አምባሳደር ዴቪድ ሺን አሜሪካ ለግብፅ እያደላች መሆኑን ተናገሩ

አምባሳደር ዴቪድ ሺን አሜሪካ ለግብፅ እያደላች መሆኑን ተናገሩ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኢትዮጵያና በቡርኪና ፋሶ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ዴቪድ ሺን የህዳሴው ግድብ የውሃ አሞላል ድርድርን አስመልክቶ የአሜሪካ መንግሥት ለግብጽ እያደላ መሆኑን ገለጹ::

የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ዴቪድ ሺን ከህዳሴው ግድብ የውሃ አሞላል ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን እያካሄዱ ባሉት ድርድር ዙርያ የአሜሪካ ግምጃ ቤት በዶናልድ ትራምፕ ተወክሎ በታዛቢነት መግባቱን እንደሚያውቁ ጠቅሰው፣ ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ መግለጫ እስከ መስጠት መድረሱ ግራ እንዳጋባቸው በብሎጋቸው ላይ በጽሑፍ አስፍረዋል፡፡

የትሬዥሪ መምሪያው ሓላፊ ስቲፈን ምኑቺን ባለፈው አርብ ይፋ ባደረጉት መግለጫ በአሜሪካ አደራዳሪነት ተደረሰበት ያሉትን ስምምነት ግብጽ ለመፈረም ዝግጁ መሆኗን በአድናቆት ማውሳታቸው እንግዳ ነገር ነው  ሲሉም ዴቪድ ሺን አካሄዱን አጣጥለዋል፡፡

ተደራዳሪዎቹ አካላት ስምምነት ላይ ስለመድረሳቸው አንዳችም በይፋ የሚታወቅ ነገር አለመኖሩን የጠቀሱት አምባሳደር ሺን መግለጫው ድርድሩ በስምምነት ሳይቋጭ የመጨረሻ ሙከራና ግድቡን ውሃ የመሙላት ሥራ መካሄድ የለበትም ሲል ኢትዮጵያን ማስጠንቀቁ አስገራሚ መሆኑን አምባሳደሩ አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ስምምነቱን ለመቀበል ዝግጁ ስለመሆኗ ምልክት እንኳ እንዳልሰጠች፣ ሌላው ቀርቶ ሱዳንም ስምምነቱን መቀበል አለመቀበሏን እንዳላሳወቀች አምባሳደር ዴቪድ ሺን ያስታወሱት አምባሳደር ዴቪድ፤ በእንዲህ ዓይነቱ ድርድር ላይ ሚና ሊኖረውና መግለጫ ሊሰጥም የሚገባው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ሆኖ ሳለ፣ የግምጃ ቤቱ መምሪያ በኢትዮጵያ ላይ ጫና የሚያሳድር መግለጫ ማውጣቱ አሜሪካ ለግብጽ እያደላች ነው የሚል ጥርጣሬ እንደሚያሳድር በግልፅ ጽፈዋል፡፡

LEAVE A REPLY