የአድዋ ጦርነት ሲዘከር ከጀግኖች አባቶቻችን እና እናቶቻችን መሃከል “በተለይ” የሚጠቀሱ ወይም ሊጠቀሱ የሚገባቸው ጀግኖች አሉ፡፡ አድዋ በተዘከረ ቁጥር አፄ ምኒሊክን መጥቀስ ግድ ነው፡፡ እቴጌ ጣይቱን እና የጦር ስልታቸውን መጥቀስ ግድ ነው፡፡ የተኮሱትን የመድፍ ጥይት በጠላት መድፍ አፍ ውስጥ የቀረቀሩትን ሊቀ መኳስ አባተን መጥቀስ ግድ ነው፡፡ ሌሎችም እንዲሁ በስም እየተጠቀሱ የሚዘከሩ ጀግኖችን ያስታውሰናል፡- አድዋ፡፡
ከእነዚህ በርካታ ጀግኖች መሃል በዛሬው ዕለት (የካቲት 22) በተለየ መልኩ ሊታወሱ የሚገባቸው ጀግኖች አሉ፡- እንደነ ባሻ አውአሎም ያሉ፡፡ የካቲት 22 ለሊት 1888 ዓ.ም ለጀግኖቻችን “የመጨረሻዋ ለሊት” ማለት ናት። በመጨረሻዋ ለሊት ለየት ያለ ጀግንነት ከፈፀሙት መሃል አንዱ ደግሞ ባሻ አውአሎም ናቸው።
.
ባሻ አውአሎም ሐረጎት፤ የኢንቲጮ ተወላጅ ናቸው፡፡ ባሻ አውአሎም የካቲት 22 ቀን 1888 ከጣሊያን ጦር ጋር ወደአድዋ እየተጓዙ ነበር፡- ያውም የጣሊያንን ጦር እየመሩ፡፡ የካቲት 22 ቀን ለሊት ለየካቲት 23 አጥቢያ በጄኔራል ባራቴሪ የሚታዘዘው የጣሊያን ጦር በባሻ አውአሎም መንገድ መሪነት ከአድዋ ተራሮች ፊት ለፊት ተፋጠጠ፡፡
ይኼን ጊዜ ባሻ አውአሎም በድንገት ከጣሊያን ጦር መሃል አፈትለከው ወደኢትዮጵያውያን ገበሬ ተዋጊዎች ምሽግ ገሰገሱ፡፡
ጄኔራል ባራቴሪ ከጉያው አፈትለከው ወደ ኢትዮጵያውን ጦር የሚሮጡትን ባሻ አውአሎምን አያቸው፡፡ እና ጮክ ብሎ ጠራቸው፡፡
“ባሻ አውአሎም! ባሻ አውአሎም!”
ባሻ አውአሎም ሩጫቸውን ሳይገቱ ጥቂት ዘወር ብለው እንዲህ አሉት፡-
“ዛሬ አንተን አያድርገኝ!”
እናም ዘለው ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያንን ጦረኞች ተቀላቀሉ፡- አሉላ አባነጋ ከሚመሩት ጦር ጋር፡፡
የታሪክ መዛግብት ባሻ አውአሎም ከጦርነቱ አስቀድሞ ከጣሊያን ጦር ጋር እንዲሰሩ ሆን ተብሎ ተመልምለው የተላኩ የአርነት አርበኛ ናቸው ይላቸዋል፡፡ ከጣሊያን ጋር አብረው፤ ለጣሊያን አድረው፤ ጣሊያንን ሰልለው እንዲመጡ በትዕዛዝ የተላኩ፤ የታዘዙትንም በቁርጠኝነት የፈፀሙ አርበኛ መሆናቸውን ታሪክ ይዘክርላቸዋል፡፡
የታሪክ መዛግብት እንደሚዘክሩት ባሻ አውአሎም ጣሊያኖች ባልፈለጉት ጊዜ እና ሁኔታ ወደጦርነት እንዲገቡ በማድረግ የተሳካ ስራ ሰርተዋል፡፡ በእሳቸው የስለላ ጥናት መሰረት የኢትዮጵያ ተዋጊዎች የጦርነት ብልጫ ማግኘት እንዲችሉ አስተዋፅኦ አድርገዋል ይላሉ፡፡
እነሆ የካቲት 22 ቀን 1888 ዓም ለሊት ባሻ አውአሎም ከአሉላ አባነጋ ጦር የተቀላቀሉበት- ለሊቱን ሙሉ ብርቱ ጦርነት የተደረገበት – በበነጋታው የአድዋ ድል የጥቁሮች ሁሉ ድል መሆኑ የተበሰረበት ቀን ነው፡፡
ክብር ለአድዋ ጀግኖች አባቶቻችን!

























