ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው ኢንተርኔት ልማት ጉባዔ በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል።
በአዲስ አበባ ከተማ በመካሄድ ላይ የሚገኘውን ጉባዔ የአፍሪካ ኢንተርኔት ሶሳይቲ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን ያዘጋጀው ሲሆን እስከ የካቲት 26 2012 ዓ.ም ድረስ ቀጥሎ እንደሚካሄድም ታውቋል።
በኢንተርኔት ልማት ጉባዔው ላይም በመቶዎች የሚቆጠሩ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የአገር ውስጥ እና ዓለም ዐቀፍ የግል ሴክተር ድርጅቶች፣ የዘርፉ ምሁራን እና የሲቪል ማኅበራት በመሳተፍ ላይ ናቸው።
ጉባዔው በቆይታው በአገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎትና ቴክኖሎጂ ጥራት እና ተደራሽነት ጋር ተያይዞ ያሉ ጉዳዮችን እና ችግሮችን ለይቶ እንደሚወያይ ይጠበቃል።
የአገር ውስጥ የኢንተርኔት መሠረተ ልማቶችን በማሻሻል ዓለም ዐቀፋዊ እና ቀጠናዊ የኢንተርኔት መሠረተ ልማቶችን በተሻለ መልኩ ለመጠቀም የሚያስችሉ የቴክኒክ አማራጮችንም በመለየት እንደሚመክር ታውቋል።
ለሁለት ቀናት ቀጥሎ የሚካሄደው ጉባዔው በኢትዮጵያ ምቹ የሆነ የኢንተርኔት ሥነ ምህዳር እንዴት መፍጠር ይቻላል የሚለው ላይ ምክረ ሐሳቦችን በማስቀመጥ ያጠናቅቃል ነው የተባለው።

























