍትሔ ሊያገኝ እንዳልቻለ አመላክቶ ፣ የመኪናው አሽከርካሪና ረዳቱም ሌላ ምርመራ ስላለባቸው በሚል እስካሁን እንደታሰሩ ሲሆኑ ፍርድ ቤት ሲሄዱም የሚሰጣቸው ምክንያት መጽሐፉ ተገምግሞ አላለቀም የሚል እንደሆነ ይፋ አድርጓል።

ከጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ጋር በነበረው ንግግር መጽሐፉን እንደሚያስለቅቁለት ቃል ቢገቡለትም፤ ይሄው ሳይለቀቅ ከ15 ቀናት በላይ መሆኑን ይናገራል። እስካሁን የሚሰጠው መልስ “ምርመራው አላለቀም” የሚል እንደሆነ የሚናገረው ሰብስቤ “ይሁን ከተባለስ ፖሊስ መጽሐፍ ይገመግማል ወይ?” ሲልም ግርምቱን አጋርቷል:: መጽሐፉን ለማሳተም እና ሌሎች ወጪዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ100 ሺህ ብር ላይ እንዳወጣበትም ደራሲው አስታውቋል::

የሦስት አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ከተማ ሦስት አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ዛሬ ተጀምሯል፡፡ የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ግንባታውምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ነው የተጀመረው፡፡

ከአውቶቡስ ተራ እስከ መሳለሚያ-18 ቁጥር ማዞሪያ፣በኮልፌ ቀለበት የሚያናኘውን መንገድ በይፋ ያስጀመሩት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ለፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ የሚባክን ጊዜ ፈጽሞ አይኖርም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከቦሌ ሚካኤል እስከ ቡልቡላ ካባ መግቢያ ድረስ የሚገነባውን የመንገድ ፕሮጀክት ያስጀመሩት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የንግድ ቢሮ ሓላፊ ኢንጅነር እንዳወቅ አብቴ  በበኩላቸውየከተማዋን እድገት የሚመጥን የመንገድ መሰረተ ልማት እንዲኖር የከተማ አስተዳደሩ በልዩ ትኩረት በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ከአውቶቡስ ተራ-መሳለሚያ-18 ማዞሪያ ኮልፌ 3 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን በቻይናው ሬል ዌል ሰቨንዝ ስራ ተቋራጭ አማካኝነት ግንባታው እንደሚከናወን ታውቋል:: ከቦሌ ሚካኤል ቡልቡላ ካባ ማውጫ የ5 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ደግሞ በሀገር በቀሉ አሰር ኮንስትራክሽን እንዲሁም ከለገሀር በጥላሁን ገሰሰ አደባባይ እስከ ጋዜቦ አደባባይ የሚደርሰውን የ1 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የመንገድ ፕሮጀክት በራስ ሀይል እንደሚገነባ በተደረገው ገለጻ ላይ ሰምተናል::

ኑሮ ከበደኝ ያለው የ22 ዓመቱ ፈረንሳዊ በአደባባይ ራሱን በእሳት አጋየ

የ22 ዓመቱ ፈረንሳዊ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እራሱን ካቃጠለ በኋላ ሕይወቱ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ መውደቁ ተሰማ። ወጣቱ በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ምክንያት የተነሳከሚማርበት ዩኒቨርሲቲ ፊትለፊት እራሱን አቃጥሏል:: ዘግናኝና ከባድ የሆነውን ይህን ደርጊት ከመፈጸሙ አስቀድሞ በፌስቡክ ገጹ ላይ መልዕክት አስፍሮ እንደነበር ተረጋግጧል።

‘የገደሉኝ’ የአሁኑና የቀድሞ የፈርንሳይ ፕሬዝደንቶች፣ የአውሮፓ ህብረት እና ቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች ናቸው በማለትም ወጣቱ ተጠያቂ አድርጓቸዋል ተብሏል።

የሊዮን ዩኒቨርሲቲ ተማሪው “በወር በሚሰጠኝ 450 ዩሮ (15ሺህ ብር ገደማ) ብቻ ህይወትን መግፋት ከብዶኛል” ሲልም ራሱን ለማጥፋት የተነሳበትን ምክንያት በፌስ ቡክ ገጹ አስፍሯል።

ወጣቱ ራሱን ካቃጠለ በኋላ ወደ ህክምና ቢወሰድም 90 በመቶ የሚሆነው አካሉ ከባድ ቃጠሎ አጋጥሞታል። በዚህም ህይወቱ የመትረፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው የተባለው::

“አንድ ላይ በመሆን ፋሽዝምን ለመታገል ቆርጠን እንነሳ፤  ልዩነቶችን የሚፈጥሩ ስርዓቶችን እንታገል” በማለት ከአደጋው ጥቂት ደቂቃዎች አስቀድሞ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ያሰፈረው ፈረንሳዊ ወጣት ፤ “ማኽሮን [የአሁኑ የፈረንሳይ ፕሬዝደንት]፣ ፍራንስዋ ኦላንድን እና ኒኮላስ ሳርኮዚን [የቀድሞ ፕሬዝደንቶች]፣ እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት ስለገደሉኝ ተጠያቂ የሚሆኑት እነሱ ናቸው። የወደፊት ህይወቴን አጨልመውታል” ሲል የሰላ ትችት ሰንዝሯል።

የ22 ዓመቱ ተማሪ ድርጊቱን ለመፈጸም ሰዎች የሚበዙበተን ስፍራ የመረጠውም ሆነ ብሎ እንደሆነም መሰናበቻዬ ባለው ጽሑፍ ላይ በግልጽ አስቀምጧል።

 

LEAVE A REPLY