ዘዉዲቱ ሆስፒታል በኮሮና የተያዙ ባለሙያዎችን ሥራ ላይ አላሰማራሁም ቢልም፤ ተገልጋዮች ግን መረጃ...

ዘዉዲቱ ሆስፒታል በኮሮና የተያዙ ባለሙያዎችን ሥራ ላይ አላሰማራሁም ቢልም፤ ተገልጋዮች ግን መረጃ አለን እያሉ ነው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የተረጋገጠ የሕክምና ባለሙያዎቹን በሥራ ላይ አሰማርቷል በሚል የተወቀሰው ዘውዲቱ ሆስፒታል ወሬው ሐሰተኛ ነው ሲል አስተባባበለ።

ሁኔታውን በቅርብ እናውቃለን የሚሉ ታካሚዎችና ለሆስፒታሉ ቅርበት ያላቸው ግለሰቦች መረጃው ትክክለኛ እንደሆነና በቫይረሱ የተያዙ የሕክምና ባለሙያዎች አሁንም ሥራ ላይ ይገኛሉ ሲሉ በመከራከር ላይ ናቸው።
እውነታውን ማጣራት ያልቻሉ ሰዎች ሰሞኑን የሚናፈሰውን ወሬ ያስተጋቡ እንጂ ሆስፒታሉ ምንም ዓይነት በቫይረሱ የተያዙ የሕክምና ባለሙያዎችን አላሰማራም ያሉት የዘውዲቱ ሆስፒታል ዳይሬክተር  ዶክተር ኤደን አለማየሁ፤ የሆስፒታሉ ሠራተኛ የሆነ አንድ የጤና ባለሙያ በቫይረሱ መያዙ ከተረጋገጠ በኋላ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኝ የለይቶ ማቆያ እና የሕክምና እርዳታ መስጫ ማዕከል ተለይቶ እንዲቀመጥ አድርገናል ሲሉ ገልፀዋል።
በዘውዲቱ ሆስፒታል ውስጥ በቁጥር የበዙትን ሕመምተኞች በበቂ መንገድ ማስተናገድ በማያስችል ሁኔታ የሕክምና ባለሙያዎች እጥረት በመኖሩ፤ የኮቪድ 19 ቫይረስ የተገኘባቸው በሆስፒታሉ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ የሕክምና ባለሙያዎች በሥራ ገበታቸው ላይ እንዲቆዮ ተደርገዋል ሲሉ የአይን እማኞች እየተከራከሩ ናቸው።
የዳይሬክተሯን ማስተባበያ ያጣጣሉት እነዚህ ታካሚዎችና አስታማሚዎች፤ በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል የተባሉት የጤና ባለሙያዎ ፣ የሚገቡበት እና የሚወጡበት በር የተለየ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያደርጉ ቢሆንም፣ ከበሽተኞችና ከአስታማሚውች ጋር በሚኖራቸው የተለያዮ ንክኪዎች በሆስፒታሉ ግልጋሎት እያገኘን ያለን ሰዎች አሁንም ስጋት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

LEAVE A REPLY